አሜሪካ ግሪንላንድን ለመያዝ በሚያስችሏት አማራጮች ላይ እየመከረች መሆኑን ዋይት ሐውስ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ወታደራዊ ኃይል መጠቀምን ጨምሮ ግሪንላንድን የአገሪቱ አካል ለማድረግ በሚያስችሏቸው "የተለያዩ አማራጮችን" በተመለከተ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
ዋይት ሐውስ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ የኔቶ አባል በሆነችው ዴንማርክ ስር የምትገኘው እና ከፊል ራስ ገዝ የሆነችውን ግሪንላንድን የመቆጣጠር ዕቅድ "ቅድሚያ የሚሰጠው የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ" ነው።
ነጩ ቤተ መንግሥት ይህንን አስተያየት የሰጠው፤ ትራምፕ የአርክቲክ ደሴትን ለመቆጣጠር ባላቸው ፍላጎት ምክንያት እየተገፋች ካለችው ዴንማርክ ጎን የቆሙ የአውሮፓ መሪዎች ከአገሪቱ ያላቸውን ድጋፍ ከገለጹ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አሜሪካ ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ግሪንላንድ "እንደምታስፈልጋት" ደጋግመው ሲናገሩ ነበር።
በትራምፕ ተደጋጋሚ አስተያየቶች ያልተደሰቱት የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬደሪክሰንም በአሜሪካ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የኔቶ መጨረሻ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ዋይት ሐውስ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ "ፕሬዝዳንቱ እና ቡድናቸው ይህንን አስፈላጊ የውጭ ፖሊሲ ግብ ለማሳካት በተለያዩ አማራጮች ላይ እየተወያዩ ነው። በእርግጥም፤ የአሜሪካን ጦር መጠቀም ሁል ጊዜም በጦር ኃይሎች ዋና አዛዡ እጅ ያለ አማራጭ ነው" ብሏል።
የሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ አገራትን ያቀፈው ወታደራዊው ጥምረት ኔቶ አባላት መከካከል አንዳቸው ላይ የውጭ ጥቃት ቢሰነዘር አገራቱ እገዛ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
ማክሰኞ ዕለት ስድስት የአውሮፓ አገራት ለዴንማርክ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። የዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ፣ ስፔን እና የዴንማርክ መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ "ግሪንላንድ የሕዝቧ ነች፣ በግንኙነታቸውን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መወሰን የሚችሉትም ዴንማርክ እና ግሪንላንድ ብቻ ናቸው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአርክቲክ አካባቢ የደህንነት ጉዳይ ላይ እንደ አሜሪካ ሁሉ ራሳቸውም ፍላጎት እንዳላቸው የአውሮፓ መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህም ቢሆን ግን መሳካት ያለበት አሜሪካንም ጭምር አባል በሆነችነት በኔቶ ስብስብ "በጋራ" መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
በተጨማሪም "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መርሆዎች የሆኑት ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የድንበር የማይደፈር መሆን" እንዲከበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጄንስ ፍሬድሪክ ኒልሰን አጋር አገራቱን መግለጫው በደስታ የተቀበሉት ሲሆን "አክብሮት የተሞላበት ውይይት" እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። "ውይይቱ፤ የግሪንላንድ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በግዛት አንድነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በሚያከብር መልኩ መከናወን አለበት" ሲሉም አቋማቸውን አሳውቀዋል።
የግሪንላንድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ዳግም የውይይት አጀንዳ የሆነው፤ የአሜሪካ ሠራዊት ኤሊት ኃይሎች የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ይዘው፤ በኒውዮርክ ፍርድ ቤት እንዲቆሙ ያደረጉበት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በተፈጸመ በኋላ ነው።
የቬንዙዌላው ወታደራዊ ዘመቻ ከተከናወነ አንድ ቀን በኋላ፤ የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ባለቤት የሆኑት ኬቲ ሚለር፤ አሜሪካ ካርታ የተቀመጠበት የግሪንላንድን ካርታን፤ "በቅርቡ" ከሚል ጽሁፍ ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተዋል።
ሰኞ ዕለት ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት ባለቤቷ ስቴፈን ሚለር፤ "ግሪንላንድ የአሜሪካ አካል መሆን አለባት የሚለው የአሜሪካ መንግሥት ይፋዊ አቋም ነው" ብለዋል።
አማካሪው ሲኤንኤን ላይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ አሜሪካ ግሪንላንድን ለመጠቅለል በምታደርገው ጥረት ኃይልን ከመጠቀም እንደምትቆጠብ እንዲያረጋግጡ በተደጋጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "በግሪንላንድ የወደፊት ሁኔታ ላይ ማንም ከአሜሪካ ጋር አይዋጋም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።















