ተታልለው በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የተሳተፉ ደቡብ አፍሪካውያን በፑቲን ፈቃድ መለቀቃቸው ተገለጸ

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲሳተፉ የተገደዱ 17 ደቡብ አፍሪካውያን መለቀቃቸው ተገለጸ።

ተታልለው በጦርነቱ ተሳትፈዋል የተባሉት ወጣቶች እንዲለቀቁ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መሆናቸውን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ገልጸዋል።

ደቡብ አፍሪካውያኑ የጥበቃ ሥራ ሥልጠና እሰጣለሁ በሚል ተቋም ተታልለው ሩሲያ ከሄዱ በኋላ በጦርነቱ እንዲሳተፉ እንደተገደዱ በመግለጽ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት እንዲታደጋቸው ተማጽነዋል።

ፑቲን ወጣቶቹን በማስለቀቃቸው ራማፎሳ አመስግነዋቸዋል።

ከደቡብ አፍሪካውያኑ መካከል አራቱ ወደ አገር ቤት እንደተመለሱ የፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የተቀሩት 11ዱም "በቅርቡ" ወደ አገራቸው እንደሚገቡ ተገልጿል።

ደቡብ አፍሪካውያኑ በምን ሁኔታ እንደተመለመሉ ለማወቅ ምርመራ ተከፍቷል።

የደቡብ አፍሪካ ሕግ ያለ መንግሥት ፈቃድ ለሌላ አገር ቅጥረኛ ተዋጊ መሆንን አይፈቅድም።

ደቡብ አፍሪካውያኑ ሩሲያ ከደረሱ በኋላ የፈረሙት ኮንትራት በሩስያኛ የተጻፈ እንደነበር ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቋንቋውን ባለማወቃቸው ምክንያት ኮንትራቱ የቅጥረኛ ተዋጊ መሆኑን እንዳልተገነዘቡም ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

የራማፎሳ ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዌንያ "ሞስኮ ሁለት ሰዎች ቀርተዋል። አንደኛው ሆስፒታል ሲሆን ሌላኛው የጉዞ ሰነዱን እያስጨረሰ ይገኛል" ብለዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ከሳምንት በፊት ራማፎሳ ከፑቲን ጋር መወያየታቸውንም አክለዋል።

"ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከልባቸው ፕሬዝዳንት ፑቲንን አመስግነዋል። ጥያቄያቸውን በቀናነት አስተናግደው ወጣቶቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ አመቻችተዋል" ሲሉም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ወጣቶቹ የተመለመሉት በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ልጅ ዱዱዚሌ ዙማ-ሳምቡድላ መሆኑ ቢገለጽም ክሱን አስተባብላለች።

"በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ሆነ ብዬ የአገሬን ልጆች ለአደጋ አላጋልጥም" ማለቷም ተዘግቧል።

የእንጀራ እህቷ ንኮስዛና ዙማ-ሙኩቤ ለፖሊስ ከከሰሰቻት በኋላ ነበር ማስተባበያውን የሰጠችው።

ወጣቶችን ለሩሲያ ጦር መልምለዋል በሚል የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ከወራት በፊት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል። በፖሊስ ከተያዙት መካከል ታዋቂ የራድዮ መሰናዶ አቅራቢ ትገኝበታለን።

ተጠርጣሪዎቹ በዋስ የተለቀቁ ሲሆን ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ማየትም አልጀመረም።