ሲፒጄ፤ የአዲስ ስታንዳርድ ፈቃድ መሰረዝ "ሂሳዊ ዘገባዎችን የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው" ሲል ተቃወመ

የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ዕትሞች

የፎቶው ባለመብት, addis standard

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት '' 'ብሔራዊ ጥቅም' እና 'የሚዲያ ሥነ-ምግባር' የሚሉ ግልጽ ያልሆኑ ድንጋጌዎችን" በመጠቀም መገናኛ ብዙኃንን "ዝም እያሰኘ ነው" ሲል በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተቸ።

የሲፒጄ የአፍሪካ ዳይሬክተር አንጄላ ኩዊንታል፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የወሰደው እርምጃ "የቁጥጥር ሳይሆን የበቀል ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ይህንን ያለው፤ የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን ፈቃድ መሰረዙን ተከትሎ ትናንት ማክሰኞ የካቲት 17/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃዱን የሰረዘው አዲስ ስታንዳርድ "የሀገርንና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል" በማለት ነው። የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባዎች "የሚዲያ ሥነ ምግባርን" እና "የኢትዮጵያን ሕጎች" እንደጣሱ በመግለጽም ከስሷል።

የአዲስ ስታንዳርድን ዘገባዎች "አደገኛ ተግባር" ሲል የገለጸው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፤ መገናኛ ብዙኃኑ "እንዲታረም እና ከአጥፊ አካሄዱ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ምክር ሲሰጥ ቢቆይም ለመታረም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል" ብሏል።

"በሚዲያ ዘርፉ ላይ የሙያ ሥነ ምግባር እና የሀገርና የሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም አክብሮ እንዲሠራ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ" መስጠቱንም በመግለጫው ጠቅሷል። "በመሆኑም የአዲስ ስታንዳርድ የበየነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ምስክር ወረቀት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ መሠረት ከዛሬ ጀምሮ ተሰርዟል" ሲል ውሳኔውን አሳውቋል።

ይህንን ውሳኔ የተቃወመው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ፤ "የአዲስ ስታንዳርድን ፈቃድ የመሰረዝ እርምጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሂሳዊ ዘገባዎችን ለማጥፋት ሆነ ተብሎ የሚካሄድ ዘመቻ አካል ነው" ብሏል። የሲፒጄ የአፍሪካ ዳይሬክተር አንጄላ፤ "ይሄ የበቀል እንጂ የቁጥጥር እርምጃ አይደለም" ሲሉ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን እርምጃ በጽኑ ተቃውመዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "' 'ብሔራዊ ጥቅም' እና 'የሚዲያ ሥነ-ምግባር' የሚሉ ግልጽ ያልሆኑ ድንጋጌዎችን እንደ መሣሪያ" እየተጠቀመ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በእነዚህ ድንጋጌዎች አማካኝነት "ገለልተኛ ጋዜጠኝነትን ዝም እያሰኘ" እንደሆነ ተናግረዋል።

የሲፒጄ አርማ

የፎቶው ባለመብት, cpj

የምስሉ መግለጫ, "የአዲስ ስታንዳርድን ፈቃድ የመሰረዝ እርምጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሂሳዊ ዘገባዎችን ለማጥፋት ሆነ ተብሎ የሚካሄድ ዘመቻ አካል ነው" - ሲፒጄ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዳይሬክተሯ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "በአስቸኳይ" የመገናኛ ብዙኃኑን ፈቃድ እንዲመልስ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ "በፕሬስ ላይ የሚፈጽሙትን እየተባባሰ የመጣ ጥቃት" እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

የአዲስ ስታንዳርድ ፈቃድ የተሰረዘው "በገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚፈጸመው አፈና እየተባባሰ በመጣበት ወቅት" እንደሆነ በመግለጫው ያነሳው ሲፒጄ፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን እና ወኪሎቻቸው ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን ዘርዝሯል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከአንድ ወር በፊት የዋዜማ ራድዮን በበይነ መረብ መገናኛ ብዝኃን የዕውቅና ፈቃድ በተመሳሳይ ሰርዟል። ዋዜማ ላይም ይህ እርምጃ ሲወሰድ በምክንያትነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ "የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ" ዘገባዎችን ማውጣት የሚለው ነው።

የዋዜማ ዘገባዎች "ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት አስተያየት እና ምላሽ ያልተካተተበት፣ ሁከት ቀስቃሽ፣ የሙያ ሥነ ምግባርን የጣሰ እንዲሁም የአንድ ወገን ዘገባ ብቻ የተንጸባረቀበት ሆኖ ተገኝቷል" ሲል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከስሷል።

በዚህም ምክንያት መገናኛ ብዙኃኑ የተሰጠውን ፈቃድ እንዲመልስ መደረጉን አስታውቋል። ዋዜማ ራድዮ የተወሰደበትን እርምጃ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ፈቃዱን መመለሱን አረጋግጧል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እርምጃ "በማንኛውም መመዘኛ ትክክል ነው ብሎ እንደማያምን" የገለጸው ዋዜማ፤ ውሳኔው "እንዳሳዘነው" ገልጿል። የቀረቡበትን ክሶች በተመለከተም "የኢትዮጵያን ሚዲያ ለሚከታተሉ ተደራሲዎች፣ ታዛቢዎች እና ባለሙያዎች የሕሊና ፍርድ እንተዋለን" ብሏል።

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ደግሞ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዘጋቢዎቹን ሦስት ፈቃድ ለማደስ አለመፍቀዱን አስታውቋል። አፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ለመዘገብ ተፈቅዶላቸው የነበሩ ጋዜጠኞቹ ፈቃድም እንደተሰረዘ ገልጿል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በሮይተርስ ላይ እነዚህን እርምጃዎች የወሰደው ዜና ወኪሉ የኢትዮጵያ መንግሥት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል "የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሥልጠና ካምፕ ማቋቋሙን" የሚገልጽ የምርመራ ዘገባ ካወጣ በኋላ መሆኑን አስረድቷል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

ጥር ወር ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዘጠኝ የጀርመኑ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢዎች ፈቃድ ታግዶ ነበር። ሰባቱ ዘጋቢዎች ታኅሣሥ ላይ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ቢፈቀድላቸውም፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ ሁለት ዘጋወቢዎች በቋሚነት ታግደዋል።

በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት የፈረንሳዩ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) የኢትዮጵያ ዘጋቢ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዝ እንደታገደ የዜና ወኪሉ አስታውቋል።

በትናንትናው ዕለት የተሰረዘው አዲስ ስታንዳርድም ቢሆን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ቢሮው በፀጥታ አካላት እንደተበረበረ እና በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች መወሰዳቸውን ገልጾ ነበር። ኋላ ላይ የኤሌክትሮኒክ መገልገያዎቹ ሲመለሱ "በተደረገ ሙያዊ ፍተሻ የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌሮች (malware)" ተጭኖባቸው እንደተገኙ መገናኛ ብዙኃኑ በወቅቱ አስታውቋል።

አዲስ ስታንዳርድ አሁን የተወሰደበትን እርምጃ በተመለከተ ባወጣው ዘገባ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን እንደሰጠ መግለጹን ውድቅ አድርጓል። የመገናኛ ብዙኃኑ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር፤ "አዲስ ስታንዳርድ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ደርሰውታል የሚለው ክስ ከእውነት የራቀ ነው" ሲሉ እንደተናገሩ አዲስ ስታንዳርድ ባወጣው ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።

ዋና አዘጋጁ፤ "የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን ቀደም ሲል ስለነበሩ የሕግ ጥሰቶችም ሆነ ስለተወሰዱ እርምጃዎች ለአዲስ ስታንዳርድ የዜና ክፍል በይፋ ያሳወቀው ነገር የለም" ሲሉም ተቃውመዋል።

አዲስ ስታንዳርድ መጽሔት አሳታሚ የሆነው 'ጃኬን ፐብሊሺንግ' ከተወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ "መብቱን ለማስከበርና የሕግ የበላይነት መከበሩን ለማረጋገጥ ያሉትን የሕግ አማራጮች እየገመገመ እንደሚገኝ" ዋና አዘጋጁ ተናግረዋል ተብሏል።