ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ይዞታ ከደረጃዋ ስታሽቆለቁል፣ ኤርትራ ከዓለም መጨረሻ ሆነች

ማይክሮፎኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ይዞታዋ በዘንድሮው በዓለም የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ደረጃ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት በአራት ደረጃ ዝቅ ብላ 145ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ይፋ አደረገ።

ለዓመታት በዓለም ጨቋኝ በሆነ የፕሬስ ነጻነት ይዞታዋ የምትታወቀው ጎረቤት አገር ኤርትራ በፕሬስ ነጻነት ደረጃው ላይ ከዓለም የመጨረሻውን ቦታ ይዛለች።

ዛሬ ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም. የሚከበረውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድኑ ባወጣው የአገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ውስጥ 180 አገራት የተካተቱ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ የፕሬስ ነጻነት ከዚህ በፊት ከነበረው ዝቅ ባለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

በጋዜጠኞች አያያዝ እና በፕሬስ ነጻነት ይዞታ በኩል ከጥቂት ዓመታት በፊት ከፍተኛ መሻሻልን አስመዝግባ የነበረችው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ደረጃዋ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከነበረችበት የ141ኛ ደረጃ በዚህ ዓመት በአራት ደረጃዎች በማሽቆልቆል 145ኛ ደረጃ መድረሷን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ለበርካታ ዓመታት በዚህ የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ደረጃ በመጨረሻ ላይ የምትገኘው ኤርትራም እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም በመጨረሻው የ180ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ሪፖርቱ እንዳመለከተው ሰባት የአፍሪካ አገራት የፕሬስ ነጻነት አመልካች ሰንጠረዡ ላይ ወደ ታችኛው ደረጃ ያሽቆለቆሉ ሲሆን፣ በተለይ 143ኛ ላይ የምትገኘው ኡጋንዳ፣ 145ኛ ላይ ያለችውኢትዮጵያ እና 146ኛ ደረጃን የያዘችው ርዋንዳ ወደ "በጣም አሳሳቢ" ምድብ ውስጥ የተንሸራተቱ አገራት መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ከፍተኛ የፕሬስ ነጻነት ጭቆና ያለባት ኤርትራ በሰንጠረዡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ 180ኛ ሆና የቀጠለች ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ነጻ ሚዲያ በአገሪቱ ካለመኖሩ ባሻገር ዳዊት ይስሃቅ የተባለውን ጋዜጠኛ ለረጅም ዓመታት በማሰር ክብረ ወሰንን ይዛለች ብሏል።

ኖርዌይ፣ ኢስቶኒያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዲን፣ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ፖርቱጋል፣ ስዊትዘርላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ የፕሬስ ነጻነት ከሚከበርባቸው አገራት ቀዳሚውን 10 ደረጃ ይዘዋል።

በፕሬስ ነጻነት የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ካለፈው ዓመት በሁለት ደረጃ ዝቅ ብላ 57ኛ የሆነችው የዩናይትድ ስቴስ የፕሬስ ነጻነት ይዞታ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መመለሳቸውን ተከትሎ እያሽቆለቆለ መሆኑን አመልክቷል።

ሪፖርቱ ጨምሮም የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የመንግሥት ተቋማትን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ለነጻ ሚዲያዎች የሚደረገው ድጋፍ እንዲቋረጥ እና ጋዜጠኞችን የማግለል እርምጃ ወስዷል ሲል ወቅሷል።

የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በዚህ ዓመት ሪፖርቱ ላይ በዓለም ዙሪያ ያለው የፕሬስ ነጻነት ይዞታ "ከመቼውም ጊዜ በባሰ ዝቅ ብሏል" በማለት አሳሳቢ ሁኔታ ማጋጠሙን እና የፕሬስ ነጻነትን መከታተል ከጀመረበት ካለፉት 23 ዓመታት ወዲህ የዚህ ዓመት ውጤት ዝቅተኛው መሆኑን አመልክቷል።

መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው ቡድኑ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ባወጣው ሪፖርቱ "ከዓለም ሕዝብ ከግምሽ የሚበልጠው [ከፕሬስ ነጻነት ይዞታቸው አንጻር] 'በጣም አሳሳቢ' በሚባሉ አገራት ውስጥ ይኖራል ብሏል።

ይህ የአገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ የሚውጣው ባለሙያዎች በየአገራቱ በጋዜጠኞች ላይ ያጋጠሙ አደገኛ ክስተቶችን እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑትን ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም የደኅንነት ይዞታን በመገምገም ነው።