ለ23 ዓመታት እስር ላይ ያለው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ የሰብአዊ መብት ተሸላሚ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, The Edelstam Foundation
ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለ23 ዓመታት የታሰረው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሀቅ የሰብአዊ መብት ተሸላሚ ሆነ።
በኤርትራ እስር ቤት ያለበት ሁኔታ የማይታወቀው ጋዜጠኛው ለንግግር ነጻነት ባደረገው ትግል በስዊድን ተሸላሚ ሆኗል።
ኤርትራዊ እና ስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዳዊት፣ ‘ኤድልስታም’ የተባለ ሽልማት የተበረከተለት “ልዩ ለሆነ ጀግንነቱ” እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል።
የኤርትራ የመጀመሪያው ነጻ ጋዜጣ የሆነው ‘ሰቲት’ መሥራች ከሆኑት አንዱ ነው።
እአአ በ2001 ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠይቅ ጽሑፍ በጋዜጣው ላይ ከታተመ በኋላ ነበር በኤርትራ መንግሥት በቁጥጥር ሥር የዋለው።
የኤርትራ መንግሥት ወደ 20 የሚጠጉ ከፍተኛ ሚኒስትሮችን፣ የፓርላማ አባላትን እና ገለልተኛ ጋዜጠኞችን ሲያስር ዳዊትም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነበር።
ባለፉት ዓመታት የኤርትራ መንግሥት ዳዊት የት እንዳለ እና ስለ ጤናውም ሁኔታ መረጃ አልሰጠም። ከዳዊት ጋር አብረው የታሰሩ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።
ለሰብአዊ መብት በመታገል አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጠው የሽልማት ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው እአአ የፊታችን ኅዳር 19 በስቶክሆልም ነው።
የዳዊት ልጅ የሆነችው ቤተልሔም በአባቷ ስም ሽልማቱን የምትቀበል ይሆናል።
በሰቲት ጋዜጣ ላይ ካቀረባቸው ጽሑፎች መካከል የኤርትራን መንግሥት የሚተቹ እና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም የንግግር ነጻነት እንዲከበር የሚጠይቁ ይገኙበታል።
ለእስር የዳረጉትም እነዚህ ጽሑፎች ናቸው።
ለዳዊት ሽልማቱን የሰጠው ኤድልስታም ፋውንዴሽን ጋዜጠኛው ከእስር እንዲለቀቅ በተደጋጋሚ ጠይቋል።
ዳዊት የት እንደሚገኝ የኤርትራ መንግሥት እንዲያሳውቅ እና ጠበቃ እንዲቆምለትም ጥያቄ አቅርቧል።
የኤድልስታም ሽልማት የዳኞች ቡድን ኃላፊት ካሮላይን ኤድልስታም “ዳዊት ይስሀቅ በዓለም ለረዥም ጊዜ በእስር ላይ ያለ ጋዜጠኛ ነው። የሚገኝበት ቦታ አለመታወቁ እና የጤናው ሁኔታ ያሳስበናል። በወንጀል አልተከሰሰም። ቤተሰቦቹ እና ጠበቆች እንዲጎበኙት አልተፈቀደም። ይህም በግዳጅ የተሰወረ ሰው ያደርገዋል” ብለዋል።
አክለውም “አይበገሬነቱ እና ጀግንነቱ ለንግግር ነጻነት ያለውን ቁርጠኛነት ይመሰክራሉ” ሲሉ ስለ ጋዜጠኛው ተናግረዋል።
ኤድልስታም ፋውንዴሽን በስዊድናዊው ዲፕሎማት ሀራልድ ኤድልስታም መታሰቢያነት ሽልማት የሚሰጠው ለሰብአዊ መብት በመታገል ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ነው።
ኤርትራ የግል መገናኛ ብዙኃን የሌለባት ብቸኛዋ አፍሪካዊ አገር ናት።
እአአ በ2001 “ብሔራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ” በሚል የግል መገናኛ ብዙኃን ተዘግተዋል።
ዳዊት ወደ ስዊድን የተሰደደው እአአ በ1987ቱ የኤርትራ ጦርነት ወቅት ሲሆን፣ ኤርትራ ነጻ አገርነቷን ካወጀች በኋላ የስዊድን ዜግነት አግኝቶ በ1993 ወደ ኤርትራ ተመልሷል።
ኤርትራ አገር ከሆነች በኋላ በአገሪቱ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሥልጣነ መንበሩን ከ30 ዓመታት በላይ ተቆጣጥረውት ይገኛሉ።












