“በውሃ ጥማት አለቅን”፡ ጎርፍ እና የነዳጅ ብክለት የሚፈትናት ደቡብ ሱዳን

ደቡብ ሱዳን

የደቡብ ሱዳን አርብቶ አደሮች ከአነስተኛ ጉድጓድ ውስጥ የደፈረሰ ውሃ ያወጣሉ። መጠጣት የሚችሉት ውሃ ግን አይደለም።

የአካባቢው መሪ ቺሎክ ፑዎት ውሃው የደፈረሰው “በአካባቢው ነዳጅ ስላለ እና ከኬሚካል ጋር ስለተደባለቀ ነው” ይላሉ።

ኒታባህ የአካባቢው ነዋሪ ናት። ዩኒቲ ስቴት በተባለው አካባቢ ከብቶችን ታረባለች። አካባቢው በነዳጅ ሃብት ይታወቃል።

“ውሃውን ስንጠጣው ያስለናል። መተንፈስም ያቅተናል። ውሃው እንደተበላሸ እናውቃለን። ግን መሄጃ የለንም። በውሃ ጥም እየሞትን ነው” ትላለች።

የቀድሞ የነዳጅ መሃንዲስ ዴቪድ ቦጆ ሌጁ እንደሚለው፣ በአካባቢው ያለው ጎርፍ ቆሻሻ ወደ ውሃው እንዲገባ እያደረገ ነው።

ያልተጠበቀ ጎርፍ ከተከሰተ በኋላ በአካባቢው ያለው ሳር ከውሃ በታች ሆኗል። ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ተባብሷል።

ባለሙያው እንደሚለው ጎርፍ ላይ የአካባቢ ብክለት እና የነዳጅ ተረፈ ምርት ተደማምረው “ዝምተኛ ገዳይ” ሆነዋል።

ደቡብ ሱዳን የዓለም አዲስ አገር ናት። ድሃ አገርም ናት። መንግሥት ዋነኛ መተዳደሪያው ያደረገው ነዳጅን ነው።

ዩኒቲ ስቴት ደግሞ ቀዳሚ የነዳጅ ክምችት ያለው አካባቢ ነው። በአካባቢው ጎርፍ በብዛት ይከሰታል።

በአውሮፓውያኑ በ2019 የተከሰተው ጎርፍ መንደሮችን ያጥለቀለቀ እና ደን ያወደመ ነበር።

ጎርፉ ከዓመት ዓመት እየተባባሰ ነው።

በ2022 የዩኒቲ ስቴት ሁለት ሦስተኛው በውሃ ተውጦ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።

አሁንም የአካባቢው 40 በመቶ ከውሃ በታች ነው።

መሃንዲሱ ለስምንት ዓመታት ግሬተር ፓዮነር ኦፕሬቲንግ ካምፓኒ ለተባለ የነዳጅ ተቋም ሠርቷል።

ተቋሙ የማሌዥያ፣ የሕንድ እና የቻይና ነዳጅ አምራች ድርጅቶች ጥምረት ነው። የደቡብ ሱዳን መንግሥት 5 በመቶ ድርሻ አለው።

ዋነኛ የነዳጅ መተላለፊያ ከተቀደደ በኋላ በአካባቢው ከውሃ ጋር የተደባለቀውን ነዳጅ ፎቶ ማንሳት ጀመረ።

የአካባቢው አፈርም በነዳጁ ተበላሽቷል። በቦታው አርብቶ አደሮች ይኖራሉ።

ከነዳጅ መተላለፊያ ትቦ የሚፈስ ነዳጅ በአካባቢው በተደጋጋሚ ይከሰታል።

የተበላሸ አፈርን በድብቅ ከአካባቢው ለማስወገድ ጥረት እንደሚደረግ የሚናገረው መሃንዲሱ፣ ቅሬታውን ለነዳጅ ተቋሙ ቢያሳውቅም መፍትሄ አላገኘም።

“አፈሩን ለማከም አይቻልም” የሚል ምላሽ ነበር የተሰጠው።

ከውሃ ጋር የሚደባለቀው እና ሃይድሮካርቦንን ጨምሮ ሌሎችም በካይ ኬሚካሎችን የያዘው ነዳጅ አሁንም ስጋት ነው።

ከዓለም አቀፍ መርህ በተቃራኒው ከፍተኛ የነዳጅ መጠን ያለው ውሃ በአካባቢው ይገኛል።

“ይህ ውሃ ተመልሶ በአካባቢው ይለቀቃል። ወደ ወንዝ ስለሚሄድ ሰዎች ይጠጡታል። ዓሣ የሚገኝበት ኩሬ ውስጥም ይገባል” ይላል።

“አንዳንዱ ኬሚካል ከመሬት በታች ሰርጎ ከውሃ ጋር ይደባለቃል። ውሃው ተበክሏል” ሲልም ያክላል።

በ2019 ጎርፍ ሲበረታ ነዳጁ ከውሃው እንዳይደባለቅ ለማድረግ ቢሞከርም የጎርፉ መጠን ከፍተኛ ስለሆነ ማስቆም አልተቻለም።

ጎርፍ ላይ የአካባቢ ብክለትና የነዳጅ ተረፈ ምርት ተደማምረው “ዝምተኛ ገዳይ” ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, David Bojo Leju

የምስሉ መግለጫ, ጎርፍ ላይ የአካባቢ ብክለትና የነዳጅ ተረፈ ምርት ተደማምረው “ዝምተኛ ገዳይ” ሆነዋል።

ሮሪክ በተባለው አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በተመለከተ መረጃ የለም። ነዋሪዎች ውሃው የተበከለ ስለሆነ ከብቶች እየታመሙ እንደሆነ ያምናሉ።

ያለ እግር ወይም ጭንቅላት የሚወለዱ የቀንድ ከብቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

የዩኒቲ ስቴት የግብርና ሚኒስትር ባለፉት ሁለት ዓመታት ነዳጅ በፈጠረው የአካባቢ ብክለት ሳቢያ ከ100 ሺህ በላይ ከብቶች መሞታቸውን ይናገራሉ።

በሮሪክ አቅራቢያ ባለው ደን ውስጥ ነዋሪዎች ለከሰል ዛፍ ይቆርጣሉ።

በጎርፍ ሳቢያ በተበላሸ መንገድ ለስምንት ሰዓት ተጉዘው ነው ደኑ ውስጥ የገቡት።

ያልተበከለ ውሃ ያለው በዚህ ደን አከባቢ ብቻ ነው።

በአካባቢው የምትኖረው ኒያካል እንደምትለው የተበከለው ውሃ ፈልቶ ቢጠጣም የሆድ ህመም ያስከትላል።

ሌላው ነዋሪ ኒዬዳ ከሰል በመሸጥ ሰባት ልጆቿን ማሳደግ እንዳለባት ስትናገር እንባ እየተናነቃት ነው።

የምትኖው በቤንቲዩ አቅራቢያ ነው። ጦርነት እና ጎርፍ ሸሽተው ወደ 140 ሺህ ሰዎች በቦታው ይኖራሉ።

የተወሰነ የምግብ እርዳታ ቢያገኙም ዓሣ በማስገር ለመተዳደር ይሞክራሉ።

ንጹህ ውሃ ግን እየተመናመነ ነው።

ኒዬዳ የጉድጓድ ውሃን ለማብሰል እና ለማጠብ ትጠቀምበታለች። ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለመግዛት ግን ገንዘብ ትፈልጋለች።

የጤና ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞች እንደሚሉት፣ የንጹህ ውሃ እጥረት እና የአካባቢ ብክለት ነዋሪዎችን እየፈተኑ ነው።

ቤንቲዩ ባለ ሆስፒታል ውስጥ አንድ እናት የወለደችው ልጅ አፍ እና አፍንጫ የተጣበቀ ነው።

ነዳጅ የበከለው ውሃው ወደ ወንዝ ስለሚሄድ ሰዎች ይጠጡታል። ዓሣ የሚገኝበት ኩሬ ውስጥም ይገባል።
የምስሉ መግለጫ, ነዳጅ የበከለው ውሃው ወደ ወንዝ ስለሚሄድ ሰዎች ይጠጡታል። ዓሣ የሚገኝበት ኩሬ ውስጥም ይገባል።

ዶ/ር ሳሙኤል ፑዎት እንደሚሉት ነዳጅ እና ውሃ ከተደባለቀበት ጉድጓድ ውስጥ የተበከለ ውሃ መጠጣት ብዙ ሕጻናት ከአካል ጉዳት ጋር እንዲወለዱ ምክንያት ሆኗል።

እግር የሌላቸው ወይም ጭንቅላታቸው ትንሽ የሆነ ልጆች እየተወለዱ ነው። ሕጻናቱ ተወልደው በቀናት ውስጥ ይሞታሉ።

መንግሥት ይህንን ጉዳት እንዲመዘግብ ዶክተሩ ያሳስባሉ።

መረጃው በአግባቡ ስለማይመዘገብ ከሕጻናቱ ምን ያህሉ ከአካል ጉዳት ጋር እንደሚወለዱ በግልጽ አልተቀመጠም።

በአሜሪካው ዬል ዩኒቨርስቲ የአካባቢ እና ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኒኮል ዴዚል “በነዳጅ ምክንያት የተከሰተ ብክለት የተጎዱ ሕጻናት እንዲወለዱ ያደርጋል” ይላሉ።

የዘረ መል መዛባት፣ ኢንፌክሽን እንዲሁም የሕጻናት እድገት ውስንነት ሊያስከትል እንደሚችልም ያስረዳሉ።

“በማሳያነት የተመዘገቡ ሪፖርቶች የአካባቢ ብክለትን ጉዳት ይጠቁማሉ” ይላሉ።

ሆኖም ግን የተደራጀ መረጃ ከሌለ የአካባቢ ብክለት ያሳደረውን ጉዳት ማሳየት እንደሚከብድ ያክላሉ።

በአውሮፓውያኑ ከ2014 እስከ 2017 የጀርመኑ ተቋም ሳይን ኦፍ ሆፕ ወደ ዩኒቲ ስቴት ተጉዞ ጥናት ሠርቷል።

በውሃ ውስጥ ከፍተኛ የጨው እና የብረት መጠን አግኝቷል። ከሰዎች ላይ በተወሰደ የፀጉር ናሙና ከፍተኛ የሊድ እና የባሪየም መጠንም ተመዝግቧል።

ይህም በነዳጅ ምክንያት የተፈጠረ ብክለትን ያሳያል።

የነዳጅ ኢንዱስትሪው እያሳደረ ያለውን ጫና ለመመርመር መንግሥት የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችን አሰማርቷል። ውጤቱ ግን ዓመት ዘግይቶ ነው ይፋ የሆነው።

የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊ ሜሪ አያን ማጆክ ለዓመታት ነዳጅ አካባቢውን እየበከለ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በሩዋንግ የተወለዱት ፖለቲከኛዋ የአገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ናቸው።

አንድ የዘመዳቸው ልጅ “የተወለደው ከአካል ጉዳት ጋር ነው” ብለዋል።

መገለልን በመፍራት ስለ ጤና እክሉ እምብዛም አይወራም። የሕክምና አገልግሎት ውስንነትም ሌላው ችግር ነው።

ደቡብ ሱዳን በአውሮፓውያኑ 2011 ስትመሠረት “ብልሹ አሠራር ያለው ኢንዱስትሪን” ተረክባለች ይላሉ ፖለቲከኛዋ።

በ2013 የእርስ በእርስ ጦርነት ሲነሳ፣ በግጭት የምትናጠው አገር በነዳጅ ምርት ላይ የተመረኮዘ ምጣኔ ሃብት ነበራት።

የአካባቢ ብክለትን ማስወገድ “የመሪዎቻችን ዋነኛ ጉዳይ አልነበረም” ይላሉ ሜሪ አያን ማጆክ።

ሕግ እና ተቋማት ቢኖሩም ተጠያቂነትን ማስፈል እንዳልተቻለ ያስረዳሉ።

“ስለ ነዳጅ ማውራት የመንግሥትን ልብ እንደመንካት ነው” ሲል መሃንዲሱ ዴቪድ ቦጆ ሌጁ ይናገራል።

አሁን ስዊድን ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆ እየኖረ ነው።

ቤኒቱ ያለ ሆስፒታል ውስጥ አንድ እናት የወለደችው ልጅ አፍና አፍንጫ የተጣበቀ ነው።
የምስሉ መግለጫ, ቤኒቱ ያለ ሆስፒታል ውስጥ አንድ እናት የወለደችው ልጅ አፍና አፍንጫ የተጣበቀ ነው።

በ2020 የደቡብ ሱዳንን መንግሥት ለመክሰስ ከአንድ ጠበቃ ጋር ተነጋግሯል።

በፍርድ ቤት ምስክርነት ሊሰጥ ሲል ግን በፀጥታ ኃይሎች ታግቶ ተደበደበ። የምስክርነት ቃሉን እንዲያጥፍም ተደረገ።

በዚህም ምክንያት ከአገር የሸሸው ወዲያው ነበር። ጠበቃውም ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሳይወስድ ቀረ።

ግሬተር ፓዮነር ኦፕሬቲንግ ካምፓኒ እና የደቡብ ሱዳን መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ከቢቢሲ ቢጠየቁም ምላሽ አልሰጡም።

በዩኒቲ ስቴት ያለው ጎርፍ ስለመቀነሱ ባለሙያዎች እርግጠኛ አይደሉም።

በአሜሪካው የካሮላይና ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ክላይሜት ሀዛርድስ ሴንተር ኃላፊ ዶ/ር ክሪስ ፈንክ እንደሚለው፣ እአአ ከ2019 አንስቶ በምዕራብ ሕንድ ውቅያኖስ ሙቀት እየጨመረ ነው።

ይህም የተባባሰው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑን ያስረዳል።

ከፍተኛ ሙቀት ሲኖር ከፍተኛ እርጥበት ማመቅ ይችላል። በምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ሙቀት የሚባባሰውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው።

"ውሃው እንደተበላሸ እናውቃለን። ግን መሄጃ የለንም። በውሃ ጥም እየሞትን ነው”
የምስሉ መግለጫ, "ውሃው እንደተበላሸ እናውቃለን። ግን መሄጃ የለንም። በውሃ ጥም እየሞትን ነው”

ባለሙያው እንደሚያስረዳው፣ በቪክቶሪያ ሐይቅ አካባቢ ከፍተኛ ዝናብ እየተከሰተ ይገኛል። በደቡብ ሱዳን የሚታየው ከፍተኛ የጎርፍ መጠን የዚህ አካል ሲሆን፣ እየተባባሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሙቀት እና እርጥበት ሲጨምር አንዳንድ አካባቢዎች “ለመኖር የማይቻልባቸው” እንደሚሆኑ ያክላል።

በሮሪክ አካባቢ ልጆች የሚጫወቱት የጭቃ ጎጆ እና በሬ በመሥራት ነው።

ቤንቲዩ የሚኖሩ አዛውንት ሴቶች ውሃ የሚቀዱት ከተበከለው ጉድጓድ ነው።

“ውሃው እየቀነሰ ቢሄድም ጥራጥሬ እተክላለሁ። ለመብቀል ዓመታት ቢወስድበትም እተክላለሁ” ትላለች አንዲት ነዋሪ።

ካርታ