የእስራኤል መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡት ዋና አቃቤ ህግ ምርመራ እንደተከፈተባቸው አይሲሲ አስታወቀ

ካሪም ኻን የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል እና የሐማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡት ዋና አቃቤ ህግ ፈጽመውታል በተባለ ጾታዊ ጥቃት ዙሪያ የውጭ ምርመራ ማካሄዱን ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አስታወቀ።

ካሪም ኻን በሂደቱ ውስጥ እንደሚሳተፉ እና ምርመራው በሚካሄድበት ጊዜ በሥራቸው እንደሚቀጥሉ አይሲሲ ገልጿል። አቃቤ ህጉ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

የፍርድ ቤቱ የበላይ ተቆጣጣሪ ምርመራውን እንዲመሩ ዋና አቃቤ ህጉ ቢጠይቅም አይሲሲ ግን "የውጭ ምርመራ" እንደሚቀጥል ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

ያልተፈለገ ጾታዊ ንክኪ እና “ጥቃትን” የሚያካትት ምርመራ ኻን ላይ መጀመሩን መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውን ተከትሎ ነው ተቋሙ መግለጫ ያወጣው።

ኻን በሰጡት መግለጫ "ከዚህ ቀደም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምርመራ እንዲደረግ ተጠርቶ እንደ ነበር" ገልጸዋል።

"በዚህ ሂደት ውስጥ በደስታ እሳተፋለሁ" ከማለት ባለፈ ምርመራው በሚካሄድበት ወቅት "በሌሎች የአቃቤ ህግ ኃላፊነቶች" እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በአቃቤ ህጉ ላይ የሚደረገው ምርመራ የሚመለከቱ ማንኛቸውም ጉዳዮች ለእሳቸው ተጠሪ ባልሆኑ ምክትል አቃቤ ህጎች የሚታይ ይሆናል። ይህም “የሁሉም ሰዎች መብት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ያደርጋል” ብለዋል።

ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በኻን ያልተፈለገ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞብኛል ያለች የህግ ባለሙያ የአይሲሲ የበላይ ጠባቂ የሆነው ኢንዲፔንደንት ኦቨርሳይት ሜካኒዝም (አይኦኤም) ብቃት ላይ ጥያቄ አንስታለች።

ኻን ቅሬታ አቅራቢዋን ብቻዋን እንዲያገኟት ቢመከሩም ክሱን ውድቅ እንድታደርግ ለማሳመን ሞክረዋል ሲል ጋዜጣው ጨምሮ ገልጿል።

ግለሰቧ ማንኛውንም ክስ እንድታነሳ ጠይቀዋል መባሉን ኻን ውድቅ እንዳደረጉት ጋርዲያን አስነብቧል።

የፍርድ ቤቱ የበላይ ተቆጣጣሪ ፕሬዝዳንት ፓይቪ ካውኮራንታ በበኩላቸው ባለፈው ወር አይኦኤም ግለሰቧን ለማግኘት መሞከሩን ገልፀው፤ በወቅቱ ምርመራውን ለመቀጠል የሚያስችል አቅም እንዳልነበረው ተናግረዋል።

"ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ እና ፍትሃዊ ሂደት እንዲኖር የውጭ ምርመራ እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

ከጋዛ ግጭት ጋር ተያይዞየእስራኤል እና የሐማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡት አቃቤ ህግ እና አይሲሲ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ ነው።

ኻን፤ መስከረም 26 ሐማስ እስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እና የሃሐማስ መሪ የነበሩት ያህያ ሲንዋር፣ መሐመድ ዴፍ እና እስማኢል ሃኒዬህ በጦር ወንጀሎች እና በሰው ልጆች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ሊጠየቁ እንደሚገባ የሚያሳምኑ ምክንያቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

ሲንዋር፣ ዴፍ እና ሃኒዬህ ክሱ ከቀረበባቸው በኋላ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

ኻን ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ እስራኤልን በግልጽ ጥፋተኛ ባያደርጉም ግን የጾታ ጥቃቱ ውንጀላ እና ሥራውን ለማዳከም የተደረገውን ጥረት "እኔ እና ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሰፊ ጥቃት የሚደርስብን ጊዜ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የጾታ ጥቃት ውንጀላዎቹ ከጋዛ ግጭት ጋር የተገናኘው የእስር ማዘዣ ጥያቄው ከመቅረቡ በፊት የተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

ሦስት ዳኞችን ያቀፈ የአይሲሲ ቡድን ኻን የጠየቁትን የእስር ማዘዣ እየተመለከተው ይገኛል።