ሊቨርፑልን ሲያንቋሽሹ በቪድዮ የታዩት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛ ከሥራቸው ታገዱ

እንግሊዛዊው የእግር ኳስ ዳኛ ዴቪድ ኩት ሥራቸው ላይ ሳሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊቨርፑልን ሲያንቋሽሹ በቪድዮ የተቀረፁት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛ ዴቪድ ኩት ከሥራቸው መታገዳቸው ተሰማ።

ሰውዬው ክለቡን ጨምሮ የቀድሞው የክለቡ አሰልጣኝ ዩርገን ክሎፕን ሲዘልፉ ይታያሉ።

የዳኞች ማኅበር የሆነው ፒጂኤምኦኤል ግለሰቡ ወዲያውኑ ከሥራቸው እንዲታገዱ ተደርገው ምርመራ እንደተጀመረ ገልጿል።

ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ በሰፊው የተሰራጨውን ቪድዮ ቢቢሲ በግሉ ማጣራት አልቻለም። ቪድዮው መች እንደተቀረፀ እና እውነተኛ ስለመሆኑ እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።

ነገር ግን የዳኛው ማኅበር ውስጥ አዋቂ የሆኑ ግለሰብ ማኅበሩ ቪድዮው ትክክለኛ ነው በሚል ምርመራ መጀመሩን ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የ42 ዓመቱ ኩት ባለፈው ቅዳሜ ሊቨርፑል አስተን ቪላን 2-0 ሲረታ የመሐል ዳኛ ነበሩ። በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አሉ ከሚባሉ እና ልምድ ካላቸው ዳኞች መካከል ሲሆኑ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ የፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ቪድዮው ላይ እንደሚታየው ከሆነ ዳኛው እያወሩ ያሉት በ2020 ሊቨርፑል ከበርንሊ ስላደረገው ጨዋታ ነው። ይህ ግጥሚያ 1-1 መጠናቀቁ ይታወሳል።

የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዩርገን ክሎፕ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመሐል ዳኛውን ሲተቹ ይታያሉ። ክሎፕ ዳኛው ለሊቨርፑል ተጫዋቾች ቅጣት ምት አይሰጡም ሲሉ ነው ምሬታቸውን ያሰሙት።

ሐምሌ 2020 ሊቨርፑል ከበርንሊ የነበራቸው ግጥሚያ ከተጠናቀቀ በኋላ ክሎፕ የመሐል ዳኛውን ሲያናግሯቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምርመራ በከፈተበት ቪድዮ ላይ ዳኛው ከአንድ ግለሰብ ጋር ተቀምጠው ክሎፕን ግልፍተኛ ናቸው ያሏቸው ሲሆን በተደጋጋሚ በፀያፍ ቃላት ሲሰድቧቸውም ይሰማል።

ፒጂኤምኦኤል ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ምንም ዓይነት አስተያየት እንደማይሰጥ አስታውቋል።

ቢቢሲ ስፖርት ማጣራት እንደቻለው ከሆነ የሊቨርፑል ኃላፊዎች ስለጉዳዩ የሚያውቁ ቢሆንም ለጊዜው አስተያየት መስጠት አይሹም።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኞች የትኛውን ክለብ እንደሚደግፉ ለዳኛው አስተዳዳሪው ማኅበር የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።

ኖቲንግሀም ከተባለው ሥፍራ የመጡት ዴቪድ ኩት ኖትስ ካውንቲ የተባለው ቡድን ደጋፊ ሲሆኑ የኖትስ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተው ኖቲንግሀም ፎረስት ጨዋታዎችን አይዳኙም ማለት ነው።

በአውሮፓውያኑ 2020 ሊቨርፑል ከበርንሊ በነበራቸው ጨዋታ 1 አቻ ተለያይተዋል። አንዲ ሮበርትሰን ለሊቨርፑል ቀድሞ አስቆጥሮ ቡድኑ መሪነቱን እንዲቆጣጠር ቢያስችልም በርንሊ በጄይ ሮድሪጉዌዝ ጎል አቻ ማድረግ ችሏል። ሊቨርፑል ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር 3 ነጥብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

ከተጠናቀቀ በኋላ የመሐል ዳኛው ዴቪድ ኩት እና በወቅቱ የሊቨርፑል አሰልጣኝ የነበሩት ክሎፕ የቃላት ምልልስ ሲያደርጉ ታይተዋል።