በኪም ቤተሰብ የሚደጎመው የሰሜን ኮሪያ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አነሳስ እና አወዳደቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ለወትሮው ዩናይትድ ስቴትስ ነበረች 25 የጎል ሙከራ የምታደርገው። አሁን ግን ታሪክ ተቀይሯል!”
ይህ ከአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ‘ኮሜንታተር’ የወጣ ቃል አይደለም። ከሄዘር ኦራይሊ እንጂ።
ሄዘር ኦራይሊ በ2007 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለዩናይትድ ስቴትስ ተሰልፋ ግብ አስቆጥራለች። ውጤት፡ አሜሪካ 2 ሰሜን ኮሪያ 2። አሜሪካን አቻ ያደረገችውን ግብ ያስቆጠረችው ኦራይሊ ናት።
ዩናይትድ ስቴትስ እና ሰሜን ኮሪያ እየተጫወቱ ነው። ግጥሚያው ሲጠናቀቅ የሰሜን ኮሪያ ተጫዋቾች ባገኙት ነጥብ እንደመደሰት በሳቷቸው ኳሶች ሲቆጩ አስተዋለች።
ሰሜን ኮሪያ ከዓለማችን እጅግ ተገልላ የምትኖር አገር ናት። መሪዋ ኪም ጆንግ-ኡን ዜጎቻቸው የውጭውን ዓለም እንዲቃኙ አይፈልጉም።
ሰሜን ኮሪያውያን ከተቀረው ዓለም ጋር ሲነፃፀር የኑሮ ደረጃቸው ዝቅ ያለ ነው። ነገር ግን በዓለማችን አሉ ከሚባሉ ጠንካራ የሴት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ከመሆን ያገዳቸው ነገር የለም።
በ2007 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ሰሜን ኮሪያ ከዩናይት ስቴትስ ተገናኙ። በወቅቱ ሰሜን ኮሪያ በሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ነበረች። በ10 ዓመታት ውስጥ ሦስት ጊዜ የእስያ ዋንጫን አንስታለች።
የሰሜን ኮሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን ታመርታለች። በ2016 ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫን አንስታለች። ስፔን፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይን በመርታት ነው ይህን ድል የተቀዳጀችው። በተመሳሳይ ዓመት ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ሰሜን ኮሪያ ነበረች።
“ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር” ስትል ታስታውሳለች ኦራይሊ።
“ከእግራቸው [ከሰሜን ኮሪያ] ኳስ መንጠቅ የማይታሰብ ነው። በጣም ፈጣን ነበሩ።”
ለዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያን መግጠም እጅግ ከባድ ነው። ምክንያቱ ወዲህ ነው። ቡድኖች የተቀናቃኞቻቸውን አጨዋወት በፊልም ይመለከታሉ። የሰሜን ኮሪያን ቪድዮ ግን ማግኘት እጅግ ከባድ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ አበረታች መድኃኒት ትጠቀማለች በሚል ለአራት ዓመታት ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መድረክ ርቃለች። ሲመለሱ እንዴት ይሆኑ ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቡድን አጨዋወትን የሚያሳይ ቪድዮ ማግኘት ተስኗት ይሆናል። ብሪጄት ዌች ግን ይህ አልተሳናትም።
አውስትራሊያዊቷ የቪድዮ ባለሙያ ለአምስት ዓመታት ቡድኑን እየተከታተለች ስትቀርፅ ቆይታለች። በ2009 ለተለቀቀው ዘጋቢ ፊልም እንዲሆን ነው እየተዘዋወረች ስትቀርፅ የነበረው።
እሷ እንደምትለው የአገሪቱ የሴቶች እግር ኳስ ለዚህ የበቃው በመሪዋ ምክንያት ነው።
“ተጫዋቾቹ በተደጋጋሚ ይነግሩናል። ‘የተከበሩ መሪያችን ኪም ጆንግ-ኢል [የኪም ጆንግ አባት] በግላቸው የሴቶች እግር ኳስን ይደግፉ ነበር’ ይሉናል።”
“ለሁሉም ነገር ምስጋና የሚያቀርቡት ለመሪያቸው ነው። ያለእሳቸው መሪነት፣ ድጋፍ እና ምልከታ የሚሆን ገር የለም” ትላለች ብሪጄት።
በአውሮፓውያኑ 1986 ሜክሲኮ በተካሄደው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ስብሰባ ላይ ኖርዌያዊቷ ኤለን ዊሌ ተነስታ በቁጣ እና በብስጭት የታጀበ ንግግር አደረገች።
ንግግሯ የሴቶች እግር ኳስ ተረስቷል። እኛም የዓለም ዋንጫ ውድድር ያስፈልገናል ብላ ተናገረች። ፊፋ ደነገጠ። ባለችውም ተስማማ። ስብሰባው ላይ የተገኙት የሰሜን ኮሪያ ተወካዮች ወደ አገራቸው ሲመለሱ አንድ ዕቅድ ነድፈው ነው።
ንድፈ-ሐሳቡ ቀላል ነው። በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ የእግር ኳስ ሜዳ ይገንባ፤ መልማዮች በየክፍለ አገሩ እየሄዱ ይመልምሉ፤ ቀጥሎ አንድ ማዕከላዊ ማሠልጠኛ ተከፍቶ ጥሩ ብቃት ያላቸው መጥተው የሚሠለጥኑበት ይሁን የሚል ነው።
ለሰሜን ኮሪያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ሽልማቱ ገንዘብ አሊያም ወደ ውጭ አገር ሄዶ መጫወት አይደለም። ወደ ዋና ከተማዋ መዘዋወር እንጂ።
ሕይወት በሰሜን ኮሪያ ቀላል የሚባል አይደለም። በተለይ በገጠራማው ክፍል የምግብ እጥረት አለ፤ የጤና አገልግሎትም በቂ አይደለም።
በ2023 የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ እንደሚጠቁመው ዜጎች የተለያዩ ወንጀሎች ፈፅመው በሚታሰሩባቸው ማጎሪያዎች ወሲባዊ ጥቃት ይፈፀምባቸዋል፤ ከባድ የጉልበት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ከዚህ ሕይወት አምልጠው አገር ጥለው የሸሹ በማጎሪያዎች ውስጥ ሴቶች ያለፍላጎታቸው ፅንስ እንደሚያስወርዱ ይናገራሉ።
በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ግን ሕይወት በተነፃፃሪ የተሻለ ነው። የኑሮ ደረጃው ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ይሻላል፤ የሥራ ዕድልም አለ።
ቁመታቸው ረዣዥም ሕንፃዎች፤ 150 ሺህ ተመልካቾች የሚያስተናግድ ስታድየም፤ የቦውሊንግ መጫወቻ፤ ሱፐርማርኬት፣ የእንስሳት መጠበቂያ መካነ እንስሳ እና ሌሎችም ሌሎችም አሉ።
“ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር ፒዮንግያንግ ውስጥ መኖር ማለት መታደል ማለት ነው” ትላለች ብሪጄት።
“ተጫዋቾቹ እንደ ስጦታ ከመሪያቸው ቤት ተሰጣቸው። ቤተሰቦቻቸውንም ወደ ፒዮንግያንግ ማምጣት ይችላሉ። ለአንዲት ተጫዋች ለብሔራዊ ቡድኑ መመረጥ ማለት ለእሷ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቿም ሕይወት ተቀየረ ማለት ነው።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ የእንግሊዝ ብሔራዊ የሴቶች ቡድንን ለመመልከት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ አይልቅም። በወቅቱ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት ለማየት ወደ ኪምል ኢል-ሱንግ ስታድየም የሚመጡ ሰሜን ኮሪያውያን ቁጥር ግን እስከ 50 ሺህ ይደርሳል።
“ተጫዋቾቹ ከዋክብት ናቸው” ትላለች ብሪጄት። “ደጋፊዎች ያውቋቸዋል፤ ፊርማ ይጠይቋቸዋል።”
ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ማለት ከሰሜን ኮሪያ መውጣት ማለትም ነው። ሰሜን ኮሪያውያን ያለመንግሥት ፈቃድ ከአገር ቤት መውጣት አይፈቀድላቸውም።
“አሜሪካውያን በጣም ረዥም ናቸው። ምክንያቱም ከእኛ የተሻለ ይመገባሉ። እኛ የሌሉን ብዙ ነገሮች አሏቸው። ነገር ግን እኛ አስተሳሰባችን ጠንካራ ነው” ይሏት እንደነበር ታስታውሳለች ብሪጄት።
በ2007 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ሰሜን ኮሪያ ከምድቧ ስዊድን እና ናይጄሪያን ጥላ አለፈች። ነገር ግን በሩብ ፍፃሜው በዋንጫው አሸናፊ ጀርመን ተረትታ ወደቀች።
በ2011 የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቡድን ስም በክፉ ይነሳ ጀመር። ምርመራ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል አምስቱ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አበረታች መድኃኒት ተገኘባቸው።
የሰሜን ኮሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህ ሊሆን የቻለው ተጫዋቾቹ ባሕላዊ መድኃኒት ስለወሰዱ ነው እንጂ አበረታች መድኃኒት ተጠቅመው አይደለም ሲል አስተባበለ።
ጥርጣሬ የገባው ፊፋ ከ2015 የዓለም ዋንጫ አገዳቸው። በ2019 ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ለዓለም ዋንጫ ውድድር መድረስ ተሳናት። በ2023 ሰሜን ኮሪያ ጥላው በነበረው ጥብቅ የኮቪድ መመሪያ ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ መንቀሳቀስ ስላልቻለ በውድድሩ ሳይሳተፍ ቀረ።
የሰሜን ኮሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ እግር ኳስ የተመለሰችው ባለፈው ዓመት ነበር። በእስያ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፋ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።
የሰሜን ኮሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደፊት ምን ሊያሳካ እንደሚችል ማንም ግምቱን ማስቀመጥ አይችልም። ያንቀላፉት አናብስት ይነቁ ይሆን?












