የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ ስለመስፈሩ ምን አለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በሴቶች ማራቶን 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት ባስመዘገበችው ክብረ ወሰን አማካኝነት ስሟ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ዎርልድ ሪከርድስ) ላይ ሰፍሯል።
የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ከቢኤም ደብሊው ማራቶን ጋር በመተባባር በ2023 በበርሊን በተዘጋጁት ውድድሮቸ ላይ ክብረ ወሰን ላሻሻሉ ስፖርተኞች የምስክር ወረቀት ሽልማት ሰጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2023 በጀርመን በርሊን በተካሄደው ማራቶን 11 ክብረ ወሰኖችን ለማሻሻል ታስቦ ስምንት መሳካቱን የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ያሳያል።
አትሌት ትዕግሥት ከቢቢሲ ጋር በነበራት አጭር ቆይታ ወቅት “በሽልማቱ እና በዕውቅናው በጣም ደስተኛ ነኝ” ያለች ሲሆን፣ የሯሷን ክብረ ወሰን ማሻሻል እንደምትፈልግም ተናግራለች።
“ከዚህም በኋላ ሪከርዱን ከዚህ በበለጠ ማሻሻል እፈልጋለሁ. . .ችሎታው አለኝ፤ አቅሙም አለኝ። ስለዚህ ችሎታዬን አዳብሬ ከዚህ የበለጠ ሰዓት መሮጥ እፈልጋለሁ።”
የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቷ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በፓሪስ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ለአገሯ የብር ሜዳሊያ ማስገኘቷ ይታወሳል።
ከ14 ዓመት በፊት ወደ ሩጫ ዓለም የገባቸው ትዕግሥት አሰፋ መስከረም 13/2016 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን በተካሄደው 48ኛው የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ መግባቷ ይታወሳል።
ይህ ከእሷ በፊት የነበረውን ያሻሻለችበት ከሁለት ደቂቃ የበለጠ የጊዜ ልዩነት በማራቶን ውድድር ላይ እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ ትዕግስት ከፍተኛ አድናቆትን ከማግኘቷ ባሻገር፣ ክብረ ወሰኑን ለማሻሻል ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
የ29 ዓመቷ አትሌት እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በተካሄደው የችካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ተመዝግቦ የነበረውን 2:14.04 ክብረ ወሰን ነበር ከሁለት ደቂቃ በላይ ያሻሻለችው።
አትሌት ትዕግሥት የዓለም ክብረ ወሰን መስከረም 20/2017 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ፣ ከተለያየ አገራት የመጡ ከ20 የማይበልጡ የተጋበዙ እንግዶች መገኘታቸውን ገልጻ የምስክር ወረቀቱም በዚያው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተበረከተላት ለቢቢሲ ተናግራለች።
የዓለም ክብረ ወሰንን ካሻሻለች አንድ ዓመት የሞላት ትዕግስት የዓለም ድንቃ ድንቅ የምሥክር ወረቀቱን ለመስጠት ቀድም ብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም እርሷ የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ላይ በመሆኗ መዘግየቱን ተናግራለች።
“እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። እንደ ማራቶን አትሌትም ትልቅ ደስታ ነው የፈጠረብኝ” ስትል ለመጀመሪያ ጊዜ በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ በመስፈሩ ደስታዋ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች።
በአሁኑ ጊዜ በእሷ የተያዘውን የራሷን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ የምትናገረው ትዕግሥት አሰፋ፣ በማራቶን ከ2 ሰዓት ከ10 በታች መግባት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላት ተናግራ ነበር።
ለረዥም ጊዜያት የ800 ሜትር ሯጭ ሆና የቆየችው ትዕግሥት፣ ወደ ጎዳና ላይ ሩጫ ፊቷን ያዞረችው በቅርቡ ነው።
በ2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ800 ሜትር ተሳትፋለች። ሆኖም ከግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ውጪ ሆና ነበር።
ትዕግሥት ከ800 ሜትር በተጨማሪ በ400 ሜትርም ስትወዳደር ቆይታለች።
አትሌቷ ቀደም ሲልም የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ለማሸነፍ በቅታለች።
የበርሊን ማራቶን እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች
በዓለም አትሌቲክስ ውድድር ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የበርሊን ማራቶን በአውሮፓውያኑ 1974 የተጀመረ ሲሆን፣ የዓለም ቁንጮ ሯጮች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።
በጀርመን መዲና የሚካሄደው ውድድር ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከልም አንዱ ነው።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት ያሸነፉ ሲሆን፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ቀዳሚዎች ናቸው።
በሴቶች በኩል ጌጤ ዋሚ ውድድሩን ለማሸነፍ የቻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ስትሆን፣ ጌጤ በ2006 እና በ2007 (እአአ) ውድድሩን በተከታታይ አሸንፋለች።
አፀደ ሃብታሙ፣ አበሩ ከበደ፣ ትርፌ ፀጋዬ፣ አሸተ በከሬ እና ጎይተቶም ገብረ ሥላሴ ውድድሩን ማሸነፍ የቻሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በኮቪድ ወረርሽን ምክንያት ውድድሩ እአአ በ2020 አልተካሄደም።
በአውሮፓውያኑ 2023 የበርሊን ማራቶን ውድድር 55 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከ120 አገራት ተሳታፊ ነበሩ።
48ኛውን ቢኤምደብሊው የበርሊን ማራቶን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቦታው ተገኝተው ተከታትለውታል ተብሎ ይገመታል።
በወንዶች ምድብ ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ የርቀቱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል።
የ37 ዓመቱ ኬንያዊ ውድድሩን 2:01:09 በሆነ ሰዓት አሸንፏል።
ሌላኛው ኬንያዊ ማርክ ኮሪር ሁለተኛ ሲወጣ ኢትዮጵያዊው ታዱ አባተ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ውድድሩን አራት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው።
ኃይሌ እአአ ከ2006 እስከ 2009 (እአአ) በተከታታይ ለአራት ዓመታት ውድድሩን አሸንፏል።












