“የራሴን የማራቶን ክብረ ወሰን ደግሜ የማሻሻል ዕቅድ አለኝ” አትሌት ትዕግሥት አሰፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ተወልዳ ያደገችው ከአዲስ አበባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች በምትርቀው ሆለታ ነው። ስድስት ልጆችን ለታደለው ቤተሰብ እርሷ የመጨረሻ ልጅ ናት።
ሆለታ ውስጥ አራዳ ምሥራቅ ሜዳ በሚባል ትምህርት ቤት የተማረችው ትዕግሥት፣ በትምህርት ቤት በሚደረግ ውድድር ነበር ወደ አትሌቲክሱ የገባችው።
በሩጫው 400 ሜትር፣ 800 ሜትር እንዲሁም ግማሽ ማራቶን ሮጣለች። አገሯን በአፍሪካ ሻምፒዮና፣ በኦሊምፒክ ወክላለች። አሁን ደግሞ ትዕግሥት በአስደናቂ የሰዓት ልዩነት የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ሆናለች። አትሌት ትዕግሥት አስደናቂው ድሏ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጋለች።
ቢቢሲ፡ ወደ አትሌቲክሱ እንዴት አንደገባሽ ታስታውሻለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ ማንንም አይቼ አይደለም አትሌቲክሱን የጀመርኩት። በአጋጣሚ ስፖርት መምህራችን፣ በስፖርት ክፍለ ጊዜ ላይ አይቶኝ ሩጫ እንድጀምር ይመክረኝ ነበር። እኔም የእርሱን ምክር ተቀብዬ ውድድር ላይ ተሳትፌ ጥሩ ሮጥኩኝ። እናም ብዙም ሳልቆይ ወደ ክለብ ገባሁ። በዚያ ነው የአትሌቲክስ ስፖርትን የጀመርኩት።
ቢቢሲ፡ ወደ አትሌቲክሱ እንድትገቢ ምክንያት የሆኑሽን የስፖርት መምህርሽን ታስታውሻቸዋለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ አዎ የስፖርት መምህሬ፣ መምህር ተክለማርያም ይባላሉ። እርሳቸው ናቸው መጀመሪያ ላይ ወደ ስፖርቱ እንድገባ ያደረጉኝ።
ቢቢሲ፡ በወቅቱ አንቺ ላይ ምን የተለየ ነገር ታይቷቸው ይሆን?
አትሌት ትዕግሥት፡ የሚገርመው ሕጻን ሆኜ ራሱ ተራምዶ መሄድ አልችልም ነበር። ሱቅ ምናምን ስላክ በሩጫ ነበር የምሄደው። በጣም ቀጫጫ ነበርኩ። ሁሉም ቦታ በሩጫ ነው የምሄደው። መራመድን አላውቅም። . . .(ሳቅ) ያንን ያዩ ይመስለኛል።
ቢቢሲ፡ ሩጫ ከጀመረሽ ስንት ዓመት ሆነሽ ማለት ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2001 ነው የጀመርኩት። አሁን 13 ወይም 14 ዓመት ይሆነኛል ማለት ነው።
ቢቢሲ፡ በጀርመን በርሊን የዓለም ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ ነው ያሻሻልሽው። ያ ደግሞ በጣም ትልቅ ውጤት ነው። ሪከርዱ በዚያን ያህል ልዩነት ይሰበራል ብለሽ ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ እውነቱን ለመናገር ያን ያህል ይሰበራል ብዬ አላሰብኩም። ነገር ግን ስሰራ የቆየሁት ልምምድ ሪከርድ ለማሻሻል ያለመ ነበር። በዚህ ልክ ግን እሰብረዋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ዕቅዴ 12 እና 13 ቤት ለመሮጥ ነበር። ከአሠልጣኜም ጋር ተነጋግረን ስንሰራ የነበረው ያንኑ ነበር። በእርግጥ ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩኝ። ግን በዚህ ልክ እሮጣለሁ ብዬ አላሰብኩም።
ቢቢሲ፡ ከዚህ በኋላስ ይህንኑ ያንቺን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ዕቅድ አለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ በደንብ. . . በደንብ።
ቢቢሲ፡ እስከ ስንት ድረስ? ለምሳሌ አሠልጣኝሽ ከ2፡10 በታች መግባት ይቻላል ይላል። አንቺ በዚህ ትስማሚያለሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ በደንብ እስማማለሁ። የተሻለ ልምምድ ከተሰራ ይሰበራል። ምክንያቱም ድካም ተሰምቶች አልነበረም የጨረስኩት። አቅም ነበረኝ። ትንሽ የዙሩ [ፔስ] አለመስተካከል ነበር። እሱ እሱን ካስተካከልን ከ2 ሰዓት ከ10 በታች ይሮጣል ብዬ አምናለሁ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢቢሲ፡ ሌላው ዓለም ሲያወራበት የነበረው ስለ ጫማው ነው። አንቺ ነሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጥሽበት። እንዴት ነው ይመቻል?
አትሌት ትዕግሥት፡ ጫማው በጣም ነው የሚመቸው። በጣም ነው የረዳኝ። በጣም አሪፍ ጫማ ነው።
ቢቢሲ፡ ባለፉት 13 ዓመታት ከሮጥሽባቸው ጫማዎች በምን ይለያል?
አትሌት ትዕግሥት፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ትንሽ ከባድ ናቸው። ይህ ግን በጣም ቀላል ነው። . . . ያው ማራቶን ይታወቃል ረዥም ርቀት ነው። በዚህ ውድድር ቀለል ያለ ጫማ ማድረግ ጥሩ ነው። ስለዚህም እኛ አድቫንቴጅ [ዕድል] ሰጥቶናል። ቀላል መሆኑ ይበልጥ ጠቅሞኛል ብዬ ነው የማስበው።
ቢቢሲ፡ ምቾትስ አለው?
አትሌት ትዕግሥት፡ አዎ ምቾትም አለው፤ በጣም ቀላል ነው።
ቢቢሲ፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በበርሊን ማራቶን ላይ አሸንፈሽ ነበር። ከዚያ ግን ጉዳት አጋጥሞሽ ነበር። ምንድን ነበር የደረሰብሽ ጉዳት?
አትሌት ትዕግሥት፡ ከበርሊን በኋላ ትንሽ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። ለበርሊን ስዘጋጅ በጣም ከባድ [ኦቨር] ዝግጅት ሳደርግ ነው የነበረው።
እግሬ ጉዳት ነበረው፤ ከበርሊን በኋላ እረፍት ሳላደርግ ወዲያው ወደ ሌላ ውድድር ነበር የሄድኩት፣ ማረፍ ነበረብኝ። ያ የለንደን ውድድር ላይ እንዳልሳተፍ አድርጎኛል።
በእርግጥ ትንሽ ጉዳት ነበር፤ ነገር ግን ዶክተሩ እንዳትሰለፊ፣ ይህ ትንሽ ጉዳት እየባሰ ከሚሄድ እዚችው ላይ ብናየው ይሻላል። ከፊታችን ኦሊምፒክ ስላለ ይህንን ጉዳት ብናገግም ይሻለል ብሎ መከረኝ። እኔም በዶክተሩ ሃሳብ ተስማምቼ የተወሰነ እረፍት አድርጌ፣ ፊቴን ወደ በርሊን ማራቶን ዝግጅት አዞርኩኝ። ስድስት ወር ነው የተዘጋጀሁት።
ቢቢሲ፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ወጥተሽ የሮጥሽው የት ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ወጥቼ የሮጥኩት ሱዳን ነው በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ። ነገር ግን በዚያው ወደ ቤኒን ሄደናል። በወቅቱ በ400 ሜትር ነበር አገር የወከልኩት።
ቢቢሲ፡ ከዚያ በኋላ ኦሊምፒክ መጣ። ሪዮ ኦሎምፒክ እንዴት ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ ኦሊሎምፒክ ላይ በ800 ነበር የተሳተፍኩት። በወቅቱ በጣም በጉዳት ላይ ነበርኩ። እግሬን በጣም ያመኝ ነበር። አኪለስ (ከቁርጭምጭሚቴ በላይ የሚገኝ ጅማት) በጣም ያመኛል። አጭር ርቀት ነው። 800 ሜትር በጣም ፈጣን ነው። በጣም የፍጥነት ልምምድ ነበር ስንሰራ የነበረው። በዚህም በጣም እግሬን እያመመኝ ነበር። ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። በከባድ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት። ከዚያ በኋላም ወደ 800 አልተመለስኩም። እዚያ ላይ ነው ያቆምኩት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢቢሲ፡ ከዚያ በኋላም የተለያዩ ጉዳቶችን አጋጥመውሽ ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ ከ800 ሜትር በቀጥታ ወደ ማራቶን ነው የገባሁት። ምክንያቱም ሌላ 10 ሺህ 5 ሺህ መሞከር አልቻልኩም። ምክንያቱም በስፓይክ (የመሮጫ ጫማ) መሮጥ አልቻልኩም። ስለዚህ ቀጥታ ነው ወደ ጎዳና ሩጫ የሄድኩት። ሰውነቴ ጫናውን መቋቋም አቅቶት የነበረው ሕመም ተባባሰብኝ።
ግማሽ ማራቶን ስፔን ቫሌንሺያ ላይ ልሮጥ ሄጄ [እኤአ 2019] እዚያ ላይ ተጎድቼ በክራንች ነበር የመጣሁት። ምንድን ነው ስህተቱ የምሮጥበትን ርቀት ስቀይር ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ ነበር። 10 ሺህ፣ 5 ሺህ መሥራት ነበረብኝ። ቀጥታ ከአጭር ርቀት ወደ ማራቶን ነው የገባሁት። ያ ትንሽ ሕመሜን አባብሶብኝ ያ ነው የተፈጠረው።
ቢቢሲ፡ ቫሌንሽያ ላይ ውጤትሽ ምን ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ አምስተኛ ነው የወጣሁት። እያመመኝ ነበር የሮጥኩት። በአንድ እግር ነው የሮጥኩት ማለት እችላለሁ። መቆም እስከማልችል ደርሼ ነው ውድድሩን የጨረስኩት። እና ከባድ ጊዜ ነበር።
ቢቢሲ፡ ህመምሽ ምን ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ የአኪለስ [Achiles] ታማሚ ነኝ። በጣም እየሄድኩ እያለ አኪለሴ በጣም አብጦ ስለነበር በምሄድበት ሰዓት ትናንሽ ስሮች አሉ፣ ወደ መሳሳብ እና መበጠስ ደርሰው ነበር። ወዲያው ውድድሩን ባቋርጠው ኖሮ ለዚያ ጉዳት አልጋለጥም ነበር።
ላለማቋረጥ ብዬ በከባድ ህመም ውስጥ ሁኜ ውድድሩን ጨረስኩት። ማቋረጥ ነበረብኝ፤ እኔ ግን ያንን ህመም ተቋቁሜ ውድድሩን ስጨርስ ግን መቆም አልቻልኩም ነበር፤ ቀጥታ በዊልቸር ነው ወደ ሕክምና የወሰዱኝ።
ቢቢሲ፡ ከዚያ በኋላ የትኞቹ የጤና ባለሙያዎች ናቸው ከዚህ በኋላ መሮጥ አትችይም ያሉሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ ስፔን ነው። ከውድድሩ በኋላ ወዲያው እግሬ አብጦ ስለነበር፣ በአምቡላንስ ነበር ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል የሄድኩት።
ሐኪሞቹ ሲያዩት ከፍተኛ ጉዳት በመሆኑ እነርሱ ናቸው ከዚያ በኋላ ለማገገም እና ቁስሉ ወደ ቦታ ው ለመመለስ ጊዜ ይፈጃል፤ ብትሰሪበትም ጉዳቱ ከዚህ በኋላ ይብሳል የሚል ምክር የሰጡኝ።
እኔ ግን እንዳልሮጥ የሰጡኝም ምክር አልተቀበልኩትም ነበር። ማናጀሬም ዶክተሮቹ ያሉትን አልተቀበለውም። በዚህ አጋጣሚ ማናጀሬን ማመስገን እፈልጋለሁ።
ከዚያ በዚያው ሳምንት ድጋሚ ልታይ ወደ ጣልያን ነበር የሄድኩት። እነርሱም ተመሳሳይ ነገር ነበር የነገሩኝ። ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ተመልሰሽ ወደ ስፖርቱ የመመለስ ዕድልሽ በጣም ጠባብ ነው ነበር ያሉት።
ቢቢሲ፡ ያንቺ ስሜት ምን ነበር እነርሱ ይህንን ሲሉሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ እኔ የሚገርምህ ተስፋ አልቆርጥም። ከዚህም በላይ ገጥሞኛል። ያንን ውድድር [ቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን] በአንድ እግር ነው ሮጬ የጨረስኩት ማለት እችላለሁ። በዚያን ጊዜ ለካ ጤነኛ ከሆንኩኝ፣ ጠንክሬ ከሠራሁ ታሪክ መሥራት ይችላል ብዬ ነበር ያሰብኩት።
በዚያ ወቅት ሐኪሞች ከዚህ በኋላ ወደ ሩጫ አትመለሽም ሲሉኝ፣ ልቤ አልተቀበለውም ነበር። እዚያው ቁጭ ብዬ ለራሴ ሙሉ ጤናዬን አግኝቼ ታሪክ እሰራለሁ ስል ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢቢሲ፡ ከዚያ በኋላ በክራንች ነበር የወጣሽው፤ ለማገገም ምን ያህል ጊዜ ፈጀብሽ?
አትሌት ትዕግሥት፡ ብዙም ጊዜ አልፈጀብኝም። ለአትሌት በክራንች መሄድ ከባድ ነው። ግን ምንድን ነው ያደረግኩት አልተቀመጥኩም። ሕመሙን የሚያሽለኝ እንደዋና ያለ ቀላል ልምምድ ስሰራ ነበረ። በሚገርም ሁኔታ በሁለት ወሩ ነው ለውጥ ያገኘሁት። ምክንያቱም እግሬ ታመመ እንጂ ጭንቅላቴ እና ልቤ አልታመመም ነበር። ያ ነው ቶሎ እንድድን ያደረገኝ።
ቢቢሲ፡ በወቅቱ አንቺ ስለ ሕመምሽ የተሰማሽን ነገርሽኝ። ቤተሰቦችሽ ወይ አሠልጣኞችሽ እንዳንቺ ያስቡ ነበር?
አትሌት ትዕግሥት፡ አዎ አሠልጣኞቼም ችሎታዬን ስለሚያውቁ፣ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት አላቸው። ከእኔ በላይ እንደውም በሰዓቱ እነርሱ ጠንካራ ነበሩ። “ያለሽ ችሎታ ዓለም ላይ ታሪክ ሳይሰራ ታሞ አይቀርም” ሲሉኝ ነበር። ቤተሰቦቼ በተለይ እናቴ፣ ባለቤቴ፣ አሠልጣኞቼ ሲሉኝ የነበረው ነገር ነው በይበልጥ ቶሎ አገግሜ እዚህ እንድደርስ ያደረገኝ። በጣም ነበር ሞራል ሲሰጡኝ የነበረው።
ቢቢሲ፡ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብሽ በባለሙያዎች ከአሁን በኋላ መሮጥ አትችይም ተብለሽ ነበር። አሁን ደግሞ የዓለም ክብረ ወሰንን በእጅሽ አስገብተሻል። ሁለቱን አንዴት ነው የምታስተያያቸው?
አትሌት ትዕግሥት፡ ጉዳቴን መቼም የማልረሳው ነገር ነው። ውስጤ ተጽፎ የተቀመጠ ነገር ነው። ግን ዛሬ ይህችን ቀን ሳያት ደግሞ እንኳን ተጎዳሁ እንድል ነው ያደረገኝ። ምክንያቱም ባልጎዳ ኖሮ ይህችን ቀን አላያትም ነበር። ጠንክሬ አልሰራም ነበር።
ቢቢሲ፡ በሕይወትሽ ተስፋ የቆረጥሽበት ጊዜ አለ?
አትሌት ትዕግሥት፡ እውነቱን ለመናገር ተስፋ የቆረጥኩበትን ጊዜ አላስታውስም።
ቢቢሲ፡ እንደ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ ያሉ አትሌቶችን ሳይ የሚጋሩት ባህሪ አለ፤ እልኸኝነት፤ የሚፈልጉትን ነገር እስኪያሳኩ ድረስ አለመበገር። አንቺስ ባህሪሽ አንዴት ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ በጣም እልኸኛ ነኝ። መሸነፍን አልወድም። (ሳቅ). . . እርሱ ነው መሰለኝ እንዲህ ጠንካራ እንድሆን ያደረገኝ። ያ እልህ ነው እንዲህ ጠንካራ ያደረገኝ። አልሸነፍም ባይ ነኝ። (ሳቅ)
ቢቢሲ፡ ከቤተሰባችሁ ሌላ የሚሮጥ ሰው አለ?
አትሌት ትዕግሥት፡ በጭራሽ የለም። (ሳቅ)
ቢቢሲ፡ አሁን ቀጣይ ዕቅድሽ ምንድን ነው? አሠልጣኝሽ ፓሪስ ኦሊምፒክ ነው ይላል።
አትሌት ትዕግሥት፡ እውነት ለመናገር እስካሁን አልወሰንንም። ለፓሪስ ኦሊምፒክ ግዴታ ሁለት ማራቶን መሮጥ ያለብኝ ይመስለኛል። አልወሰንንም። በእኛ ፍላጎት ቢሆን ጫና ሳናበዛ ቀጥታ ወደ ኦሊምፒክ ብንሄድ የሚል ነው።
ከአሠልጣኜ ጋር ያወራነው ግዴታ በዓመት ሁለት ማራቶን መሮጥ ስላለብኝ በፓሪስ ላይ ለመሳተፍ የለንደንን ማራቶን መሮጥ አለብኝ። ከአሠልጣኜ ጋር ያወራነው ግን ውድድር ሳናበዛ ቀጥታ ወደ ፓሪስ ዝግጅት ብንገባ ነው የተሻለ የሚሆነው እየተባባልን ነው። ምን አንደሚሆን እንግዲህ አንማከርበታለን።
ቢቢሲ፡ ራስሽን የምታዝናኚው በምንድን ነው?
አትሌት ትዕግሥት፡ ፊልም በማየት እዝናናለሁ። ነገር ግን ልምምዴን በጥሩ ብቃት ሠርቼ የመጣሁ ቀን ነው በጣም ደስ የሚለኝ።












