“የዓለም ሻምፒዮና ቁጭት ክብረ ወሰን እንድሰብር አድርጎኛል” ጉዳፍ ጸጋይ

አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በሃንጋሪ ቡዳፔስት

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ የዓለም ሻምፒዮና ቁጭት በዳይመንድ ሊግ ውድድር ክብረ ወሰን እንድሰብር አድርጎኛል አለች።

ጉዳፍ ትናንት እሑድ መስከረም 6/2016 ዓ.ም በአሜሪካዋ ኦሪገን ፣ ዩጂን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር በኬንያዊቷ አትሌት ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል አሸንፋለች።

ከዓለም ሻምፒዮና ውድድር ከተመለሰች በኋላ በነበሩት ቀናት ጥሩ ልምምድ ስታደርግ እንደነበር የምትናገረው ጉዳፍ፣ ወደ ኦሪገን ስታቀና ክብረ ወሰን ለመስበር አልማ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ብርቱ ተፎካካሪዎች ቢኖሩም ትኩረቴ ክብረ ወሰኑን መስበር ላይ ነበር ያደረኩት። ማንም ያሸንፍ ማን ብዙ አላሳሰበኝም ነበር። መስመሬን ተከትየ ነበር ስሮጥ የነበረው” ብላለች።

ጉዳፍ የትናንቱን ውድድር 14 ደቂቃ ከ00.21 በመጨረስ ነበር በክብረ ወሰን ውድድሩን ያሸነፈችው።

በዚህም ጉዳፍ በኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን ተይዞ የነበረውን የዓለም ሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ወድድር ክብረ ወሰን በ5 ሰከንዶች በማሻሻል የግሏ አድርገዋለች።

ፌዝ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በፓሪስ በተደረገ ውድድር 14 ደቂቃ ከ05.20 ሰከንድ በመግባት ነበር ለ8 ዓመታት በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበር የቻለችው።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደምቀው በታዩበትና ነሐሴ ወር ላይ በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ጉዳፍ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ለአገሯ አመጣለሁ ብላ አስባ የነበረ ቢሆንም የተሳካላት አንዱ ነበር።

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ተከታትለው በገቡበት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ጉዳፍ ለአገሯ ወርቅ አስገኝታለች።

በ5ሺህ ሜትር ግን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል።

ይህን ውድድር አሁን ሪከርዷ የተሰበረባት ፌይዝ ኪፕዬጎን ማሸነፏ አይዘነጋም።

አትሌት ጉዳፍ በዚህ ቅር ብሏት እንደነበርና ቁጭት አድሮባት እንደነበር ተናግራለች።

“በቡዳፔስት አንድ ወርቅ ባመጣም ቅር ብሎኛል። ሕዝቡ በጉጉት ይጠብቅ ነበር። ብዙ ጥረት አድርጌ ድንገታዊ በሆነ ህመም ምክንያት ያሰብኩት ሲበላሽ ይከብዳል። ከዚያ ግን ወደ አገሬ ተመልሼ ልምምድ መስራት ጀመርኩ” ብላለች።

በሁለቱ ውድድሮች መካከል ለልምምድ የነበሯት ቀናት አጭር ቢሆኑም ባደረገችው ብርቱ ልምምድ ነው ክብረ ወሰኑን ለማሻሻል የቻለችው።

የአየሩ ሁኔታም ለ5 ሺህ እና 10 ሺህ ውድድር ከባድ ቢሆንም እንደፈራችው ግን አልነበረም። ጥሩ የአየር ሁኔታ ነበር ብላለች ጉዳፍ።

የውድድሩ ሰዓት ማታ ላይ ቢሆን ደግሞ ካስመዘገበችው በተሻለ ሰዓት መሮጥ ትችል እንደነበርም ተናግራለች።

የኢትዮጵያን አዲስ ዓመትን በድል እንደተቀበለችው የምትናገረው ጉዳፍ ፤ “በስፖርት ስኬት ላይ ስትደርስ ቀላል ይመስላል እንጂ፤ ጠንክሬ በመስራቴ እና በበርካታ ሰዎች እገዛ እና ድጋፍ ነው እዚህ ላይ መድረስ የቻልኩት።” ስትልም ጥረቷን አስረድታለች።

ጉዳፍ በቀጣይ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር የተያዘውን ክብረ ወሰን ለመስበር እቅድ እንዳላትም ተናግራለች።

“ትልቁ ነገር ጠንክሮ መስራት ነው። እግዚአብሔር ይረዳኛል። ትልቁ ህልሜ የ10 ሺህን ክብረ ወሰን መያዝ ነው” ብላለች።