ኢትዮጵያውያኑ በደመቁበት ውድድር ሲፈን በጉዳፍ "ተገፍቻለሁ" አለች

Gudaf Sifan

የፎቶው ባለመብት, World Athletics

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በደመቁበት ውድድር ሩጫውን ሲመሩ ከነበሩ አትሌቶች መካከል አንዷ የነበረችው አትሌት ሲፈን "ተገፍቻለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናገረች።

ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10ሺህ ሜትር የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

በውድድሩ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ31፡27.18 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያውን ለአገሯ ስታስገኝ፣ ለተሰንበት ግደይ በ31፡28.16 የዓመቱን የግል ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ እንዲሁም እጅጋየሁ ታዬ የነሐስ ሜዳሊያ ወስዳለች።

ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አስደናቂ ድል በተጨማሪ ሌላኛው መነጋገሪያ ሆኖ ያመሸነው የውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ እና የወርቅ ሜዳሊያ ሊወስዱ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱት አትሌቶች መካከል አንዷ የነበረችው አትሌት ሲፈን ሐሰን የውድድሩ ፍጻሜ ላይ መውደቋ ነው።

ሲፈን የወርቅ ሜዳሊያውን ለማሸነፍ ከአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ጋር አንገት ላንገት ተናንቀው እየተሸቀዳደሙ ሳለ ለውድድሩ ፍጻሜ 20 ሜትር ሲቀራት ወድቃለች።

ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ ስትናገር “በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ተገፍቻለሁ” በማለት ለመውደቋ ምክንያት አትሌት ጉዳፋን ተጠያቂ አድርጋለች።

“በኢትዮጵያዊቷ የተገፋሁ ይመስለኛል። ምን ታደርገዋለሁ? ስፖርት ነው፤ ያጋጥማል። የተሳሳትኩ አይመስለኝም ግን ፍጥነት ላይ እያለሁ የመገፋት ስሜት ተሰምቶኝ እግሮቼን መቆጣጠር አልቻልኩም። ይህ ለእኔ ምንም ማለት አይደለም። ያጋጥማል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሲፈን በቃለ መጠይቋ ክስተቱን በተመለከተ ተገፍቻለሁ በማለት ለስፖርት አስተዳዳሪዎች አቤቱታ የማቅረቧ ዕድል ያነሰ ስለመሆኑ ቃለ መጠይቅ የሰጠችበት ሁኔታ አመላክቷል።

አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ31፡27.18 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያውን ለአገሯ አስገኝታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ31፡27.18 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያውን ለአገሯ አስገኝታለች

ከውድድሩ በኋላ የውድድሩ ቪዲዮች ዳግም ሲታዩ ከሲፈን በስተቀኝ በኩል ስትሮጥ የነበረችው የአትሌት ጉዳፍ እና የሲፈን ክርን ንክኪ ፈጥረዋል።

ክስተቱን በተመለከተ ለቢቢሲ አስተያየቷን የሰጠችው እውቋ እንግሊዛዊት አትሌት ፖውላ ራድክረሊፍ “በትክክል በሁለቱ አትሌቶች መካከል ንክኪ አለ ግን ይህ ንክኪ ለሲፈን መውደቅ በቂ ነው ወይ የሚለው ግን መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው” ብላለች።

ፖውላ በሴቶች የ10ሺህ ሜትር ፍጻሜ ላይ የታየው ክስተት አትሌት ሲፈን በቀጣይ ውድድሯ በእልህ ተሞልታ እንድትወዳደር የሚያደርጋት ነው ብላለች።

አትሌት ጉዳይ ጸጋይ እና አትሌት ሲፈን ሐሰን በቀጣይ 5ሺህ ሜትር ውድድር ይገናኛሉ።

ከዚህ ውድድር በፊት ቅዳሜ ጠዋት የ1ሺህ 500 ሜትር ማጣሪያ አድርጋ ያለፈችው አትሌት ሲፈን ሐሰንም ለቢቢሲ አስተያየቷን ስትሰጥ “በቀጣይ ሁለት ውድድሮች አሉኝ በዛ ላይ የሚሆነውን እናያለን” ብላለች።