ከታሊባን ዐይን የተደበቁት የአፍጋኒስታን ምሥጢራዊ የሴቶች ትምህርት ቤቶች

በድብቅ እየተማሩ ያሉ የአፍጋን ታዳጊ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/ Sandra Calligaro

የምስሉ መግለጫ, በድብቅ እየተማሩ ያሉ የአፍጋን ታዳጊ ሴቶች

በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ለማሰብ እንኳን የሚከብዱ ነገሮች ሲፈጸሙ ይታያሉ።

ዓለማችን ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ ልህቀት አንጻር ሴቶች ትምህርት ለመማር ሲታገሉ ይሰማል።

በተለይም የሴቶች መብት ከደረሰበት አንጻር በመንግሥት ደረጃ ሴቶች ትምህርት መከልከላቸው ሲሰማ ማስገረሙ አይቀርም።

አፍጋኒስታንን እየመራ የሚገኘው ታሊባን ሴቶች እንዳይማሩ ከልክሏል።

ክልከላው ያላገዳቸው አፍጋኒስታውያን ታዳጊ ሴቶችም በድብቅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ምሥጢራዊ ትምህርት ቤቶቹ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ክልከላውን ተከትሎ ነው።

በእነዚህ ድብቅ ትምህር ቤቶች በአብዛኛው የሚያስተምሩት ሴቶች ናቸው።

የታሊባንን ቅጣት ለሚፈሩ በኢንተርኔት አማካኝነት (ኦንላይን)፣ ለደፈሩ ደግሞ በአካል ትምህርታቸውን መከታተል ይችላሉ።

የቢቢሲ አፍጋኒስታን ዘጋቢ ሳና ሳፊ ቢያዙ የሚደርስባቸውን አደጋ ከቁብ ሳይቆጥሩ ለትምህርት እየተጉ ያሉባቸውን ትምህርት ቤቶችን በመዳሰስ በአንደበቷ ትተርክልናለች።

“ትምህርት እየሰረቅኩ እንደሆነ ይሰማኛል” ነበር ያለችው በአፍጋኒስታን ያለች ታዳጊ።

ለንደን ተቀምጬ የዚህች ታዳጊ ንግግር እንደገና በአዕምሮዬ ይመላለስብኛል።

ታዳጊዋ የሚማሩበትን ክፍል በቪዲዮ እያሳየችኝ ነበር።

“ሙሉውን ክፍል ለማየት እንድችል ከኋላ ልትቆሚ ትችያለሸ” ስልም በላፕቶፑ ቪዲዮ እያናገረችኝ ያለችውን ታዳጊን ጠየቅኳት።

በመማሪያ ክፍሉ ውስጥ ቢያንስ ከ30 ያላነሱ ወጣት ሴቶች ይታዩኛል።

ሁሉም በመደዳ የተቀመጡ ሲሆን ከራስ መሸፈኛቸው (ሂጃባቸው) በስተቀር ሙሉ ጥቁር ነው የለበሱት።

መምህራቸውም ሙሉ በሙሉ ጥቁር ለብሳ ነጭ ሰሌዳው አጠገብ ቆማ ትታየኛለች።

በሰሌዳው ከተሳለው ሥዕላዊ መግለጫ እየተማሩ ያሉት ባዮሎጂ (ሥነ ሕይወት) የትምህርት ዓይነት ይመስላል። ተማሪዎቹ ቀስ ብለው ሲነጋሩ፣ ጨዋታቸውም ይሰማኛል።

አሁን እያየሁት ያለው ምሥጢራዊ (ድብቅ) ትምህርት ቤትን ብቻ አይደለም።

እንዲያውም ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል የሴቶች እና የታዳጊዎች የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርስቲ ትምህርት ያገደውን የታሊባንን ክልከላ በመቃወም የተጀመረ እምቢተኝነት ነው።

በድብቅ እየተማሩ ያሉ የአፍጋን ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/ Sandra Calliagro

ልብ የሚሰብር አዙሪት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ እነዚህ ድብቅ የአፍጋኒስታን ትምህር ቤቶች ያደረግኩት ጉዞ ልብ የሚሰብር አዙሪት መሆኑን ያስታወሰኛል።

ከእነዚህ መምህራን እና ተማሪዎች ጋር በኢንተርኔት መስኮት ያደረግኩት ውይይት የራሴን የልጅነት ጊዜ አስታወሰኝ።

በደቡባዊቷ አፍጋኒስታን ካንዳሃር የነበረኝ የትምህርት ወቅት ፊቴ ድቅን አለ።

እኔም በወቅቱ እንደነበሩት አፍጋኒስታናውያን በልጅነቴ በድብቅ ነው ትምህርቴን የተከታተልኩት።

ከመምህሯም ጋር እያወራሁ ጨለማ እና ፈታኝ ከሆኑ ትዝታዎች ጋር እየታገልኩ ነበር።

እንደ ምንም ስሜቴን ዋጥ አድርጌ በትምህርት ቤቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሠራች ጠየቅኳት።

“በመምህርነት ለስድስት ወራት ቆይቻለሁ” አለችኝ።

ሆኖም ፍርሃት አሁንም ቢሆን አልተለያትም።

“ወንድሜ አብዛኛውን ጊዜ እባክሽ ትምህርት ቤቱን ለቀሽ ውጪ ይለኛል” ትላለች።

አክላም “ስለትምህርት ቤቱ የትኛውም ባለሥልጣን አያውቅም፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የታሊባን ባለሥልጣናት ይመጡ ይሆን የሚለው ለወንድሜ ሰቀቀን ሆኖበታል።

“ነገር ግን ወላጆቼ ናቸው እዚሁ ቆይቼ እህቶቼን እንዳስተምር ያሳመኑኝ። የታናሽ እህቶቼን ህመም እጋራለሁ። የእኔም ዩኒቨርስቲ ቢሆን ተዘግቷል። ስለዚህ እነዚህን ታዳጊዎች በማስተማር ማገዝ እፈልጋለሁ” ብላለች።

የመማሪያ ክፍሉ ሕይወት የሞላው ነው።

ባህላዊ የእንጨት የመስኮት ክፈፎች ለክፍሉ ድምቀት ሰጥተውታል።

ግድግዳውም በሥዕሎች አጊጧል።

በእኔ ልጅነት ጊዜ ይህ አልነበረም።

በተማርኩበት በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ አጋማሽ ከነበረው ፍጹም የተቃረነ ነው።

በአፍጋኒስታን ከተከሰተው አሰቃቂ እና ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው ታሊባን፣ የመጀመሪያ እርምጃው ሴቶች እና ታዳጊዎችን ትምህርት እንዳይማሩ መከልከል ነበር።

በድብቅ እየተማሩ ያሉ የአፍጋን ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/ Sandra Calligaro

የመለሱኝ ከትምህርት ቤቱ በር ነበር

በሕይወት እስካለሁ ድረስ በታሊባን አገዛዝ ስር ትምህርት እማራለሁ ብዬ ወደ ትምህርት ቤት ያቀናሁበትን ዕለት መቼም አልረሳውም።

የሰባት ዓመት ልጅ ነበርኩ።

ትምህርት ቤቱ በር ላይ ስደርስ አንዲት ሴት፣ ሴቶችም ሆነ ታዳጊዎች ትምህርታቸውን መከታተል አይችሉም አለችኝ።

እናቴ በቢጫ የተጠለፈ ቀበቶ ሠርታልኝ ስለነበር እሱንም ከጥቁር ዩኒፎርም ጋር ለብሼ ነበር።

ቢጫው ቀበቶም አይፈቀድም ነበር።

ዩኒፎርሜ በጣም አስደስቶኝም ነበር። ነገር ግን ክልከላው ደስታዬን አጨለመው።

ክው ብዬ ወደ ቤት ተመለስኩ።

ወላጆቼ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ ምሥጢራዊ ትምህርት ቤት መፈለግ ጀመሩ።

እንደ ዕድል ሆኖም ቤታቸውን ወደ በርካታ መማሪያ ክፍሎች የቀየሩ ባል እና ሚስትም አገኙ።

ሁልጊዜ ጠዋት፣ ጠዋትም እናቴ ወደ አትክልት ገበያ ትወስደኝ ነበር።

ከዚያም ከጀርባው ወዳለው ከጭቃ ወደተሠራው ምሥጢራዊ ትምህርት ቤት ተደብቄ እገባለሁ።

መምህራኑ የሚያገኟቸውን መጻሕፍት እናነባለን። እንማራለን።

ነገር ግን የጥንዶቹ ትምህርት የማስቀጠል ተስፋ በአሳዛኝው በአጭሩ ተቀጨ።

ታሊባን ስለ ትምህርት ቤቱ ሰማ።

ፀጥታ አስከባሪዎችም ትምህርት ቤታችንን ከበቡት።

ባል እና ሚስቱ መምህሮቼም ለ15 ቀናት ታሰሩ።

ሲፈቱም አፍጋኒስታንን ለቀው ወጡ።

በአሜሪካ የዓለም የንግድ ማዕከል እና ፔንታገንን ጨምሮ ለበርካቶች መቀጠፍ ምክንያት የሆነው ከ20 ዓመት በፊት የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ደረሰ።

ጥቃቱ ከደረሰ ከአምስት ዓመታት በኋላ አሜሪካ እና አጋር ኃይሎች ታሊባንን ከሥልጣን ገረሰሱት።

አጋር ኃይሎቹ አፍጋኒስታን ውስጥ ያደረሱት መከራ እንዳለ ሆኖ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳጊዎች እና ሴቶች የመማር መብታችን ተመለሰ።

ከአስር ዓመታት ትግል በኋላ ታሊባን ከሁለት ዓመት በፊት እንደገና ወደ ሥልጣን ተመልሷል። እንደገናም ሴቶች እና ታዳጊዎች በነጻነት የመማር ዕድልን ተነፈጉ።

በአሁኑ ወቅት ሴቶች አንደኛ እና መለስተኛ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ተፈቅዶላቸዋል። ሆኖም ሴቶች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች እንዳይደርሱ ክልከላ ተጥሎባቸዋል።

ይህም የታዳጊ ሴቶችን ህልም አጨለመ፤ አቅማቸውንም እንዲጨናገፍ ያደረገ ነው።

በአፍጋኒስታን የምሥጢር ትምህርት ቤቶች ውስጥም ፍርሃትን ያሸነፉ መምህራን እና ተሟጋቾች አሉ።

እገዳው ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ምሥጢራዊ ትምህርት ቤቶች በማቋቋም ኃላፊነቱን ወስደው እየሠሩ ካሉ ተሟጋቾች አንዷ ፓሽታና ዱራኒ ናት።

‘ለርን አፍጋኒስታን’ በተሰኘው ድርጅቷ ውስጥ 230 ተማሪዎች ያሏት ሲሆን፣ ሁሉም ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ናቸው።

ምንም እንኳን አደጋው የከፍ እንደሆነ ብትረዳም ዝም ብሎ መመልከት ፍጹም አማራጭ አይደለም ትላለች።

“ትምህርት ባልማር ትዳር ውስጥ እገባ ነበር፤ እህቴም እንዲሁ። ወንድሜም ባይማር ኖር በሕጻንነቱ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ይገደድ ነበር። በመማሬ ምክንያት የቤተሰቤ ኃላፊ ሆንኩኝ። በዕጣ ፈንታዬ ላይ መወሰን ቻልኩ” ትላለች።

ፓሽታና የምታስተምራቸውን ተማሪዎች በማናግርበት ወቅት በተቀላጠፈ እንግሊዝኛ ነው የሚያወሩት። ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ፍልስፍና እንዲሁም እንደ ግራፊክ ዲዛይን ያሉ ተግባራዊ ትምህርቶችን እንደሚማሩ ነገሩኝ።

በርካቶቹ ታዳጊዎች ዲፕሎማት፣ ዶክተር፣ መሃንዲስ የመሆን ምኞታቸውንም ይገልጻሉ።

የታዳጊዎቹ ህልም እንዲሳካ ያላቸው መነሳሳት ቢያስደስተኝም በስጋት ነበር የምመለከታቸው።

ትምህርት ቤቶቹን ታሊባኖች ካገኗቸው እንደሚዘጉ እርግጥ ነው።

በዚህም የእነዚህ ታዳጊዎች የመማር እና የማደግ ቁርጠኝነት እንዲሁ ይገታል።

ታሊባን የትምህርት ዕገዳው ቋሚ አለመሆኑን ይናገራል።

ባለሥልጣናቱ “ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ለመፍጠር እና በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ አስፈላጊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እየሰሩ” እንደሆነም ሲናገሩ ይሰማል።

ሆኖም ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነም፣ እንዲሁም ክልከላው ስለመነሳቱ እና መቼ እንደሚነሳ የታወቀ ነገር የለም።

ታሪካቸውንም ስሰማ የእኔንም ስላስታወሰኝ የተደበላለቀ ስሜት ተሰማኝ። ተስፋ፣ ብስጭት፣ አድናቆት እና ሐዘን።

በአፍጋኒስታን ሴቶች የትምህርት ዕድል ትግል ገና ረጅም ጉዞ ይጠብቀዋል ነገር ግን የእነዚህ ታዳጊዎች፣ መምህራን እና የመብት ተሟጋቾች ቁርጠኝነት የጥንካሬን ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው።

“በእምቢተኝነታችን እና በተቃውሟችን እንቀጥላለን። ምናልባት አንድ ቀን በዋሻው መጨረሻ ላይ ብርሃን እናይ ይሆናል” በማለት አንዲት ተማሪ የነገረችኝ ተስፋን የሚያሳይ ነው።