ናይጄሪያ፤ በደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኛ ተቃውሞ ወቅት ሁለት ዜጎቿ እንደተገደሉባት አስታወቀች

የደቡብ አፍሪካ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው እጃቸውን የዘረጉ ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ናይጄሪያ በደቡብ አፍሪካ የውጭ ዜጎች ዒላማ በተደረጉበት ወቅት ሁለት ዜጎቿ እንደተገደሉባት አስታወቀች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ባወጣው መግለጫ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ኢሜካ ቻርልስ ኢሮግቡ የተባለ ዜጋው አሰቃቂ በሆነ የፖሊስ ምርመራ መገደሉን ገልጿል።

በተመሳሳይ ቀንም የሱቅ ባለቤት የሆነው ሙሳ ዩናና የተባለ ሌላ ዜጋው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድሏል ብሏል።

በቀረበው ክስ ላይ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በዜጎቹ ላይ ግድያው የተፈፀመው በደቡብ አፍሪካ የፀረ ስደተኞች ጥላቻ ባየለበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።

እንቅስቃሴውን ተከትሎ 700 ናይጄሪያውያንን ጨምሮ ወደ 25 ሺህ የሚደርሱ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።

በደቡብ አፍሪካ ያሉ ተቃዋሚዎችም መንግሥታቸው ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

ተቃዋሚዎቹ የውጭ ዜጎች ሥራችንን እየቀሙን ነው፤ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ከሕዝብ አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው የሚሉ ቅሬታዎችን ያቀርባሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ኢሮግቡ ፕሪቶሪያ በሚገኘው ትሽዋኔ ሜትሮ ፖሊስ ጣቢያ ባሉ መኮንኖች እንደተገደለ ገልጿል።

ጆ ደግሞ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 28 ቀን በኢማላህሌኒ ከተማ ከሱቁ ደጅ ላይ ጥቃት እንደደረሰበት ጠቅሷል።

ይህንን እየተከታተለች እንደሆነ የገለፀችው አቡጃ፣ "ስደተኞች ላይ የሚፈፀመውን የደቡብ አፍሪካን ባህል ያልተከተለ፣ ያለመቻቻል ልማድ እንዲሁም የአፓርታይድ ዓይነት ባሕርይ የማይፈታ ከሆነ ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ ናቸው" ብላለች።

ናይጄሪያ ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ለውጡ ዜጎቿ ካሳ እንደምትጠይቅም ገልጻለች።

ለዚህም ዜጎቿ ጥለውት የወጡትን የንግድ ተቋማት እና ንብረቶች እየሰነደች እንደሆነ አሳውቃለች።

ሆኖም የደቡብ አፍሪካ የካቢኔ ሚኒስትር ክሁምቡድዞ ንሻቭሄኑ ዓርብ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግሥታቸው ካሳ እንደማይከፍል እና ናይጄሪያውያን በነፃ ገበያ ሕጋዊ እና የተመዘገበ ንብረታቸውን መሸጥ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሚንስትሯ ጨምረውም " የናይጄሪያውያን የእፅ ማዕከላት የት እንዳሉ ማወቅ እንፈልጋለን። ስለዚህ የት እንዳስቀመጡት ሊነግሩን ይችላሉ። በመሆኑን በፍጥነት በደቡብ አፍሪካ ያለውን እፅ ማፅዳት እንችላለን" ብለዋል።

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ይህንን አስተያየት ያወገዘ ሲሆን " ተቀባይነት የሌለው" ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።

" እንዲህ ዓይነት አዋራጅ ቃላት ፣ ሙያዊ ያልሆነ፣ ሕዝቡን በጅምላ የፈረደ ያልተገመገመ መግለጫ በከፍተኛ ባለሥልጣናት መደረጉ ጥላቻን ይፈጥራል" ሲልም ኮንኗል።

ሚኒስቴሩ አክሎም 'ማርች ኦን ማርች' እና 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' የተባለውን ቡድን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ፀረ ስደተኛ ቡድኖችን " ግጭት እና በሌሎች አፍሪካውያን ላይ ጥላቻ በማነሳሳት" ከስሷል።

እነዚህ ቡድኖች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚገጥማቸውም አስጠንቅቀል።

ሆኖም ናይጄሪያ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ሕብረት ልትወስደው ትችል እንደሆን ወይም ምን ዓይነት እርምጃዎችን እንደምትከተል ግልፅ አይደለም።

በደቡብ አፍሪካ ያሉ አንዳንድ ፀረ ስደተኛ ቡድኖች ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች እስከ ሰኔ 30 ድረስ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ሰጥተው ነበር።

ይህንን ተከትሎ ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት የተወሰኑ ዜጎቸቻውን ካስወጡ የአፍሪካ አገራት መካከል ጋና፣ ማላዊ እና ናይጄሪያ ይገኙበታል።

ደቡብ አፍሪካ በዓለም ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ካለባቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን በቅርብ ወራት ፀረ ስደተኛ ተቃውሞዎች ጨምረዋል።

በአሕጉሩ ያደገ ኢኮኖሚ ያላት ደቡብ አፍሪካ፤ በዝቅተኛ ሥራዎች ላይ ለመቀጠር እና ሥራ ለመፈለግ የሚሹ በተለይ የድሃ አገራት ዜጎችን ትኩረት ትስባለች።