ሕንድ እና ጀርመንን እያወዛገበች ያለችው ሕጻን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜ ያላት ሕጻን ሕንድ እና ጀርመንን እያወዛገበች ትገኛለች።
ሕጻኗ በሁለቱ አገራት መካከል ላለው ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ምክንያት መሆን የጀመረችው ገና የሰባት ወር ጨቅላ እያለች ነው።
ህንዳዊ ቤተሰቦቿ በሕጻኗ ላይ ጥሰት ፈጽማለች በሚል ነው የጀርመን ባለሥልጣናት ከቤተሰቦቿ ነጥቀው ወደ ሕጻናት መንከባከቢያ ማዕከል ያስገቧት።
ልጅቷ በጀርመን በርሊን ከተማ አቅራቢያ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕጻናት በተቋቋመ ማዕከል ውስጥ እንደምትገኝ እናቷ ይናገራሉ።
የሕንድ ምግብ ትወዳለች እንዲሁም ወላጆቿ ለቢቢሲ ባጋሩት ቪዲዮዎች ውስጥ ወላጆቿን ስታይ ምን ያህል እንደምትፈነድቅ አሳይተዋል።
በሰኔ ወር ላይ የበርሊን ፍርድ ቤት የዚህችን ሕጻን ዲያ እና አሚት ብለን የምንጠራቸውን የወላጆቿን መብት ሽሯል።
በሕጋዊ ጉዳዮች ምክንያት የወላጆቿን ማንነት እና መጠሪያቸውን ቢቢሲ መግለጽ አልቻለም።
ሕጻኗም በጀርመን ለሚገኘው የታዳጊዎች የደኅንነት ቢሮ ጥበቃ እንዲያደርግላት ውሳኔ አስተላልፏል።
ወላጆቿ ሕጻኗን ወደ ሕንድ ለመውሰድ ጥያቄ ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል።
ወላጆቿ የፍርድ ሂደቱ የይስሙላ ነው በማለትም ይግባኝ ጠይቀዋል።
እናቷ ዲያ ልጇን ወደ ሕንድ መውሰድ ትችል ዘንድ ድጋፍ ለማሰባሰብ በአሁኑ ወቅት ኒው ዴልሂ ትገኛለች።
ዲያ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ከልጇ ጋር መለያየቷ የፈጠረባትን ሐዘን ስትናገር በእንባ ታጥባ ነው።
አሚት በአውሮፓውያኑ 2018 በርሊን ውስጥ ሥራ ሲያገኝ ከባለቤቱ ጋር ወደ ጀርመን ሄዱ።
ሕጻኗም በየካቲት 2/ 2021 (እአአ) ተወለደች።
በወላጆቿ እና በጀርመን ባለሥልጣናት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው የሰባት ወር ጨቅላ እያለች በደረሰባት ጉዳት ነው።
ይህም በሕጻኗ ብልቷ ላይ የደረሰው ጉዳት እንደሆነ የፍርድ ቤት ሰነዶች ያስረዳሉ።
አንድ ዶክተር “በጨቅላ ሕጻን ላይ እንደዚህ ያለ የከፋ የብልት ጉዳት” አይተው እንደማያውቁ ተናግረው፣ ይህንንም ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት አስረዱ።
የጀርመን የሕጻናት ጥበቃ አገልግሎት በበኩሉ ሕጻኗ የወሲብ ጥቃት ደርሶባታል በሚል ጥርጣሬ የወሰዷት ሲሆን፣ ቤተሰቦቿ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።
ሕጻኗ የታከመችበት ሆስፒታልም ቆይቶ ወላጆቿን ነጻ የሚያወጣ ምስክርነት ሰጥቷል።
የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎች ወሲባዊ ጥቃት ስለመፈጸሙ “ምንም ማስረጃ የለም” ሲሉም ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፣ ፖሊስም ክስ ሳይመሰርት መዝገቡን ዘግቶታል።
ወላጆቿ በበኩላቸው ጉዳቱ በአጋጣሚ የተፈጠረ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ከአሜሪካ እና ከሕንድ የመጡ ሁለት ገለልተኛ ዶክተሮችም የሕጻኗን የሕክምና መረጃ በመመርመር በወላጆቹ ግምገማ ተስማምተዋል።
“ሕጻኗ የደረሰባት ጉዳት በአደጋ የተከሰተ ሳይሆን እንዳልቀረ እናምናለን። ወላጆቿ በተደጋጋሚ ሆን ብለው ጉዳት ካደረሱባት በኋላም በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ቦታ ወስደዋታል መባሉ የማይሆን ነው” ሲሉ የሕክምና ባለሙያዎቹ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል።

ጉዳቷም በተደጋጋሚ በተደረገላት የንክኪ ምርመራ ተባብሶ ሊሆን እንደሚችል እንደሚያኑም ባለሙያዎቹ አክለዋል።
ነገር ግን የሕጻናት ጥበቃ ባለሥልጣናት ሕጻኗ በቤቷ ውስጥ ደኅንነቷ ይጠበቃል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኋላ ለሕጻናት ጥበቃ ተቋሙ በይኗል።
በአሁኑ ወቅት ታዳጊዋ ሁለት ዓመታትን በማደጎ አሳልፋለች። ወላጆቿም ከልጃቸው ጋር መገናኘት ብዙም እየተፈቀደላቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ለወላጆቹ የተመደቡት የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች ወላጆቿን ሲገልጹ “አፍቃሪ እና አሳቢ” በሚል ሲሆን፣ ከልጃቸውም ጋር ባላቸው ግንኙነት ደስታ የተሞላበት እንደሆነ ነው።
በፍርድ ቤት የተመደቡ የሥነ ልቦና ባለሙያም እንዲሁ ከወላጆቿ አንደኛው በተቆጣጣሪ ሥር አብረዋት እንዲኖሩ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ነገር ባለፈው ሳምንት የታዳጊዎች የደኅንነት ቢሮ “ሕጻኗን የሚወስዳት እና የሚመልሳት የለም” በሚል ሁሉንም ጉብኝቶች ሰርዟል። የሕጻኗ እናት ዲያም ልጃቸውን በቪዲዮ ደውለው ለማግኘት እንዳልተፈቀደላቸውም ተናግራለች።
“ልጃችን ከማደጎ ወደ ልዩ የሕጻናት ማዕከል ከተዛወረች ጀምሮ ማን እንክብካቤ እያደረገላት እንደሆነ መረጃ የለንም። ልጃችን ላይ እየታየ ያለው ምሥጢዊነት ፍጹም እንግዳ ነው” ብላለች።
ዲያ የጀርመን ባለሥልጣናትን “በባህል ልዩነት እና ባለመግባባት ልጄን ነጥቀውኛል” ስትል ትከሳቸዋለች።
ጀርመንኛ ቋንቋ መናገር እንደማትችል የምትናገረው ዲያ፣ የተሰጣት አስተርጓሚ ሂንዲ ቋንቋ ቢናገርም የእሷ አፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነውን ጉጅራቲ እንደማያውቅ ተናግራለች። ቢቢሲ ለታዳጊዎች የደኅንነት ቢሮ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል።
የሕጻኗ ጉዳይ በሕንድ እና በጀርመን ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።
በበርካታ የሕንድ ከተሞች እንዲሁም በጀርመኖቹ ፍራንክፈርት እና ዳርምስታድት በህንድ ዲያስፖራዎች አማካኝነት የአደባባይ ተቃውሞ ተካሂዷል።
እንዲሁም በርካቶች ለወላጆቿ የድጋፍ ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛል።

ዲያ ከሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝታ ተወያይታለች። እንዲሁም በርካታ የሕንድ የፓርላማ አባላትን አነጋግራ በሕንድ ተቀማጭ ለሆኑት የጀርመን አምባሳደር ፊሊፕ አከርማን ሕጻኗን ወደ ሕንዱ እንዲመልሷት የሚጠይቅ ደብዳቤ እንዲልኩ አደርጋለች።
አንድ የምክር ቤት አባል የሕንድ መንግሥት ሕጻኗን ወደ አገሯ ለመመለስ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ሌላኛው ፖለቲከኛ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሚቀጥለው ወር ለቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ወደ ሕንድ ከሚመጡት የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ጋር የሕጻኗን ጉዳይ አንስተው በዋነኝነት እንዲወያዩበት ጠይቀዋል።
ዲያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ጣልቃ እንዲገቡ እየጠየቀች ትገኛለች።
“ብቸኛው ተስፋዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ናቸው። እሳቸው ጣልቃ ከገቡ ልጄ ትመለስልኛለች” ብላለች።
በሕጻኗ የተፈጠረው አለመግባባት ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2011 በኖርዌይ ነዋሪ የነበሩ ሕንዳውያን ልጆች በባለሥልጣናት መወሰድን አስታውሷል። ልጆቹ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር ወደ ሕንድ የተመለሱት።
በኖርዌይ የሕንዳውያኑን ወላጆች ጉዳይ ይዘው የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት የዚህችን ሕጻን ወላጆች በመርዳት ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሕግ ባለሙያ እና ተሟጋች ሱራኒያ አያየር፣ እንዲህ አይነት ጉዳዮች የተለመዱ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።
“እየታየ ያለ ጉልህ ችግር ነው። እያደረጉ ያሉት በራሳቸው ግምት ጥሩ መፍትሄ ነው የሚሉትን እርምጃ በመውሰድ ተጨማሪ ውይይቶችን ማስወገድ ነው” ይላሉ።
በድንበር ተሻጋሪ የቤተሰብ አለመግባባቶች ውስጥ የጀርመን የታዳጊዎች የደኅንነት ቢሮ ሚና በአውሮፓ ፓርላማ ተተችቷል።
ፓርላማው በ2018 (እአአ) ባወጣው ጠንከር ባለ ሪፖርት፣ ተቋሙ በስደተኞች ልጆች ላይ ኢ-ፍትሃዊ እና አድልዎን በመፈጸም እንዲሁም የወላጆችን እና የነጠቋቸውን ልጆች መብት እየጣሰ ነው ሲልም ከሶታል።
ፓርላማው በግንቦት ወር ባወጣው አዲስ ሪፖርት አቤቱታዎችን የሚቀበለው ኮሚቴው አሁንም በታዳጊዎች የደኅንነት ተቋሙ ላይ በርካታ ቅሬታዎች እንደሚደርሱት አስታውቋል።
ስደተኛ ወላጆች አሁንም ኢ-ፍትሃዊ እና አድልዎ በተቋሙ እየተፈጸመባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ሱራኒያ በእንደነዚህ ዓይነት አለመግባባቶች ላይ የተሻለ ብለው የሚያቀርቡት መፍትሔ መንግሥት እነዚህን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ ለመርዳት ማኅበራዊ ሠራተኞችን መመደብ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
በሕጻኗ ጉዳይ ላይ ሱራኒያ የሚያቀርቡት ብቸኛ መፍትሔ የሕንድ መንግሥትን ጣልቃ መግባት ነው።
“ሕጻኗ ምንም ስህተት አልሰራችም። ወደ ሕንድ ይመልሷት። የሕንድ ዜጋ ናት፤ እናም በዚህም አገር ቢሆን የመቆየት ሙሉ መብት አላት” ብለዋል።
የሕንድ መንግሥት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።
የሕንድ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦሪንዳም ባግቺ በቅርቡ በሕንድ ተቀማጭ የሆኑትን የጀርመን አምባሳደር ጠርተው የሕንድን ስጋቶች ለአገራቸው መንግሥት እንዲያደርሱ መንገራቸውን ገልጸዋል።
“በትንሹ የዚህች ሕጻን የባህል መብቶች እንዲሁም እንደ ሕንዳዊ ያሏት ሰብዓዊ መብቶቿ እየተጣሱ ነው ብለን እናምናለን። ሕጻኗን ወደ ሕንድ እንዲመልሷት ጠይቀናል። በዚህ ጉዳይ በጀርመን ላይ የምናደርገውን ጫና እንቀጥላለን” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
በዴልሂ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ቃለ አቀባይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ነገር ግን በጀርመን የሚገኙ የመንግሥት ምንጮች ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንደተያዘ እና ከእጃቸው ውጭ እንደሆነ ገልጸው፣ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ከሕንድ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን አክለዋል።
የሕንድ ባለሥልጣናት ሕጻኗ በማደጎ ልትቀመጥ የምትችልበትንአንድ ቤተሰብ ጉጅራት ውስጥ መለያታቸውንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ሕጻኗ ከወላጆቿ ጋር ልትሆን እንደምትገባ የሚከራከሩት በጡረታ የተገለሉት የመንግሥት የሕጻናት ሐኪም እና በመንግሥት የተቋቋመው የሕጻናት ደኅንነት ኮሚቴ የቀድሞ አባል ዶክተር ኪራን አጋርዋል ናቸው።
“ሕንድ ጠንከር ያሉ የሕጻናት ጥበቃ ሕጎች አሏት። እናም የጀርመን ፍርድ ቤት ወደ አገሯ ከመለሷት በሕንድ ውስጥ እንክብካቤ ሊደረግላት ይችላል” ብለዋል።
ቀናት እያለፉ በሄዱ ቁጥር የልጇን የጨቅላነት ጊዜ እያጣች ያለችው እናት አሁንም በከፍተኛ ጭንቅ ላይ ናት።
“የአፍ መፍቻ ቋንቋዋን ጉጅራቲ መማር አልቻለችም። ጀርመንኛ ብቻ ነው የምትናገረው። እንዴት ላናግራት እችላለሁ” ስትል እናት ትጠይቃለች።
በተጨማሪም ወላጆቿ ለማደጎ እና ለፍርድ ቤት ወጪዎች እንዲከፍሉ የታዘዙትን 9 ሚሊዮን ሩፒ ወይም 108 ሺህ ዶላር ለመክፈል እየታገሉ ይገኛሉ።
“በተለያዩ መንገዶች ገንዘብ በማሰባሰብ 5 ሚሊዮን ሩፒ ከፍለናል። እኛ ሃብታም አይደለንም፤ መካከለኛ ገቢ ያለን ቤተሰብ ነን። ሞራላችንን እና መንፈሳችንን ሰብረውታል። አሁን ደግሞ በገንዘብ ሊሰብሩን እየሞከሩ ነው” በማለትም እናት ተናግራለች።












