ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለሥራ የሚያቀኑ ሠራተኞች እየገጠማቸው ያለው ዘመናዊ ባርነት

 ዊልቸር እየገፋች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዩናይትድ ኪንግደም በጤና እንክብካቤው ዘርፍ ውስጥ ዘመናዊ ባርነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።

አገሪቱ በጤናው እና በእንክብካቤ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ የሠለጠኑ የውጭ አገራት ሠራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ ቪዛ እየሰጠች ባለበትም ወቅት ነው ይህ የተሰማው።

ከጥር ወር እስከ መጋቢት ባለውም 102 ሺህ የውጭ አገር ሠራተኞች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲመጡ ቪዛ ተሰጥቷቸዋል።

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 171 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

አንዳንድ ሠራተኞች ከሕጉ በተጻራሪ ከሁለት ፓውንድ በታች እንደተከፈላቸው እና በቀን ለሃያ ሰዓታት በመሥራት ለእንግልት እንዲሁም ለሰቆቃ መዳረጋቸውን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ዘመናዊ ባርነትም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩንም መረጃዎች ያሳያሉ።

ከጥር እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ 109 የጉልበት ብዝበዛ አጋጥሟቸዋል የተባሉ ሠራተኞች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም ቀደም ባለው ጊዜ ከነበረው በእጥፍ ጭማሪ አሳይቷል።

ሠራተኞችን ከመበዝበዝ ለመታደግ በሚል በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት የፀረ ባርነት የእርዳታ የስልክ ጥሪ መስመር የተዘረጋ ሲሆን፣ ይህንንም መረጃ ቢቢሲ ያገኘው ድጋፉን በበላይነት ከሚቆጣጠረው ‘አንሲን’ ከተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

መንግሥት የጤና እና የእንክብካቤ ዘርፉ “ቅድሚያ ሰጥቼ የምሰራበት ነው” ብሏል።

በመላው ዩናይትድ ኪንግደም ሠራተኞችን ከጉልበት ብዝበዛ ለመጠበቅ የተቋቋመው ‘ጋንግ ማስተር ኤንድ ሌበር አቢዩዝ’ የተባለው ተቋም በአሁኑ ወቅት 17 የጉልበት ብዝበዛዎችን እየመረመረ እንደሆነ እና ከ300 በላይ ጉዳዮች ላይም ጥብቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

አንሲን በበኩሉ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ እርዳታ ፈልገው የሚደውሉ ሠራተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስታውቋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ኅብረት መውጣቷን ተከትሎ በጤና እና በእንክብካቤው ዘርፍ የታዩ የሥራ ክፍተቶችን ለመሙላት ከውጭ አገራት ነርሶችን እና የጤና ባለሙያዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የጉልበት ብዝበዛ እና ዘመናዊ ባርነት ታይቷል ተብሏል።

የሠራተኛ አቅርቦት ሰንሰለቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የብዝበዛ ዕድሉም ሰፊ እንደሚሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገልጿል።

መንግሥት ዘመናዊ ባርነትን ለመከላከል ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ 17.8 ሚሊዮን ፓውንድ መውጣቱ ተገልጿል።

የዘመናዊ ባርነት ሰለባ የሆኑ ሠራተኞች በአካል ተገኝተው ታሪካቸውን ሲናገሩ መስማት ያልተለመደ ቢሆንም በሥራ ቪዛ ወደ እንግሊዝ የመጣች አንዲት ሴት ለቢቢሲ ታሪኳን ተናግራለች።

እረፍት እና እንቅልፍ በሌለው ሁኔታ በእንክብካቤ ሰጪነት እንድትሰራ የተገደደችው ይህች ግለሰብ፣ አድካሚ ጉዟዋንም ታስረዳለች።

የዘመናዊ ባርነት ሰለባ የሆነችው ቴሪ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁንም ቢሆን የቀድሞ አሰሪዎቿን የምትፈራውን ይህች ሠራተኛ ማንነቷን ለመጠበቅ ስንል ‘ቴሪ’ ብለን እንጠራታለን።

ከአፍሪካ እና ስሙን ከማንጠቅሰው ከትውልድ አገሯ በአንድ ኤጀንሲ ተመልምላ በዩናይትድ ኪንግደም የቤት ውስጥ እንክብካቤ እንድተሰጥ ነው የተቀጠረችው። ኤጀንሲው ቪዛ እና ትራንስፖርት እንደሚያመቻችላት አሳወቃት።

በአካልም ተገኝታ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፈተናም ወስዳለች፤ እንዲሁም የሥራ ልምድዋን የሚያሳይም ማስረጃ ማቅረብ ነበረባት።

ከዚህም በኋላ በእንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው የእንክብካቤ ሰጪ ኩባንያ በእንክብካቤ ሠራተኝነት እንደምትቀጠር ቃል ተገባላት።

ዓመታዊ ደመወዟም እስከ 29 ሺህ ፓውንድ እንደሆነም ተነገራት። በአስከፊ ትዳር ውስጥ ለነበረችው ቴሪ ሥራው ከሦስት ልጆቿ ጋር የምታመልጥበትን አጋጣሚ ሰጣት።

“በጣም የተለየ ስሜት ተሰማኝ። በሕይወቴ ምርጥ ከምላቸው ቀናት አንዱ ነበር” ትላለች።

ቴሪ እናቷን ልጆቿን እንዲንከባከቡ በሚል ወደ እንግሊዝ አመጣቻቸው። ቴሪ በእንክብካቤ ሰጪ ኩባንያው በኩል የምትሠራባቸው ቦታዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ መኖሪያ ተሰጣት። ልጆቹም ከአያታቸው ጋር በኪራይ ቤት መኖር ጀመሩ።

ቴሪ የሥራ ሁኔታው አስጨናቂ ብቻ ሳይሆን ምሬት ፈጠረባት።

በቀን እስከ 20 ሰዓታት እና በሳምንት ሰባት ቀናት ለመሥራት ተገደደች። ከአንድ ደንበኛ ወደ ሌላ ደንበኛ ለመሄድ ቃል የተገባላት መኪና ባለመሳካቱም በእግሯ መሄድ ነበረባት። ከሁለት ወራት በኋላ ደመወዟን ከድርጅቱ ስትቀበል በሰዓት ከሁለት ፓውንድ በታች ተደምሮ ተሰጣት።

ይህም በዩናይትድ ኪንግደም የሠራተኞችን መብት የሚጥስ ነው። በሕጉ መሠረት ከ23 ዓመት በላይ የሆኑ የእንክብካቤ ሠራተኞች በሰዓት ከ10.42 በላይ ፓውንድ እንዲከፈላቸው ያስገድዳል።

በተጨማሪም በቀጠሮ ለሚያሳልፉት ጊዜ እንዲሁም ከሥራ ወደ ሌላ ሥራ የሚያመሩበት የጉዞ ወቅትም ከክፍያው ሂሳቡ ውስጥ መካተት እንዳለበት ተደንግጓል።

ቴሪ ለቀጠራት ድርጅት ያላትን ቅሬታ ብታቀርብም የሥራ ቪዛዋን እንደሚሰርዘው አስፈራራት። ሌሎች አብረዋት የሚሠሩ ሠራተኞችም የድርጅቱ ባለቤት በትውልድ አገሯ ካሉ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳለው በመንገር አስጠነቀቋት።

“ከመጣሁበት አገር አንጻር ይህንን መስማት አደገኛ ነው። ማንም እንዲህ አይነት ሰውን ተቃውሞም ሆነ ከሶ መቆም አይፈልግም” ስትልም ለቢቢሲ ተናግራለች።

በሚከፈላት ዝቅተኛ ደመወዝ ምክንያትም ለእናቷ እና ለልጆቿ የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሏ የነበሩበትን ቤት ለቀው ለመውጣት ተገደዱ።

እናቷ እና ልጆቿ ጎዳና ላይ ባደሩበትም ዕለት ቴሪ በምሽት ፈረቃ ሥራ ላይ ነበረች።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከተመለከቷቸው በኋላም ቴሪን በተመለከተ ለማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም ሪፖርት አደረጉ።

የሥራ ሁኔታዋን ለማየት ፈረቃዋን ሲያዩም የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ደነገጡ። ያለምንም እረፍት እና እንቅልፍ ለጉልበት ብዝበዛ መጋለጧንም በማየት “ይሄ እብደት ነው” ነበር ያሉት።

የዘመናዊ ባርነት ሰለባ እንደሆነችም በመፈረጅ በዚህ ወንጀል ተጠቂ የሆኑትን ለመለየት እና ለመደገፍ በዩናይትድ ኪንግደም የተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ እና የክትትል ሥርዓት ውስጥ እንድትካተት ተደረገች።

ከቤተሰቧ ጋር በማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷታል። እንዲሁም ‘ኮዝ ዌይ’ የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅትም እያገዛቸው ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ቴሪ በዩናይትድ ኪንግደም የጥገኝነት ጥያቄ አቅርባለች። ጉዳይዋ እልባት እስኪያገኝ ድረስም ሥራ እንድትሰራ አይፈቀድላትም።

የስደተኞችን ጉዳይ የሚከተታለው ተቋምም የዘመናዊ ባርነት ሰለባ መሆኗን ለማረጋገጥ በቂ የሆኑ ማስረጃዎች እንዳሉም ነግሯታል።

ቴሪ ትሠራበት የነበረው ድርጅት በመንግሥት ምርመራ ተከፍቶበታል። ምርመራውንም የሠለጠኑ ሠራተኞችን ቪዛን የሚያስፈጽመው መንግሥታዊ ተቋም እየተከታተለው መሆኑን የ‘ጋንግ ማስተር ኤንድ ሌበር አቢዩዝ’ ኃላፊ ኢያን ዋተርፊልድ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የእንክብካቤ ዘርፉ ከዚህ ቀደም ይህን ያህል ትኩረት የሚደረግበት ባይሆንም ባለፉት 18 ወራት ውስጥ መንግሥት በዋነኝነት ቅድሚያ የሚሰጠው ሆኗል። ዘመናዊ ባርነት የግንባታ እና የመኪና ጽዳትን ጨምሮ በሌሎች የሥራ ዘርፎችም ሰርጎ እየገባ እንደሆነ ነው የሚያስረዱት።

የዕድሜ ባለጸጋን ሰው እጅ የያዘች የእንክብካቤ ሰጭ ሰራተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ዓመት የባርነት ሰለባዎች ናቸው ተብለው ወደ ብሔራዊ የድጋፍ እና የክትትል ሥርዓት የተላኩት ሰዎች ቁጥር 17 ሺህ ያህል ሲሆን፣ ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው።

የብሔራዊ ፖሊስ አዛዥ ምክር ቤት ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ ለመረዳት እና ለመቅረፍ ራሱን የቻለ ቡድን መቋቋሙን አስታውቋል።

በአሁኑ ጊዜ በመላው እንግሊዝ እና ዌልስ ከ3500 በላይ ምርመራ ተከፍቷል። ነገር ግን ክሶችን መመሥረት ፈታኝ እንደሆነ ተነግሯል።

ባለፈው ዓመት የእንግሊዝ እና የዌልስ ፖሊስ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ የባርነት ሰላባ ጉዳዮችን መዝግበዋል። ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ ተዘግተዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ወንጀለኞችን ተከታትሎ መያዝ ባለመቻሉ ሲሆን፣ ከመካከላቸው ወደ ክስ ያመሩት ከሁለት በመቶ ያነሱ ናቸው።

“የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች ለተለያዩ ችግሮች እጅግ በጣም ተጋላጭ ናቸው” ሲሉም የገለልተኛው የፀረ ባርነት የቀድሞ ኮሚሽነር ሳራ ቶርተን ያስረዳሉ።

“በሕገወጥ መንገድ ያዘዋወሯቸው ወይም በባርነት የያዟቸውን ሰዎች በጣም ነው የሚፈሯቸው። ወደ ፖሊስ፣ የመንግሥት ቢሮም ሆነ በጎ አድራጎት ድርጅት ቢሄዱ እነሱን ስለማይደግፏቸው ምንም ፋይደ እንደሌለው ይነግሯቸዋል” ይላሉ ሳራ ቶርተን።

ባለፈው ሳምንት ዩናይትድ ኪንግደም ያጸደቀችው ሕገወጥ ስደተኞች ሕግ ተጋላጭ የሆኑትን ተጎጂዎችን መደገፍን የበለጠ ከባድ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

አዲሱ ሕግ በሕገወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገቡ ሁሉንም ሰዎች ማሰር እና ከአገር ማስወጣት ይፈቅዳል።

ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ይህንን ሕግ በመጥቀስ ተጠቂዎችን ወደ ፖሊስ እንዳይሄዱ ለማሳመን እንደሚጠቀሙበትም ያምናሉ። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የፀረ ባርነት ኮሚሽን አለመኖሩ “በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ቴሪ በሥራዋ የደረሰባትን እንግልት ስታስበው ሰቆቃው አልረሳ ይላታል።

“አንዳንዴ በሥራው ወቅት የነበረው ነገር አሁንም ያቃዠኛል” ብላለች።