በናይጄሪያ ከ50 በላይ ሕጻናት በታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

ታጣቂ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ከሦስት ትምህርት ቤቶች ከ50 በላይ ሕጻናት በታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ።

መምህራን እና ወላጆች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ አብዛኞቹ ታግተው የተወሰዱት ልጆች ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ነው።

ሙሳ ቦንቶ በተባለው ግዛት ያለፈው አርብ ጥቃቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ የፀጥታ ኃይሎች እንዳይተኩሱባቸው ሕጻናትን እንደ መከላከያ ሲጠቀሙባቸው ነበር።

እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። የናይጄሪያ መንግሥት ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ባይሰጥም የግዛቱ የምክር ቤት አባል አሊ ንዱሜ 42 ሕጻናት ከትምህርት ቤቶች መታገታቸውን ገልጸዋል።

ሕጻናቱ የታገቱት ገቨርንመንት ደይ ከተባለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሙሳ ሴንትራል ከተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ስቴት ዩኒቨርሳል ቤዚክ ኤጁኬሽን ከተባለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።

እገታው የተፈጸመው በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

በናይጄሪያ የጅምላ እገታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መጥተዋል። የቦርኖ ግዛት ነዋሪዎች ለረዥም ጊዜ በፀጥታ ማጣት መፈተናቸውም ተገልጿል። ጥቃቶችን በመሸሽ ብዙዎች ከአካባቢው ወጥተዋል።

ልጆቻቸው የታገቱባቸው ቤተሰቦች አንዳች ዜና እስከሚሰሙ ድረስ ከመጠባበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የስድስት ዓመት ልጁ የታገተችበት አባት እንዳለው ባለቤቱ እስካሁን ድረስ ከድንጋጤ አልወጣችም።

የሙሳ ሴንትራል ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አብዱ ዱናማ እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።

ወደ 34 የሚጠጉ የመዋለ ሕጻናት ተማሪዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።

የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው ሲወጡ ታጣቂዎቹ በሞተር ሳይክል መድረሳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ልጁ የታገተችበት ቡካር ቡባ "የፀጥታ ኃይሎች በሄዱ በ30 ደቂቃ ውስጥ ነው ታጣቂዎቹ የመጡት" ብሏል።

ታጣቂዎቹ አከታትለው ጥይት እየተኮሱ ስለነበር ነዋሪዎች ለመደበቅ ተገድደዋል። ልጆቻቸው ታግተው በሞተር ሲወሰዱ የተመለከቱ ወላጆችም እርዳታ ቢስ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ በመደበቅ ከእገታ አምልጠዋል።