'ደም በደም ሆኜ ነበር'- ከናይጄሪያ ቤተ ክርስቲያን እገታ ያመለጡት ምስክርነት

ሳራ ፒተር ከአጋቾች ለማምለጥ ችለዋል
የምስሉ መግለጫ, ሳራ ፒተር ከአጋቾች ለማምለጥ ችለዋል

ሳራ ፒተር የሚፈሳቸውን ደም ለማስቆም ጭንቅላታቸው ላይ ትልቅ ፕላስተር ተለጥፏል።

ሳራ (ስማቸው ተቀይሯል) እሑድ ጠዋት በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኝ መንደር ውስጥ ከቤተክርስቲያን ታግተው ከተወሰዱ ምዕመናን አንዷ ናቸው።

የ60 ዓመቷ አዛውንት ጉዞውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ በጠመንጃ ሰደፍ ጭንቅላታቸው ተመቷል።

"ደም በደም ሆኜ ነበር" ሲሉ በጣታቸው ቁስሉ ያለበትን ቦታ እየጠቆሙ አሳዩ።

"ተሰቃየሁ" ሲሉ አክለዋል። ከሦስት ቀናት በፊት በተከሰተው ነገር አሁንም እንደደነገጡ ነው።

"መራመድ እንደማልችል ብነግራቸውም እየጎተቱኝ ቀጠሉ። ከዚያም እነሱ ርቀው እስኪሄዱ ድረስ አንድ ቦታ ተደበቅኩ። በጣም ስለደከመኝ በእንብርክክ ነበር ወደ መንደሩ የተመለስኩት።"

ከዋና ከተማዋ አቡጃ በስተሰሜን 135 ኪሎ ሜትር ላይ ባለው ኩርሚን ዋሊ ከሚገኘው የኪሩቢም እና የሴራፊም ንቅናቄ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተወስደዋል።

ሳራን ጨምሮ 11 ሰዎች ማምለጥ ቢችሉም፣ ከ160 በላይ ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም ሲል የናይጄሪያ የክርስቲያን ማኅበር ገልጿል።

የቀሩት የመንደሩ ነዋሪዎች በከባድ ሁኔታ ውስጥ ከመግባት ባለፈ ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይከሰቱ ፍርሃት ውስጥ ናቸው።

ባለሥልጣናት ስለጠፉት ሰዎች ምንም ዓይነት ቁጥራዊ መረጃ አላወጡም።

ሳራ በጥቃቱ ምክንያት ተረብሸዋል
የምስሉ መግለጫ, ሳራ በጥቃቱ ምክንያት ተረብሸዋል

ኩርሚን ዋሊ በካዱና ግዛት ሪጃና ደን አቅራቢያ ይገኛል። ቦታው "ሽፍታ" በመባል የሚታወቁት የታጠቁ ቡድኖች መደበቂያ ሥፍራ ነው።

እሑድ ዕለት ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም። ጥቃቱ በናይጄሪያ ውስጥ ትልቅ የጸጥታ ቀውስ አካል እየሆነ የመጣው ለገንዘብ ሲባል የሚደረግ እገታ አካል ነው።

በናይጄሪያ ውስጥ ለአጋቾች ገንዘብ መክፈል ሕገ-ወጥ ቢሆንም የታገቱትን ለማስለቀቅ ገንዘብ ተከፍሏል ተብሎ ብዙ ጊዜ ይጠረጠራል። በአሁኑ ክስተት የገንዘብ ጥያቄ ስለመቅረቡ አልተዘገበም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ክርስቲያኖች በከፍተኛ ቁጥር ዒላማ ተደርገው እየተገደሉ ነው ብለው ከገለጹ በኋላ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረቱ እየጨመረ መጥቷል።

ከሳምንታት በፊት የአሜሪካ ጦር በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኙ ተጠርጣሪ የእስልምና ታጣቂዎች ካምፖች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽሟል።

የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ተነጥለው እየተወሰዱ እንዳልሆነ ከመግለጽ ባለፈ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ጭምር ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኩርሚን ዋሊ የውጥረት እና የቁጣ ድባብ ተፈጥሯል። የመንደሩ ኃላፊ እንዳሉት ሰዎች በፍርሃት መኖር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ባለሥልጣናት ጥበቃውን እንዲያጠናክሩ ሲያሳስቡ ቆይተዋል። እሑድ ዕለት ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ መረጃን ለማፈን እየሞከሩ ነው ሲሉም ከሰዋቸዋል።

በየቦታው የወዳደቁት የቤተክርስቲያኗ ወንበሮች
የምስሉ መግለጫ, በየቦታው የወዳደቁት የቤተክርስቲያኗ ወንበሮች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዓይን ምስክሮች ስለጉዳዩ ደጋግመው ቢናገሩም ባለሥልጣናት መጀመሪያ ላይ ምንም ነገር እንዳልተከሰተ ሲክዱ ቆይተው ማክሰኞ ምሽት ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

"ምንም ዓይነት መረጃ እንዳናካፍል፣ ሊያስፈራሩን ይፈልጋሉ። ነገር ግን ታሪካችንን መናገር አለብን" ብለዋል።

"አንዳንድ ጋዜጠኞች ወደ ከተማው እንዳይመጡም እያደረጉ ነው" ሲል በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት ተናግሯል።

ባለሥልጣናቱ ዜናው እንዳይወጣ ለምን እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም። የካዱና ግዛት ገዥ ኡባ ሳኒ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ባለስልጣናት ምንም ዓይነት መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ዝርዝር ጉዳዩን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።

ምላሻቸው የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ እና አንድ የክልሉ ባለሥልጣን መጀመሪያ ላይ ጥቃት እንዳልተፈጸመ ለምን እንደካዱ ግን አያብራራም። ሪፖርቶቹን "ሁከት ለመፍጠር የሚፈልጉ የግጭት ጠንሳⶄች እየተዘዋወሩት ያለ ተራ ውሸት" ሲሉ ገልጸዋል።

አንድ ፖለቲከኛ እና የደኅንነት ሠራተኞች ወደ መንደሩ ለመግባት የሚደረገውን ሙከራ በማደናቀፋቸው ቢቢሲ ወደ ኩርሚን ዋሊ ለመድረስ ችግሮች ገጥመውታል።

ቢቢሲ በሥፍራው ከደረሰ በኋላ ግን የኪሩቢም እና የሴራፊም ንቅናቄ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ተመልክቷል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ አካባቢው ባለመነካቱ የፕላስቲክ ወንበሮች በየቦታው ተበታትነዋል፤ የጸሎት መጻሕፍት ወለሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተሰባብረዋል።

ክሪስቶፈር ዮሃና የሁለት ዓመት ሴት ልጁን በድንጋጤ እየተመለከታት ነው። ከልጁ ጋር ከታጣቂዎቹ ማምለጥ እንደቻለ ተናግሯል።

"በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሆነን ነው ጩኸት የሰማነው። ወጥተን ለመሮጥ ስንሞክር፣ ታጣቂዎች መንደሩን ከበውት እንደነበር ተመለከትን።"

እሱ ባለመያዙ ቢሳካለትም ሁለቱ ሚስቶቹ እና ሌሎች ልጆቹ ዕድለኞች ስላልነበሩ በጣም አዝኗል።

"ቤተሰቦቼ ከእኔ ጋር ካልሆኑ ሕይወቴ ዋጋ ቢስ እና ደስታ የለሽ ነው" ብሏል።

አስተዳደሪው ሳኒ ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሦስት ቀናት በኋላ በኩርሚን ዋሊ የተገኙ ሲሆን፤ በአካባቢው ወታደራዊ ጣቢያ፣ ሆስፒታል እና መንገድ ለማቋቋም ቃል ገብተዋል። እንዲሁም ለተጎዱ ነዋሪዎች ሕክምናን ጨምሮ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

"ማረስ ስላለባቸው እነሱን ማዘዋወር አንችልም… ነገር ግን ወደፊት እነሱን ለመጠበቅ በዚያ መንደር እና በሪጃና ደን መካከል ባለው አካባቢ ወታደራዊ ጣቢያ ሊኖረን ይገባል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሁንም በእገታ ውስጥ ያሉትን ለማስለቀቅ ከደኅንነት ተቋማት ጋር ለመሥራት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ከነዋሪዎቹ ጋር በተገናኘንበት ወቅት አብረናቸው እንደሆንን አረጋግጬላቸዋለሁ… በጭራሽ አናሳፍራቸውም።"

የኩርሚን ዋሊ ነዋሪዎች የቤተሰባቸው አባላት መመለሳቸው በጉጉት እየተጠባበቁ ባለበት ወቅት አስተዳዳሪውም ቃሉን እንደሚጠብቅ ተስፋ ያደርጋሉ።