ትራምፕ በናይጄሪያ አለ ያሉት የአይኤስ ቡድን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ለምን ወሰኑ?

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ, የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ጦራቸው በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኘው የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን ላይ "ከባድ ጥቃት" ፈጽሟል ብለዋል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አይኤስን "አጭበርባሪ አሸባሪ" ሲሉ ገልጸውታል።

ቡድኑ በተለይ "አብዛኛው ንጹኅን ክርስቲያኖችን በጭካኔ እያጠቃ እና እየገደለ ነው" ሲሉ ወንጅለውታል።

ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ጦር "በርካታ ዒላማዎች ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን ፈጽሟል" ሲሉ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ሳይሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ጦሩ ናይጄሪያ ውስጥ የትኞቹን ዒላማዎች እንደመታ ወይም መቼ ጥቃቱን እንደፈጸመ አይታወቅም።

ፕሬዝዳንቱ በኅዳር ወር ጦራቸው በናይጄሪያ ውስጥ የእስልምና ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት እንዲዘጋጅ አዝዘው ነበር።

ትራምፕ ሐሙስ ምሽት ባጋሩት ጽሑፍ "በእኔ አመራር ስር አገራችን የአክራሪ እስልምና ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ አትፈቅድም" ብለዋል።

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ማይታማ ቱጋር ለቢቢሲ "በአሸባሪዎች" ላይ የተደረገው የጋራ ዘመቻ መሆኑን ተናግረው ጥቃቱ "ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም" ብለዋል።

ቱጋር ተጨማሪ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ተናግረው ይህም "የሁለቱም አገራት መሪዎች በሚወስኑት ውሳኔ" ላይ የተመሠረተ ይሆናል ብለዋል።

ባለፈው ኅዳር ወር ትራምፕ በናይጄሪያ ክርስቲያኖች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይፈጸማል የሚለውን የወግ አጥባቂዎች አስተያየት ተከትሎ በአገሪቱ የሚፈጸም የክርስቲያኖችን ግድያ አውግዘዋል።

ትራምፕ በናይጄሪያ ላይ ለምን እንዳተኮሩ እና በኢስላሚክ ስቴት ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ምክንያት የሆናቸውን ነገር እንመለከታለን።

የተወሰነ ክፍላቸው የተጎዳ ተያይዘው የተሠሩ ቤቶችን ዛገ ጣሪያ የሚሰሳይ የአየር ላይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, BBC grab

የምስሉ መግለጫ, በናይጄሪያዋ የአሜሪካ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በክዋራ ግዛት

በናይጄሪያ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካ በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ናይጄሪያን በክርስቲያን ሕዝቦቿ ላይ "በተደቀነው የኅልውና ስጋት" የተነሳ "ልዩ ትኩረት የሚሰጣት አገር" ስትል ፈርጃታለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ከባድ የሃይማኖት ነፃነትን የሚጥሱ" አገራትን የሚቀጣ ማዕቀብ የሚጥልበት ምደባ ነው።

ትራምፕ በበኩላቸው ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ በናይጄሪያ "በሺዎች የሚቆጠሩ" ክርስቲያኖች እየተገደሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ለወራት በዋሽንግተን የሚገኙ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች እስላማዊ ታጣቂዎች በናይጄሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጥቃት እየፈጸሙ ነው በማለት ይናገሩ ነበር።

በመስከረም ወር ዝነኛው የቴሌቪዥን አቅራቢ እና ኮሜዲያን ቢል ማሄር በናይጄሪያ እየሆነ ያለውን "የዘር ማጥፋት" ሲል ገልጾታል።

ቦኮ ሃራም የተሰኘውን እስላማዊ ታጣቂ ቡድን በመጥቀስ ከአውሮፓውያኑ "2009 ጀምሮ 100 ሺህ ክርስቲያኖችን ገድለዋል እንዲሁም 18 ሺህ ቤተክርስቲያኖችን አቃጥለዋል" ብሏል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም ተመሳሳይ ቁጥር ሲዘዋወር ነበር።

ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባል ቴድ ክሩዝ በበኩላቸው በናይጄሪያ ይፈጸማል ያሉትን ግድያ ሲያወግዙ ተደምጠዋል።

ቴድ ክሩዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ከ2009 ጀምሮ ከ 50 ሺህ በላይ ክርስቲያኖች ተገድለዋል። ከ18 ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናት እና 2ሺህ የክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ወድመዋል" ሲሉ ጽፈዋል።

የቴድ ክሩዝ ቢሮ በኢሜል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ይፈጸማል ያሉትን ግድያ "የዘር ማጥፋት" ከማለት ተቆጥበው "ጭቆና" ብቻ ማለት መርጠዋል።

ነገር ግን ክሩዝ የናይጄሪያ ባለሥልጣናትን "በእስላማዊ ጂሃዲስቶች የሚፈጸምን የጅምላ ግድያ ቸል ይላሉ እንዲሁም ያመቻቻሉ" ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ትራምፕ ይህንን የክሩዝን ሃሳብ በማስተጋባት ናይጄሪያ "ክብሯን ያጣች አገር" እንዲሁም መንግሥቷ "ክርስቲያኖች እንዲገደሉ ይፈቅዳል" ሲል ከስሰዋል።

ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ የፖሊስ መርማሪዎች የፍንዳታ ናሙና ሲሰበስቡ

የፎቶው ባለመብት, Usman Binji

የምስሉ መግለጫ, ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ የፖሊስ መርማሪዎች የፍንዳታ ናሙና ሲሰበስቡ

የናይጄሪያ መንግሥት አቋም

የናይጄሪያ መንግሥት የቀረበበትን ውንጀላ "ከእውነታው ጋር የተጣረሰ" በማለት ለማስተባበል ሳምንት ፈጅቶበታል።

የናይጄሪያ መንግሥት ከፍተኛ ሞት ያስከተሉ ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ማስተባበያ አልሰጠም። ነገር ግን የአገሪቱ ባለሥልጣናት "የሽብርተኞች ጥቃት ገዳይ የሆነው ርዕዮተ ዓለማቸውን የማይቀበሉ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና ሌላ እምነት የሚከተሉ ላይ ይፈጸማል" ብለዋል።

በናይጄሪያ የሚፈጸሙ ፖለቲካዊ ጥቃቶችን የሚከታተሉ ቡድኖች እንዲሁ በናይጄሪያ የተገደሉ ክርስቲያኖች ቁጥር ከሚባለው በጣም ያነሰ ነው በማለት በእስላማዊ ጂሃዲስት ቡድኖች የበለጠ ጥቃት የሚደርስባቸው ሙስሊሞች ናቸው ባይ ናቸው።

ናይጄሪያ በጂሃዲስቶች የሚፈጸም ጥቃቶች ብቻ ሳይሆን በርካታ የደኅንነት እና የፀጥታ ስጋቶች ያለባት አገር ናት።

የአገሪቱ መንግሥትም ጂሃዲስቶችን ለመዋጋት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ይናገራል። በአቡጃ የሚገኘው የአገሪቱ መንግሥት ጂሃዲስቶችን በመዋጋት ረገድ ከአሜሪካ ጋር ተመሳሳይ አቋም ያለው መሆኑን ለማሳየት እና በጋራ ለመዋጋት ያለውን ፍላጎት ሲገልጽ ተስተውሏል።

ናይጄሪያ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከጂሃዲስቶች ጥቃት በተጨማሪ የተለያዩ የደኅንነት ስጋቶችን ያለባት አገር ነች።

እነዚህ የደኅንነት ስጋቶች ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳላቸው መሳት አይገባም ስትል ታስረዳለች።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት የጂሃዲስት ቡድኖችን እና አመፀኛ የወንጀል ቡድኖችን ለመቆጣጠር አለመቻላቸው ግን ገሃድ የወጣ ነው። ለበርካታ ሳምንታት አዳዲስ ጥቃቶች እና እገታዎች ሲሰሙ ነበር።

ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ የሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሃራም ከአስርት ዓመታት በፊት 276 የቺቦክ ልጃገረዶችን ያገተ ቡድን ነው።

ነገር ግን የቡድኑ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ሙስሊም የሆኑ ማኅበረሰቦች በሚኖሩበት በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ የተገደበ ነው።

ከዚህ ቡድን በተጨማሪ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚንቀሳቀስ ኢስላሚክ ስቴት ዌስት አፍሪካ ፕሮቪንስ የተሰኘ ሌላ ታጣቂ ቡድን መጥቷል።

በካቶሊክ ጳጳስ ሞት ከፎቷቸው ፊት ለፊት የሐዘን መግለጫ ላይ የምትጽፍ ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የናይጄሪያ 220 ሚሊዮን ሕዝብ ገሚሱ የእስልምና እና ቀሪው ደግሞ ክርስትና እምነት ተከታይ ነው። አብዛኞቹ ሙስሊሞች የሚኖሩት ጥቃት በሚፈጸምበት የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ነው

ቁጥሮች ምን ይነግሩናል?

በኅዳር ወር ትራምፕ 3,100 ክርስትያኖች በእስላማዊ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ይህንን ቁጥር የወሰዱት ከጥቅምት 2023 ጀምሮ የደረሱ ግድያዎች በሚል ኦፕንዶርስ ካወጣው ሪፖርት መሆኑን ዋይት ሐውስ ተናግሯል።

ኦፕንዶርስ ዓለም አቀፍ የክርስቲያን ድርጅት ሲሆን፣ በመላው ዓለም በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ይከታተላል።

በሪፖርቱ ላይ በ12 ወራት ውስጥ ብቻ 3,100 ክርስቲያኖች ሲገደሉ 2,320 ሙስሊሞች መሞታቸው ተጠቅሷል።

ኦፕንዶርስ ጥቃት ፈጻሚዎች በሚል ከዘረዘራቸው መካከል የፉላኒ የሽብር ቡድን ይገኝበታል።

ይህ ቡድን በናይጄሪያ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸሙ አንድ ሦስተኛ ግድያዎች ተጠያቂ ነው ሲል ይወነጅለዋል።

በኦፕንዶርስ ተባባሪ ተመራማሪ የሆነው ፍራንስ ቨርማን "እያየን ያለነው ክርስቲያኖች አሁንም ጥቃት እንደሚደርስባቸው ነው፤ ነገር ግን በፉላኒ አማፂያን በርካታ ሙስሊሞችም ጥቃት እየደረሰባቸው ነው" ብለዋል።

በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ በርካታ ሙስሊሞች እና መስኪዶች ላይ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ ተንታኞች ይናገራሉ።

ኤስቢኤም ኢንተለጀንስ የተባለ አማካሪ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ማክሃሪ "ይህ የተስፋፋው የደኅንነት ማጣት አካል ነው" ብለዋል።

"ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰው ይህ ጥቃት ሃይማኖታዊ መልክ ያልተሰጠው ግድያውን የሚፈጽሙት ራሳቸው ሙስሊሞች በመሆናቸው ነው" ሲሉ አክለዋል።

የእስላማዊ ታጣቃ ቡድኖች ዒላማ ከሚያደርጓቸው መካከል ሙስሊሞችም ይገኙባቸዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስላማዊ ታጣቃ ቡድኖች ዒላማ ከሚያደርጓቸው መካከል ሙስሊሞችም ይገኙባቸዋል

አሜሪካ ለክርስቲያኖች ሞት የጠቀሰቻቸው ቁጥሮች አስደንጋጭ ናቸው። ነገር ግን ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።

ሴናተር ክሩዝ በመስከረም ወር በአንድ ፖድካስት ላይ ቀርበው የጠቀሱትን ቁጥር የወሰዱት በ2023 ኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ፎር ሲቪል ሊበርቲስ ኤንድ ሩል ኦፍ ሎው የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያወጣውን መረጃ ነው።

የቴድ ክሩዝ ቢሮ እነዚህን ቁጥሮች ከየት እንዳገኘ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ኢንተር ሶሳይቲ ያሳተማቸውን ሪፖርቶች ማስፈንጠሪያዎች ልኳል።

ማሄር ቢቢሲ የጠቀሳቸውን ቁጥሮች ያገኘበትን በሚመለከት ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል። ነገር ግን ቁጥሮቹ ክሩዝ ከጠቀሷቸው መረጃዎች ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው በኢንተርሶሳይቲ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ መገመት ይቻላል።

አሜሪካ በናይጄሪያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ በመቅረጽ ረገድ የኢንተርሶሳይቲ ሪፖርት ያለው ሚና ግለጽ አይደለም።

ኢንተር ሶሳይቲ የተሰኘው ይህ ድርጅት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆኑን ያህል የግልፅነት ችግርም እንዳለበት ከዚህ ቀደም ያወጣቸውን ሪፖርቶች የተመለከቱ ሰዎች ይገልጻሉ።

በነሐሴ ወር ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ባሉት 16 ዓመታት ብቻ በጂሃዲስቶች ጥቃት ከ100 ሺህ በላይ ክርስቲያኖች ተገድለዋል ይላል።

በእነዚህ ዓመታት 60 ሺህ "ለዘብተኛ ሙስሊሞች" መገደላቸውንም ያትታል።

ኢንተርሶሳይቲ የመረጃ ምንጮቹን ስለማያጋራ ቁጥሮቹን በገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ሌሎች መላምቶች

ኢንተርሶሳይቲ ባለፈው ዓመት ከጥር ወር እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ብቻ 7,000 ክርስቲያኖች መገደላቸውን ሪፖርት አድርጓል።

ይህ ቁጥርም ራይሊ ኤም ሙር የተሰኙ የኮንግረስ አባልም አስተጋብተውታል።

ድርጅቱ ለዚህ ሪፖርቱ 70 የሚዲያ ዘገባዎችን በመረጃነት መጠቀሙን ቢናገርም በግማሽ ያህል የሚዲያ ሪፖርቶች ላይ ግን የተጠቂዎቹ ሃይማኖት አልተጠቀሰም።

ለምሳሌ ኢንተርሶሳይቲ አልጀዚራ ቦኮሃራም በርካታ ክርስቲያን ገበሬዎችን ማገቱን መዘገቡን ቢገልጽም በአልጀዚራ ሪፖርት ላይ ግን የተጠቂዎቹ ሃይማኖት አልተጠቀሰም።

"ቦኮ ሃራም በቦርኖ ግዛት በዳምቦአ ክልል ከ40 የማይበልጡ በአብዛኞቹ ክርስቲያን የሆኑ ገበሬዎችን አግቷል" ስለዚህ የአልጀዚራ ዘገባ ታጋቾቹ "በዋናነት ክርስቲያን" መሆናቸውን አይገልጽም።

ኢንተርሶሳይቲ ለቢቢሲ እንደገለጸው የተጠቂዎቹን ማንነት ለመለየት የራሱን ትንተና እንደሚጠቀም ቢናገርም ስለ አካባቢው ማኅበረሰብ ያለውን ዕውቀት እና "የክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን" ስለመጠቀሙ ያለው ነገር የለም።

በእነዚህ ኢንተርሶሳይቲ የተጠቀሱ ዘገባዎች ላይ ያሉ ቁጥሮች ሲደመሩ አጠቃላይ ቁጥሩ እንደሚባለው 7ሺህ አይመጣም።

ቢቢሲ በኢንተርሶሳይቲ የተጠቀሱትን 70 የሚዲያ ሪፖርቶች ሲመለከት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,000 ብቻ መሆኑን መረዳት ችሏል።

ይህም በ2025 ተገደሉ ከተባሉት በግማሽ ያህል የቀነሰ ሲሆን፣ የተወሰኑ ጥቃቶችም በተደጋጋሚ ተቆጥረው ተገኝተዋል።

ኢንተርሶሳይቲ ይህንን ሲያስተባብል በእገታ ላይ ሳሉ የሞቱ ሰዎችን ከግምት አንደሚያስገባ ገልፆ የዐይን ምስክሮች እማኝነትም እንደሚካትት ገልጿል።

የፉላኒ አርብቶ አደሮች ከከብቶቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፉላኒ አርብቶ አደሮች የሚሳተፉበት ግጭት መነሻው በድንበር መገፋፋት እና የግጦሽ መሬት የተነሳ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ

እስላማዊ ታጣቂዎች

ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት እና የሚገድሉት ቦኮ ሃራም እና የፉላኒ አርብቶ አደሮች መሆናቸውን ይጠቀሳል።

ነገር ግን አብዛኞቹ ሙስሊም የሆኑትን የፉላኒ አርብቶ አደሮች እንደ "ጂሃዲስት" መግለጽ በናይጄሪያ ውስጥ ውዝግብ ያስነሳል።

በጉዳዩ ላይ ጥናት እና ምርምር የሠሩ ባለሙያዎች በአብዛኛው"ጂሃዲስቶች" ተብለው ከተጠቀሱት የፉላኒ አርብቶ አደሮች ጋር የሚኖር ግጭት መነሻው የግጦሽ መሬት እና የውሃ እጥረት እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም ይላሉ።

ምንም እንኳ አርብቶ አደሮቹ ሙስሊሞች ቢሆኑም በርካታ ተመራማሪዎች የሚኖረውን ግጭት ሃይማኖታዊ ነው በሚለው አይስማሙም።

የፉላኒ አርብቶ አደሮች በናይጄሪያ ከሙስሊሙም እንዲሁም ከክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ጋር ይጋጫሉ።

ባለሙያዎች ከፉላኒ አርብቶ አደሮች ጋር የሚኖር ግጭት ከድንበር እና ከግጦሽ መሬት ጋር የተያያዘ መሆኑን ይናገራሉ።

ኤስቢኤም ኢንተለጀንስ የተባለ አማካሪ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ማክሃሪ ግጭቶቹ በአብዛኛው ጊዜ መነሻቸው የብሔር ውጥረት እና የግጦሽ መሬት ይገባኛል ነው ብለዋል።

"በባሕሪው የብሔር መልክ አለው፤ መሬት መውሰድ ይፈልጋሉ፤ ግዛታቸውን ማስፋፋት እፈልጋሉ። በዚህም የተነሳ በብዛት የክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ያፈናቅላሉ፤ የእምነት ስፍራዎችን ያጠቃሉ። ለዚህ ነው እነርሱ ክርስቲያኖችን ለይተው ያጠቃሉ የተባሉት።"

ኢንተርሶሳይቲ ሽፍታዎች ሲል የጠራቸው የፉላኒ ብሔር አባላት በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ በሚፈጸሙ እገታዎች እና የክርስቲያን እና ሙስሊሞች ሞቶች ተጠያቂ አድርጓቸዋል።