በማዕከላዊ ናይጄሪያ ሃይማኖታዊ ጉዞ ላይ የነበሩ 28 ሙስሊሞች ታገቱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
በማዕከላዊ ናይጄሪያ ፕላቱ ግዛት ዓመታዊ የእስልምና ክብረ በዓል ለመታደም ሲጓዙ የነበሩ 28 ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ ተናገረ። ከታጋቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚገኙበትም ተገልጿል።
ተሳፋሪዎቹን ይዞ ሲጓዝ የነበረው አውቶብስ እሑድ ምሽት ድንገተኛ ጥቃት የተከፈተበት በአንስተኛ መንደሮች መካከል እየተጓዘ በነበረበት ሰዓት ነው።
የፖሊስ ቃል አቀባይ አላቦ አልፍሬድ እንደተናገሩት ተጎጂዎቹን ለማስለቀቅ እገታው ወደተፈጸመበት አካበባቢ የጸጥታ "አካላትን ተሰማርተዋል።"
ይህ የእገታ ዜና የተሰማው፤ የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ባለፈው ወር በኒጀር ግዛት በሚገኝ የካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በተፈጸመው እገታ ተወስደው የነበሩ የመጨረሻዎቹን 130 ተማሪዎች እና መምህራንን ማስመለሳቸውን ይፋ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ነው።
በፕላቱ ግዛት የሚገኝ አንድ ጋዜጠኛ እንደሚናገረው የአሁኖቹ ታጋቾች ቤተሰቦች ገንዘብ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ ነው። ፖሊስ የጥቃቱ ፈጻሚዎች ማን ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን በተመለከተ የተናገረው ነገር የለም።
በአካባቢው ነዋሪዎች "ሽፍታዎች" እየተባሉ የሚጠሩት የወንጀል ቡድኖች ገንዘብ ለማግኘት የሚፈጽሙት እገታ በሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ናይጄሪያ እየተለመደ መጥቷል።
ናይጄሪያ ውስጥ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ሲባል ገንዘብ መክፈል ሕገ ወጥ ተግባር ቢሆንም ብዙ ሰዎች ነጻ የወጡት በክፍያ እንደሆነ እና ወንበዴዎቹን ገንዘብ የሚያገኙት በዚሁ መንገድ እንደሆነ ይታሰባል።
በፕላቱ ግዛት የተፈጸመው እገታ፤ ጀሃዲስት ቡድኖች ከ10 ዓመት በላይ ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ባሉበት የአገሪቱ ሰሜን ምሥራቃዊ ክፍል ከሚታየው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ አይደለም።
ናይጄሪያ ውስጥ ያለው የደኅንነት እጦት በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር የተነሳ ካለፈው ሕዳር ወር አንስቶ በድጋሚ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቷል። በአገሪቱ ውስጥ ክርስቲያኖች የጥቃት ዒላማ እየተደረጉ እንደሆነ የሚናገሩት ትራምፕ፤ ወታደሮቻቸውን ወደ ናይጄሪያ እንደሚልኩ ዝተው ነበር።
የናይጄሪያ የፌደራል መንግሥት የጸጥታ ችግር መኖሩን ቢያምንም ክርስቲያኖች ተለይተው እየተጠቁ ነው የሚለውን ንግግር ውድቅ አድርጓል።
የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ሞሀመድ ኢድሪስ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር፤ ከደኅንነት እጦት እና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ነው ከተባለው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ ጋር የተፈጠረው ውጥረት "በአብዛኛው መፈታቱን" ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ አገራቸው ከዋሽንግተን ጋር ያላት ግንኙነት መጠናከሩን አክለዋል።
አክለውም፤ ደኖችን ሰላማዊ ለማድረግ እና የወንጀለኛ ቡድኖች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመደገፍ ሲሉ የሚደበቁባቸውን ቦታዎች ደኅንነት ለማስጠበቅ የሰለጠኑ እና የታጠቁ የጫካ ወታደሮች እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል።















