በናይጄሪያ ታግተው የነበሩ 100 የሚሆኑ ተማሪዎች ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ባለፈው ወር በማዕከላዊ ናይጄሪያ ከሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት ታግተው ተወስደው የነበሩ 100 የሚሆኑ ሕፃናት ተለቀቁ።
ተማሪዎቹ ከተለቀቁ በኋላ በወታደራዊ መኪና እና መሣሪያ በታጠቀ ተሽከርካሪ ታጅበው በኒጀር ግዛት መዲና ሚና የደረሱ ሲሆን የግዛቷ አስተዳዳሪ ኡመር ባጎ ተቀብለዋቸዋል።
ሕፃናቱ በድርድር ይሁን በኃይል ስለመለቀቃቸው እንዲሁም የማስለቀቂያ ገንዘብ ተከፍሎ እንደሆነ ጭምር የተለቀቁበት ዝርዝር ሁኔታ ግልጽ አይደለም።
በቅርቡ በተፈፀመው የጅምላ ጠለፋ ከ250 በላይ ተማሪዎች እና 12 ሰራተኞች ፓፒሪ ከሚገኘው ቅድስተ ማሪያም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ታግተው የተወሰዱት ባለፈው ወር ነበር።
ከእገታ የተለቀቁት ተማሪዎች ዛሬ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደሚገናኙበት ከአገሪቷ መዲና ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ትምህርት ቤት እንደሚወሰዱ ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።
ድርጊቱ የተፈፀመበት ግዛት ጎረቤት የሆነችው ናሳራዋ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱላሂ ሱሌ፣ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ የፌደራል መንግሥት ቁልፍ ሚና መጫዎቱን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ሆኖም ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ከጀርባ የተደረገውን ጥረት "ለደኅንነት ሲባል" መግለጽ እንደማይቻል አስተዳዳሪው አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ኑሁ ሪባዱ ፓፒሪን የጎበኙ ሲሆን እዚያም በቄስ ቡሉስ ዳዋ ዮሃና የተመራ ልዑክ ጋር በተገናኙበት ወቅት ሕፃናቱ በቅርቡ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚቀላቀሉ አረጋግጠዋል።
ሆኖም አሁንም 153 ተማሪዎች እና 12 ሰራተኞች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እጅ ናቸው።
በቅርቡ በሰሜን እና በማዕከላዊ ናይጄሪያ በተፈፀሙ ጥቃቶች በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች እና የእምነት ተቋማት ኢላማ ሆነዋል።
ከሦስት ሳምንት በፊት በቅድስተ ማርያም ትምህርት ቤት የተፈፀመው ጥቃትም ከቀናት በፊት ቀደም ብሎ የተፈፀመውን የጅምላ ጠለፋ ተከትሎ የሆነ ነው።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 18 ክዋሬ ግዛት በሚገኘው ክሪስት አፖስቶሊክ ቤተክርስቲያን በተፈፀመው ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ 38 ሰዎች ደግሞ ታግተው ነበር።
ከዚህ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ በኬቢ ግዛት በሚገኝ የመንግሥት የሴቶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ተማሪዎች ሲገደሉ 25 ሙስሊም ተማሪዎች ታግተዋል።
በክዋሬ እና በኬቢ ጥቃት ታግተው የተወሰዱት ሁሉም ተለቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በኮጊ ግዛት አዲስ በተመሰረተ ቤተክርስትያን ላይ ታጣቂዎች በፈፀሟቸው ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች ፓስተር እና ባለቤቱን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች ታግተዋል።ከታገቱት መካከል ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት ሶኮቶ ግዛት የታገቱት አንዲት ሙሽራ እና ሚዜዎቿ ይገኙበታል።
ከእገታዎቹ ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን ግልጽ አይደለም። ሆኖም የማስለቀቂያ ገንዘብ በሚፈልጉ ወንጀለኛ ወንበዴዎች የተፈፀሙ እንደሆኑ በርካታ ተንታኞች ያምናሉ።
የፕሬዚደንቱ ቃል አቀባይ ግን ቀደም ብሎ ድርጊቱ የጂሃዲስት ቡድኖች ሥራ እንደሆነ መንግሥት እንደሚያምን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እገታዎችን የሚፈፅሙ ወንበዴዎች የሚያገኙትን የገንዘብ አቅርቦት ለመቁረጥ ሲባል በናይጄሪያ ለማስለቀቂያ ገንዘብ መክፈል ሕገ ወጥ ተደርጓል። ሆኖም አሁንም የማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው በስፋት ይታመናል።
ባለፈው ወር የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የናይጄሪያ መንግሥት "ክርስትያኖች እንዲገደሉ መፍቀዱን የሚቀጥል" ከሆነ ወታደሮችን እንደሚልኩ ካስፈራሩ በኋላ የአገሪቷ የጸጥታ ቀውስ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል።
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እና ተንታኞች በበኩላቸው የሁሉም እምነት ተከታዮች የጥቃቱ እና የእገታው ሰለባዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ክርስትያኖች ብቻ ኢላማ ይደረጋሉ የሚለው እውነት እንዳልሆነ ገልጸዋል።















