ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው፡ ለሴቶች ደኅንነት ባደረጉት ጥረት ለኖቤል ሽልማት እስከመታጨት የደረሱት ኢትዮጵያዊት

ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው

የፎቶው ባለመብት, Birhane

የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

በ1930ዎቹ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አገር ነበረች? የማኅበረሰቡ አኗኗር? የሴቶች ቦታስ? ለመገመት ባያዳግትም ባህላዊ ዕሴት እና መደብ ላይ የፀና ሥርዓት ያለባት አገር የሚል አጭር መልስ መስጠት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በጣሊያን ተወርራ አርበኞቿ በትግል፤ ንጉሧ ደግሞ በስደት፤ ገባሪ እና አስገባሪ ሥርዓት በነበረበት፤ ሴቶች ሁለተኛ መደብ በነበሩበት ዘመን፤ ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ሺህዎቹን በጨፈጨፈበት ማግስት በጎንደር ብርሃኔ የተባለች አንዲት ሴት ተወለደች።

ብርሃኔ አስፋው ፊታውራሪ በሆኑት አያቷ ቤት ብታድግም ሴት መሆኗ ብቻ እንደማንኛውም የዘመኑ ሴት ቀድሞ የተፃፈ ዕጣ ፈንታ ነበራት።

ግን ደግሞ እምቢተኝነት መንገዷን በራሷ እንድትመራ አድርጓታል።

በ1931 ዓ.ም. የተወለዱት ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ሴቶች እንዳይገረዙ የሚያደርግ ሕጎች እንዲወጡ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ብርቱ ሴት ናቸው።

87 ዓመታቸውን የያዙትን የወ/ሮ ብርሃኔን ግለ ታሪክ የሚዳስስ "የጨረቃ ብርሃን" የተሰኘ መፅሐፍ ባለፈው ታኅሣሥ ለንባብ በቅቷል።

መፅሐፉ አድኃኖም ምትኩ እና ዮሐንስ አዝመራው በተባሉ ሁለት ፀሐፊዎች የተዘጋጀ ነው።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለታሪኳ ወ/ሮ ብርሃኔ ሕይወታቸው ሙሉ እኩልነት እና ፍትሕ ላይ ያጠነጠነ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከአስተዳደረጋቸው እስከ ማኅበረሰባዊ ጫና፤ ከቤተሰባቸው እስከ የትምህርት ጉዟቸው፤ ከመምህርነት እስከ መብት አርበኝነት የሚዳስሰውን መፅሐፍ ሲያነቡት ወ/ሮ ብርሃኔ "በጣም ነው የገረመኝ" ይላሉ፤ የራሳቸው ታሪክ እንዳልሆነ ሁሉ ስምንት አስርት ዓመታትን የተሻገረ ሕይወታቸው በወረቀት እና ቀለም መልክ አበጅቶ ሲታተም።

"በዚያን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ሁሉ አልፌ፤ በዚያን ጊዜ በነበረው ባህል፣ በነበረው ልምድ፣ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ዝቅ ያለ በነበረበት ጊዜ፤ እኔ ያን ሁሉ አልፌ ዩኒቨርስቲ ገብቼ፤ ተመርቄ እዚህ ቦታ ደረስኩ ብዬ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ። ይህ በእውነት ትልቅ አጋጣሚ እና ዕድል ነው" ይላሉ።

ወ/ሮ ብርሃኔ ለዚህ ስሜታቸው ትልቅ ምክንያት አላቸው፤ ይህም ጊዜው ነው።

"ብዙ ሴቶች የሚዳሩበት ጊዜ ነበር። . . .ዕድል ነው ያጋጠመኝ እንጂ፤ ሁኔታው አይፈቅድም ነበር" ይላሉ የተፃፈላቸውን ዕጣ ፈንታ ተሻግረው የሚሊዮኖች ሴቶች ሕይወት የቀየረውን ሥራቸውን መለስ ብለው ሲያስቡ።

ወ/ሮ ብርሃኔ የመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት ስምምነት ላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የሚከለክሉ አንቀፆችን አርቅቀዋል፤ በስምምነቱ እንዲካተቱቱም ውትወታ አድርዋል።

የሰብዓዊ መብት አርበኛ የሆኑት ወ/ሮ ብርሃኔ 60 ዓመታት የዘለቀ ስኬታማ ትዳርም አላቸው።

 ወ/ሮ ብርሃኔ

የፎቶው ባለመብት, Birhane

የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ ብርሃኔ በወጣትነታቸው

"እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወ/ሮ ብርሃኔ ከራስ ዳሸን ተራራ ስር አድገው እስከ ሦስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ቤተሰባቸው ወደ ደሴ በመዘዋወሩ አብዛኛውን የትምህርት ሕይወታቸውን ደሴ ነው ያሳለፉት።

በወ/ሮ ስኂን እና እቴጌ መነን ትምህርት ቤቶች ተምረው በቀድሞው ቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጣት ከሚቆጠሩት ሴት ተማሪዎች አንዷ ሆነው የመጀመሪያ ድግሪያቸውን አግኝተዋል።

ነገር ግን ይህ አይደለም ታሪካቸው ጎላ ብሎ እንዲፃፍ ያደረገው። ወ/ሮ ብርሄኔ ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሮ ያደገው አንድ ባህሪያቸው የሕይወታቸውን መንገድ መርቶታል። ይህም ኢ-ፍትሐዊነት መጠየፋቸው ነው።

ምንም እንኳ አስገባሪ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድጉም ለገባሪ ተቆርቋሪ ነበሩ። ይህ የልብ ትግላቸውም መስመር የያዘው ኑሯቸውን ከባለቤታቸው ጋር በመሠረቱበት ጄኔቭ ነው።

በስዊትዘርላንድ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ "የዓለምን አቀማመጥ ተረዳሁ። የኢ-ፍትሐዊነትን ሥርዓት/ስልተ መሠረት አጠናሁ" ሲሉ መፃፋቸው ላይ ገልፀውታል።

በተለይም ደግሞ "Missusing symbols" የተባለው ትምህርት በማኅበረሰቡ ቅቡልነት እና ከበሬታ ባላቸው ባህል እና ሃይማኖት በማሳበብ ለኢ-ፍትኃዊነት የተዘጋጀ መደላድል መሆኑን የተረዱበት ነው።

በመንግሥታቱ ድርጅት ስር ለፆታ እኩልነት እና ሴቶች መብት በሚሠራው አካል ውስጥ መሥራት ሲጀምሩ ደግሞ የሕይወታቸውን እኩሌታ ያሳላፉበትን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የበኩላቸውን አበርክተዋል።

ግን ከእኩልነቱ በፊት ሰው የመሆን ትግል ነበር። አህጉራቸው አፍሪካ ላይ ስር የሰደደው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ሽፋን የተጎናፀፈው የሴት ልጅ ግርዛትን ሊዋጉ ሲነሱ፤ ለዘመናት ሊቆይ በጽኑ መሠረት ላይ የተቀረፀ የመሰለው ሥርዓት፣ አስተሳሰብ፣ ባህል . . .እጁን ዘርግቶ አልተቀበላቸውም።

ይልቁንም አፍ አውጥቶ ተሟገታቸው፤ ፈተናቸው። እርሳቸውም የዋዛ አልነበሩም እና ድርጅት መሥርተው፤ መሳሪያቸውን ስለው ብቅ አሉ።

"እኔ በተፈጥሮዬ ሰው ሲጎዳ ማየት አልወድም ነበር፤ ልጅም እያለሁ። አንድ ሰው ደሀ ነው፤ ሌላ አማራጭ የለውም ተብሎ ሲገፋ እና ሲጨቆን ሳይ አለቅስ ነበር" በማለት ከሚገፉ ጎንመቆም አብሯቸው ያደገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ወ/ሮ ብርሃኔ ከቤተሰቦቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Birhane

ወ/ሮ ብርሃኔ በ1970ዎቹ መጨረሻ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የሚሠራውን ኢንተር አፍሪካ ኮሚቴ (Inter Africa committee) የተባለውን ድርጅት በመመሥረት ለ27 ዓመት ፕሬዝዳንት ሆነው መርተውታል።

የሴት ልጅ ግርዛት ሆነ ተብሎ የሴት ልጅን የመራቢያ አካል መቁረጥ ማለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ይሄ ጎጂ ድርጊት የሚፈፀመው ከሴቶች ንፅህና እና ከትዳር ጋር ይገናኛል።

"በጣም ጨቋኝ ባህል ነበር፤ አሁንም አለ። ሴቶች መገረዝ አለባቸው የሚል።. .. ይህን የመተለልተል፤ የመገረዝ ልማድን ካየሁ በኋላ በጭራሽ መንፈሴ አልረጋም። ይህን ማስወገድ አለብኝ፤ ይሄ ነገር መቅረት አለበት ብዬ [ተነሳሁ]" ይላሉ ወ/ሮ ብርሃኔ የረጅም ዘመን ትግላቸውን አነሳስ ሲገልፁ።

"ጂቡቲ አንዲት ልጅ እግሯ ታስሮ ስትተለተል በዓይኔ አይቻለሁ። ይህን አይቼ እንዴት ብዬ ልለፍ? ምዕራብ አፍሪካ ስሄድ [ደግሞ] ይህ ባህል በጣም ጨቋኝ እና አደገኛ በመሆኑ በፍጹም መንፈሴ አላረፈም፤ ትግሉን ቀጠልኩ" ይላሉ።

በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ከአስገራዦች (ወላጆች) እስከ ገራዥ (የባህል ሐኪሞች)፤ ከማኅበረሰብ መሪዎች እስከ ፖለቲከኞች መክረዋል።

በመጨረሻ የልፋታቸው ውጤት የመብት ሕግ ሆኖ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲከለከል ሆነ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መብትን (UN convention on the rights of a child) በማርቀቅ እና በመወትወት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

ይህ ስምምነት የሴቶችን ግርዛት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሲል ድርጊቱን ይከለክላል። የድንጋጌው አንቀፅ 24/3 መንግሥታት የሕፃናትን ጤና የሚጎዳውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስወገድ ሕግ እንዲያወጡ፣ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ እና ማኅበራዊ እርምጃዎች እንዲወስዱ ያስገድዳል።

ይህ ድንጋጌ እንዲወጣ የወ/ሮ ብርሃኔ እና የድርጅታቸው ሚና ወሳኝ ነበር። ይህ ልዩ አንቀፅ እንዲገባ ውትወታ ካደረጉ ጥቂት ባለሙያዎች ውስጥ ወ/ሮ ብርሃኔ አንዷ ናቸው። ከዚህ ባሻገርም የአፍሪካ ኅብረት የሴቶችን መብት በስፋት በሚዳስስበት የማፑቶ ስምምነት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የሚከለክሉ አንቀፆች እንዲካተቱም አበርክቶ አላቸው።

ወ/ሮ ብርሃኔ ከተለያዩ አገራት ባልደረቦቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Birhane

የምስሉ መግለጫ, "ጂቡቲ አንዲት ልጅ እግሯ ታስሮ ስትተለተል በዐይኔ አይቻለሁ"

ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ኋላ ዞር ብለው ሲቃኙም እንዲህ ይላሉ።

"[የሴት ልጅ ግርዛት] እየታወቀ፤ እየቀነሰ ይመስለኛል። እኛም አገር እየቀነሰ ያለ ይመስለኛል። ጨርሶ ግን ጠፍቷል ለማለት ያስቸግራል። ግን ጥሩ ነው፤ ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል ይባላል።

"የዚህ ባህል መቅረት ቀስ በቀስ እየታየ ነው። መጨረሻም ጊዜ ይወስድ ይሆናል። ግን ጨርሶ የሚቀር ባህል ነው። የሴቶችን መብት በጣም አደጋ ላይ የሚጥል ነው። የመኖር ያለመኖር ጥያቄ ነው" ይላሉ ስሜታቸው ዛሬም ድረስ ከግለቱ ሳይበርድ።

ወ/ሮ ብርሃኔ በ80 የዓለም አገራት ተዘዋውረዋል። ከአፍሪካ እስከ እስያ፤ ከላቲን አሜሪካ እስከ አውሮፓ ለሴቶች ሲሉ ኳትነዋል።

አስርት ዓመታትን በዘለቀው ልምዳቸውም ለውጥን መገንዘብ ችለዋል። ነገር ግን አሁንም ይቀረናል ይላሉ። ሕጎች ቢኖሩም "የባህል ልምድ" አሁንም አላራምድ ብሏል ይላሉ።

ባለፉት 30 ዓመታት በአጠቃላይ በአፍሪካ የሴቶች ግርዛት ቀንሷል። ነገር ግን እንደ ቻድ፣ ማሊ እና ሴራሊዮን ባሉ አገራት ደግሞ እስከ ስምንት በመቶ እንደጨመረ ጥናቶች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያን የተመለከትን ከሆነ የሴት ልጅ ግርዛት ከ25 ዓመት በፊት ከነበረበት 80 በመቶ ገደማ ወደ 65 በመቶ ዝቅ ማለቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሆኖም በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች ከ90 በመቶ በላይ ሴቶች ይገረዛሉ።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ እየቀነሰ ቢሆንም፤ ጠንካራ ክትትል እና ሥራዎች ጥረቶች ተሟጋቾች ይወተውታሉ።

ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Birhane

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት 30 ዓመታት በአጠቃላይ በአፍሪካ የሴቶች ግርዛት መቀነሱን ጥናቶች ያሳያሉ

ለኖቤል ሽልማት መታጨት

ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው ለሴቶች ጤና እና ደኅንነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ እርሳቸው እና ድርጅታቸው በሽልማት ተንበሽብሸዋል።

ድርጅታቸውን አቋቁመው ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም ሲታትሩ የተመለከቱ ሰዎች ለአንድ የከበረ ላለ ሽልማት አሰቧቸው።

የወ/ሮ ብርሃኔን ትጋት እና ብርታት ያዩ ለአብነት ያህል ኢንተርናሽናል ካውንስል ኦፍ ውሜን እና ኢንተርናሽናል ፖፑሌሽን ካውንስል የተባሉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሰባስበው መቀመጫውን ኖርዌይ ላደረገው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ አጯቸው።

ጊዜው ደግሞ በ1980ዎቹ መጨረሻ ነበር።

". . . እዚያም [በኮሚቴው] ተቀባይነት ተገኘ መሰለኝ። እነርሱም አስቀድመው በየቦታው የሠራሁትን ሥራ ማጥናት አለባቸው።...እና አገሬ ደግሞ መጥተው ይህን ነገር አጥንተው መንግሥት ምን እንደሚል፤ ባለሥልጣናቹ ምን እንደሚሉ ማወቅ ነበረባቸው" ይላሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዱ።

ነገር ግን ዕጩነታቸው ያን ያህል መራመድ አልቻለም። ወ/ሮ ብርሃኔ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በቂ ድጋፍ አለመስጠቱን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

"እኔ ደግሞ ያን ጊዜ የሰዎች መብት ሲረገጥ፣ አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ይፈጽም የነበረው እስር፣ መንገላታት. . .በጣም ይቆጨኝ ነበር፤ እቃወማለሁ። መንግሥትን ተቃውሜ ሰልፍም እወጣ ነበር። ይህ በደርግ ጊዜ ጀምሮ በኋላም የሆነ ነው። ይሄ ደስ አላላቸውም" ይላሉ።

የታጩበት የኖቤል ሽልማት "አገሬ ስላልፈቀደችልኝ ሳይሆን ቀረ" የሚሉት ወ/ሮ ብርሃኔ፤ ልባቸው ግን ቂም አልቋጠረም።

"ባገኘው ደስ ይለኝ ነበር። ግን ይሄ ቀረብኝ የምለው የለም። [ሥራዬን] አላቆምኩም፤ ቀጠልኩ። እዚህ ደርሻለሁ" ይላሉ በቂ ሽልማት ማግኘታቸውን በመጥቀስ።

ከእርሳቸው በኋላ የመጡት ከሽሪን ኢባዲ እስከ ማላላ የሱፍ ዛይ ድረስ ያሉ ሴቶች ለሴቶች እና ሕፃናት መብት በመታገል የኖቤል የሰላምን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ወ/ሮ ብርሃኔ ከክፍለ ዘመን በፊት የተመሠረተ የኦስትሪያ መንግሥት የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ባለው ዓመት እናት ባንክ በስማቸው ቅርንጫፍ ከፍቷል።

ወ/ሮ ብርሃኔ ከቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Birhane

የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ ብርሃኔ ከቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ጋር

60 ዓመታትን የተሻገረ ትዳር እና አጋርነት

ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው ረጅም የትዳር ሕይወት ያላቸው ስኬታማ ሴት ናቸው። ከባለቤታቸው አቶ ተረፈ ራስወርቅ ጋር ከ60 ዓመት በላይ በዘለቀ ትዳር ውስጥ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።

ባለቤታቸው አቶ ተረፈም በራሳቸው ጎራ ስኬታማ ሰው ናቸው።

በትውውቅ የተጀመረው ግንኙነታቸው ጠንክሮ መፈቃቀዱ ሲደረጅ እና ባለቤታቸው "የታገቢኛለሽ" ጥያቄ ሲያቀርቡ የእሽታ ወይም የእምቢታ ምላሽ አልነበረም የተሰጣቸው።

የወ/ሮ ብርሃኔ የሰጡት መልስ "እኔ ወጥ መሥራት አልችልም" የሚል ነበር፤ ለምን እንደዚያ ለማለት ደረፈሩ?

"ያኔ ሴት ልጅ ከመዳሯ በፊት ምግብ መሥራት መማር አለባት። ባልየውም ሳገባ እርሷ ናት ወጥ የምትሠራው ብሎ ያስባል። እኔ ግን ከልጅነት ጀምሬ ወጥ ቤት መግባት አልወደም ነበር። እናቴ አንዳንድ ጊዜ 'ኧረ እባክሽ' ስትለኝ እኔ 'አልችልም፤ አልፈልግም፤ እምቢ' ባይ ነበርኩ።

"እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ሳለን ወጥ መሥራት ተማሩ እንባላለን። እና እኔ ስፌት መስፋት እና ወጥ መሥራት በጣም የደከመ ውጤት የማመጣበት ዘርፍ ነበር። አልወድም ነበር" ይላሉ።

ለዚህም ነው "እውነቱን መንገር አለብኝ" የሚል አቋም የያዙት።

"ላገባህ እፈልጋለሁ። ይኸውልህ አንድ ነገር ልንገርህ ወጥ መሥራት አልችልም፤ ይህን አትጠብቅ አልኩት። እሱም 'ግድ የለሽም፤ እኔ ምግብ መሥራት አሜሪካን አገር ለምጃለሁ፤ እኔ እሠራለሁ' አለኝ።"

ከዚያም ጋብቻቸውን ፈፀሙ።

አቶ ተረፈ ራስወርቅ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሞት እስኪለዩ ድረስ ለ60 ዓመታት "በሰላም፣ በፍቅር፣ በመከባበር" እንደኖሩ ወ/ሮ ብርሃኔ ይናገራሉ።

ስለ ባለቤታቸው ሲመሰክሩም "ባል ብቻ አልነበረም" ይላሉ። "ትልቅ ሰው፣ የኑሮዬ ምሰሶ. . ." ይሏቸዋል።

ከትዳር አጋርነታቸው ባሻገር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን ለማጥፋት የጀመሩት ዘመቻ አጋር፣ አማካሪ፣ አስተማሪ እና ጓደኛ እንደነበሩም ይመሰክራሉ።

"በእውነት ትልቁ የሕይወቴ መሪ እርሱ ነበር። የማደንቀው ሰው ነው። . . . እርሱ የእኔ ስኬት እንዳስደሰተው፤ በምሠራው ነገር ሁሉ ያበረታተኛል።"

ባለቤታቸው አቶ ተረፈ ወ/ሮ ብርሃኔንን በስኬታቸው ከመደገፍ በተጨማሪ እሳቸውም የመጀመሪያውን የአማርኛ ቴሌ ፕሪንተር በፈጠር ታሪክ የሠሩ ሰው ናቸው።

ወ/ሮ ብርሃኔ እና ባለቤታቸው አቶ ተረፈ ራስወርቅ

የፎቶው ባለመብት, Birhane

የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ ብርሃኔ 60 ዓመታት በላይ በዘለቀው ስኬታማ ትዳራቸው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል

ወ/ሮ ብርሃኔ ለጥንካሬያቸው ምንጭ "አንድ ነገር ብቻ አይደለም" ይላሉ። ዕድልን ትልቅ ስፍራ ቢሰጡም ከራሳቸው ጥረት ባልተናነሰ እናታቸው የመጀመሪያ አስተማሪያቸው በመሆን፤ አያታቸው ደግሞ በለጋ ዕድሜያቸው ለጋብቻ የሚቀርብ ጥያቄን በተደጋጋሚ በመመለስ ለስኬታቸው ያመሰግኗቸዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ደግሞ የደረሱበት ደረጃ የመጨረሻው የሴት ልጅ የትምህርት መዳረሻ እንዳልሆነ ይመክሯቸው የነበረውን በማንሳት ለደረሱበት "ተጨማሪ ምክንያቴ" የሚሏቸው።

ወ/ሮ ብርሃኔ በተሰማሩበት ዘርፍ የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ማኅበረሰቡን ወደፊት የሚያራምዱ ሰዎችን ያደንቃሉ። "መስዋዕትነታቸው ክቡር ነው" ብለው ያምናሉ። ይህን በመፅሐፋቸው በግልፅ ያትታሉ።

የአያሌ ሴቶችን ሕይወት የቀየሩት፤ የረጅም የሕይወት ምዕራፎችን የተሻገሩት ወ/ሮ ብርሃኔ 'እንዴው በሕይወትዎ ይህን ባደርግ ኖሮ፤ ባላደርግ የሚሉት ጉዳይ ምንድን ነው? ምን ይጸጽትዎታል?' ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄ "የምችለውን አድርጌያለሁ" ይላሉ።

ለአፍታ ካሰላሰሉ በኋላ ደግሞ አያታቸው መላው ቤተሰባቸውን እና ጓዛቸውን ከአገልጋዮቻቸው ጋር በሦስት መኪና ጭነው ሲሰደዱ እቅፉን ከፍቶ የተቀበላቸው የወሎ ሕዝብ በረሃብ ቸነፈር ሲጎዳ ተጉዘው አለመርዳታቸው ግን ይጸጽታቸዋል።

"አንዳንዴ መንፈሴ ውስጥ ይመጣል። ዘመዶቼ ናቸው የተራቡት። ምንም ሳላደርግ በመቅረቴ አንዳንድ ጊዜ ይመጣብኛል" ይላሉ።