ከቢሾፍቱው የአውሮፕላን ማረፊያ የዲዛይን አማካሪዎች አንዱን የመሠረተችው ዕውቅ አርክቴክት ዛሃ ሐዲድ ማን ናት?

ዛሃ ሐዲድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ አቅራቢያ አቡሴራ በሚባል አካባቢ ለሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መሠረተ ድንጋይ የተቀመጠው ከቀናት በፊት ነው።

በ12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ እንደሚችል ተገልጿል።

አውሮፕላን ማረፊያው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ እንደሚችል ይጠበቃል። አውሮፕላን ማረፊያው በ3,500 ሔክታር መሬት ላይ የሚገነባ ይሆናል።

የአውሮፕላን ማረፊያው መሠረተ ድንጋይ ሲቀመጥ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አርክቴክት ዛሃ ሐዲድ ትጠቀሳለች።

ዛሃ ሐዲድ ከኪነ ሕንጻ ጋር በተያያዘ በዓለም ስመ ጥር ከሆኑ ባለሙያዎች አንዷ ነበረች።

ከቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የዲዛይን አማካሪዎች አንደኛው ዛሃ ሐዲድ ያቋቋመችው 'ዛሃ ሐዲድ አርክቴክትስ' ነው። ሌላኛው ተቋም ደግሞ ዳር ይሰኛል።

ዴም ዛሃ መሐመድ ሐዲድ (ዛሃ ሐዲድ) ኢራቃዊት-እንግሊዛዊት አርክቴክት፣ ዲዛይነር እና አርቲስት ነበረች።

በአውሮፓውያኑ 1950 ኢራቅ፣ ባግዳድ ውስጥ ተወለደች። በአውሮፓውያኑ 2016 በልብ ድካም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

የኪነ ሕንጻው ዓለም ፈርጥ እንደሆነች የሚነገርላት ዛሃ ሐዲድ ከተመለደው ወጣ ባሉ ግንባታዎች ስሟ ይወደሳል።

ተፈጥሯዊ የሆኑ መስመሮች እና እጥፋቶች ለአብዛኞቹ ዲዛይኖቿ መነሻ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ዛሃ ሐዲድ አንድ ሕንጻ እንድትገነባ ስትጠየቅ መጀመሪያ አካባቢውን ታጠናለች። ሕንጻውን ዲዛይን ከማድረጓ አስቀድሞ ሐሳቧን በሥዕል ትሰንዳለች።

ዛሃ ሐዲድ በ2004 የመጀመሪያዋ ሴት የፕሪዝከር አርክቴክቸር ተሸላሚ ሆናለች። ሽልማቱ በኪነ ሕንጻ ዲዛይን እጅግ ከፍተኛው ነው።

የዛሃ ሐዲድ ተቋም በ2024 በድረ ገጹ ባወጣው ሐተታ፤ ዳር ከሚባለው ተቋም ጋር በመሆን ለቢሾፍቱው የአውሮፕላን ማረፊያ የዲዛይን አማካሪ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

የዛሃ ሐዲድ አርክቴክትስ የአቪዬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ክርስቲያኖ ሴሳቶ "አዲሱ የአቡሴራ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ አፍሪካ ለመግባት ቀዳሚው በር እና ኢትዮጵያንም የአህጉሪቱ የመጓጓዣ ማዕከል የሚያደርግ ይሆናል" ማለታቸው በድረ ገጹ ተመልክቷል።

አውሮፕላን ማረፊያው ዲዛይን የሚደረገው "ከአገሬው ባህል" በመነሳት እንደሆነ እና ግንባታው ሲጠናቀቅ "የዓለም ቀልጣፋው አውሮፕላን ማረፊያ" እንደሚሆን ተገልጿል።

"የአቡሴራን መልከዓ ምድር ባማከለ መንገድ ተፈጥሮ የዲዛይኑ ማዕከል ይሆናል" በማለትም የዛሃ ሐዲድ አቪዬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ገልጸውታል።

ዛሃ ሐዲድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የግንባታ አካባቢን ያማከለ ዲዛይን አርክቴክቷ ዛሃ ሐዲድ ከምትታወቅባቸው ጥበቦች አንዱ ነው።

የኢራቅ እና እንግሊዝ ጥምር ዜግነት ያላት ዛሃ ሐዲድ 'ሮያል ኢንስቲትዮት ኦፍ ብሪትሽ አርክቴክትስ' የተባለውን የወርቅ ሽልማት ያገኘች የመጀመሪያዋ ሴት ናት።

ሽልማቱን ስትቀበል "አሁን ላይ ዕውቅና ያላቸው ሴት አርክቴክቶች እያየን ነው። ቀላል ነው ማለት አይደለም። ፈተናዎቹ ብዙ ናቸው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን ትልቅ ለውጥ ታይቷል። ይህንንም እናስቀጥላለን" ማለቷ ተዘግቧል።

የዛሃ ሐዲድ ሕንጻዎች በዩናይትድ ኪንግደም፣ በሆንግ ኮንግ፣ በጀርመን፣ በአዘርባጃን እና በሌሎችም በርካታ አገራት ይገኛሉ።

የቻይና ጉዋንዡ ኦፔራ ሐውስ፣ የለንደን ሰርፔንቲን ሳክለር ጋለሪ እና የግላስጎ የትራንስፖርት ሙዚየም ከዲዛይኖቿ መካከል ይጠቀሳሉ።

ለዩናይትድ ኪንግደም አርክቴክቶች የሚሰጠውን የሪባ ስተርሊንግ ፕራይዝ ሽልማትን ሁለት ጊዜ አሸንፋለች። በ2010 የሮም ማሲ ሙዚየም ሲሸልማት በ2011 ብሪክስተን የሚገኘው ኤቨሊን ግሬስ አካዳሚ ሽልማት ሰጥቷታል።

ዛሃ ሐዲድ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቤይሩት ሒሳብ አጥንታለች። ኋላ ላይ ለዩኒቨርስቲው አንድ ሕንጻ ዲዛይን አድርጋለች።

ዛሃ ሐዲድ አርክቴክስትን ያቋቋመችው በ1979 ነበር።

የመጀመሪያ ትልቅ ፕሮጀክቷ በጀርመን፣ ዊ አም ሪን የተገነባው 'ቪትራ' የተባለው የእሳት አደጋ መከላከያ ነው።

ዛሃ ሐዲድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለኦሊምፒክ ዲዛይን ያደረገችው የውሃ ላይ ውድድሮች የሚካሄዱበት 'ለንደን አኳቲክስ ሴንተር' የውሃ ወጀብ ቅርጽ ያለው ሲሆን፤ 50 ሜትር ጥልቀት ያለው የመዋኛ ገንዳን የያዘ ነው።

"የምኖርበት አካባቢ ስለተገነባ እወደዋለሁ" ስትል በአንድ ቃለ ምልልስ ወቅት ተናግራለች።

በ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ዋነኛ ከነበሩት ስቴድየሞች አንዱን ዲዛይን ያደረገችው ዛሃ ሐዲድ ናት።

ለ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ዲዛይን ያደረገችው ስቴድየም ግን ውድቅ ተደርጎ አነስተኛ ገንዘብ በሚያስወጣ ዲዛይን መተካቱ አነጋጋሪ ነበር።

ዛሃ ሐዲድ የ20ኛው እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኮከብ ከሚባሉ አርክቴክቶች መካከል እንደምትጠቀስ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ።

በወንዶች በበላይነት በተያዘ ዘርፍ ውስጥ ሥራዎቿ ዕውቅ እና ተቀባይነት እንዲያገኙ እንዲሁም ሴቶችን አካታች እንዲሆን መታገሏ ይነገርላታል።

የዲዛይን ጥበቧን ዘመናዊ እንዲሁም የወደፊቱ ዓለም ማሳያ ብለው የሚገልጹት ባለሙያዎች አሉ።

ለትምህርት ከኢራቅ የወጣችው በ17 ዓመቷ ነበር። ከቤሩት ዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ በለንደን አርክቴክቸራል አሶሴሽን ስኩል ኦፍ አርክቴክቸር ተምራለች።

ለ30 ዓመታት ወደ ኢራቅ ሳትመለስ ቆይታ በ2010 የባግዳድን ብሔራዊ ባንክ ሕንጻን ዲዛይን እንድታደርግ ስትጠየቅ "በጣም ስሜታዊ" እንደሆነች ተናግራለች።

ጀርመን ላይፕዢግ የሚገኘው የቢኤምደብሊው ሕንጻ እና በስፔን፣ በስፔን ዛራጎዛ የሚገኘው ድልድይ ከዛሃ ሐዲድ ዕውቅ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በ2014 በባኩ፣ አዘርባጃን የሠራቸው የሙዚየም ዲዛይን የዓመቱ ምርጥ ዲዛይን ተብሎ ተሸልሟል።

በሳዑዲ አረቢያ፣ ሪያድ ከምድር በታች የሚገነባ የባቡር ጣቢያ ዲዛይን አድርጋለች።

የዩናይትድ ኪንግደም አርክቴክቶች "የፆታ መድልዎ" እንደሚያሳዩ ዛሃ ሐዲድ ተችታለች።

ከዓመታት በፊት ባደረገችው ቃለ ምልልስ ዘርፉ "በወንዶች የበላይነት የተያዘ ነው" ብላ ነበር።

"በማስተምርበት ወቅት በጣም ጎበዞቹ ተማሪዎቼ ሴቶች ናቸው። ሁሉም ግን ቀስ ቀስ ይከስማሉ" ስትልም ተችታለች።

ሴት አርክቴክቶች ግዙፍ የንግድ ሕንጻዎችን ዲዛይን ከሚያደርጉ ይልቅ የመኖሪያ ሕንጻ ወይም ቅንጡ ሕንጻ ዲዛይን ቢያደርጉ የተሻለ ነው የሚል የተዛባ አመለካከት መኖሩን ትቃወም ነበር።

"ሴት ሆኜ ቆንጆ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ እንደምሠራ እርግጠኛ ነኝ። የወንዶች ብቻ ሥራ ነው ብዬ አላምንም" ማለቷ አይዘነጋም።

ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኙ የዛሃ ሐዲድ ሕንጻዎች

ዛሃ ሐዲድ ዲዛይን ያደረገቻቸው ሕንጻዎች ከተለመደው የሕንጻ ቅርጽ ወጣ በማለት ይታወቃሉ። እነዚህ ሕንጻዎች ለዕይታ ማራኪ የሆኑትም ለዚህ ነው።

አርክቴክቷ በተያዩ አገራት ከሠራቻቸው እና ታዋቂ ከሆኑ ሕንጻዎች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፦

የመጀመሪያ ትልቅ ፕሮጀክቷ በጀርመን፣ ዊ አም ሪን የተገነባው 'ቪትራ' የተባለው የእሳት አደጋ መከላከያ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Riba

የምስሉ መግለጫ, የመጀመሪያ ትልቅ ፕሮጀክቷ በጀርመን፣ ዊ አም ሪን የተገነባው 'ቪትራ' የተባለው የእሳት አደጋ መከላከያ ነው።
የለንደን ሰርፔንቲን ሳክለር ጋለሪ

የፎቶው ባለመብት, Riba/ Luke Hayes

የምስሉ መግለጫ, የለንደን ሰርፔንቲን ሳክለር ጋለሪ
በሮም ለተገነባው ብሔራዊ ሙዚየም ዲዛይን መነሻ የሆናት ቲበር ወንዝ እና እንቅስቃሴው እንደሆነ ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Riba

የምስሉ መግለጫ, በሮም ለተገነባው ብሔራዊ ሙዚየም ዲዛይን መነሻ የሆናት ቲበር ወንዝ እና እንቅስቃሴው እንደሆነ ተናግራለች።
ለኦሊምፒክ ዲዛይን ያደረገችው 'ለንደን አርኳቲክስ ሴንተር' የውሃ ወጀብ ቅርጽ ያለው ሲሆን፤ 50 ሜትር ጥልቀት ያለው የመዋኛ ገንዳ የያዘ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Riba

የምስሉ መግለጫ, ለኦሊምፒክ ዲዛይን ያደረገችው 'ለንደን አርኳቲክስ ሴንተር' የውሃ ወጀብ ቅርጽ ያለው ሲሆን፤ 50 ሜትር ጥልቀት ያለው የመዋኛ ገንዳ የያዘ ነው።
በባኩ፣ አዘርባጃን የሠራቸው የሙዚየም ዲዛይን የዓመቱ ምርጥ ዲዛይን ተብሎ ተሸልሟል።

የፎቶው ባለመብት, Helene Binet

የምስሉ መግለጫ, በባኩ፣ አዘርባጃን የሠራቸው የሙዚየም ዲዛይን የዓመቱ ምርጥ ዲዛይን ተብሎ ተሸልሟል።
በጣልያን ክሮንፕላዝ ተራራ ላይ የሚገኘው ኮሮኖስ ሙዚየም

የፎቶው ባለመብት, Inexhibit

የምስሉ መግለጫ, በጣልያን ክሮንፕላዝ ተራራ ላይ የሚገኘው ኮሮኖስ ሙዚየም