ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ውይይትን ለማስተናገድ ጥሪ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳን ጦር፣ የፖለቲካ እና የሲቪል ፓርቲዎች አካታች በሆነ አገራዊ ውይይት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ በአረብኛ ቋንቋ ባጋሩት መግለጫ በሱዳን ያለውን ጦርነት ለመቋጨት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ውይይቱን ለማዘጋጀት እና ለማስተባበር እንደሚሹ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ መድረኩን ለማዘጋጀት እና ግልፅ ውይይት እንዲካሄድ ለማስቻል ዝግጁ መሆኗን የገለፁት ዐቢይ፤ የሱዳን የተለያዩ ኃይሎች ልዩነታቸውን ፈትተው የፖለቲካ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እንደሚመኙ ገልፀዋል።
ዐቢይ ያቀረቡት ዕቅድ በሱዳን ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመቋጨት፣ በሱዳን ተዋጊ ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት እና ፖለቲካዊ ሽግግር ለማምጣት ያለመ መሆኑን መግለጫቸው ያትታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ዕቅዱ በፖለቲካ አጀንዳ የተመራ አለመሆኑን አስምረው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት መሠረት በማድረግ የአገሪቱ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና መረጋጋት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።
የሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሱዳናውያን ብቻ ነው የሚወሰነው ያሉት ዐቢይ፤ ሁሉን ያሳተፈ ውይይት ብቸኛው የሰላም አማራጭ መሆኑን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በሱዳን ወታደራዊ እና ሲቪል አመራሮች መካከል የነበረውን ልዩነት ለመፍታት ኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥረት አውስተው አዲስ አበባ ለኻርቱም ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
አራት ዓመታት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የሱዳን ጦርነት በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የሚደረግ ነው።
በጄኔራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድጋፍ ታደርጋለች ሲል ይከሳል። አዲስ አአባ ግን ይህንን ውንጀላ አትቀበለውም።
















