ባለንበት ዘመን የወጣቶች በካንሰር የመያዝ ዕድል እየጨመረ መምጣት ምክንያቱ ምንድን ነው?

በወጣቶች ላይ በስፋት እየታዩ ካሉት የካንሰር ዓይነቶች መካከል የጡት ካንሰር አንዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, SPL

የምስሉ መግለጫ, በወጣቶች ላይ በስፋት እየታዩ ካሉት የካንሰር ዓይነቶች መካከል የጡት ካንሰር አንዱ ነው

በ20ዎቹ፣ በ30ዎቹ እና በ40ዎቹ ያሉ ውጣቶች በጡት እና በአንጀት እንዲሁም በሌለች የካንሰር ዓይነቶች እየተጠቁ ነው። ለምን?

ባለፉት 10 ዓመታት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ እና አርጀንቲናን ጨምሮ በ24 ሀገራት በአንጀት ካንሰር የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጠን ከፍ ብሏል።

ዩአይሲሲ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የካንሰር ቁጥጥር ቡድን በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት አስደንጋጭ የሚባል ውጤትን ይዞ ቀርቧል።

የአሜሪካ የካንሰር ማኅበረሰብ (ኤሲኤስ) አጥኚዎች እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ተመራማሪዎች ከ50 ሀገራት ያሰባሰቡትን የምርምር ውጤት ይፋ አድርገዋል።

በ14 ሀገራት በተለይ ወጣቶች በካንሰር እየተጠቁ እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል።

በተጨማሪ ሌሎች ጥናቶች ይፋ እንዳደረጉት ወጣቶች በተለይ በጡት ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው ከፍ እያለ ነው።

የአሜሪካ የካንሰር ማኅበረሰብ ይፋ ያደረገው ጥናት በጡት ካንሰር ምክንያት የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር ባለፈው 10 ዓመት በ10 በመቶ ቀንሷል ይላል። ነገር ግን የመያዝ ዕድላቸው በየዓመቱ 1 በመቶ እየጨመረ ነው።

ይህ የካንሰር መስፋፋት የጀመረው በ1990ዎቹ እንደሆነ ጥናቶቹ ይጠቁማሉ። ከአውሮፓውያኑ 1990 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ወጣቶች በካንሰር የመያዝ ዕድላቸው 79 በመቶ ጨምሯል። በካንሰር ምክንያት የሚሞቱ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ላንሴት ፐብሊክ ሄልዝ የተሰኘው ተቋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚተነትነው በአሜሪካ በካንሰር የሚያዙ ወጣቶች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

ይህን ተከትሎ እንደ ዩአይሲሲ ያሉ ተቋማት በዓለም ዙሪያ ወጣቶች ስለካንሰር ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር እየተጉ ይገኛሉ።

የአንጀት ራጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአንጀት እና ጠያያዥ ክፍሎች ካንሰርም ከአሳሳቢዎቹ መካከል ናቸው

"ዕድሜያቸው ከ60 በላይ ያሉ ሰዎች ከወጣቶች ይልቅ የሐኪም ምክር ይሰማሉ" ይላሉ የዩአይሲሲ ባልደረባ የሆኑት ሶናሊ ጆንሰን።

"ምናልባት አሳሳቢ ያልሆነ ህመም አሊያም ከሥራ የመነጨ ጭንቀት አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። ለዚህ ነው ምልክት ሲያሳዩ መታከም ሲገባቸው ችላ የሚሉት።"

የካንሰር ባለሙያዎች እንደሚሉት ብዙውን ጊዜ ዕድሜያቸው ከ70 በላይ የሆኑ ሰዎችን የሚያጠቃው የጣፊያ ካንሰር በወጣቶች ላይ እየታየ ነው።

"ዕድሜያቸው ከ40 በታች የሆኑ ሰዎች የጣፊያ ካንሰር ተይዘው ማየት አዲስ ነገር አይደለም" የሚሉት ኒው ዮርክ በሚገኘው ሚሞሪያል ስሎን ኬተሪንግ የካንሰር ማዕከል የሚያገለግሉት የሕክምና ባለሙያዋ አይሊን ኦራይሊ ናቸው።

"በየሳምንቱ ይመጣሉ። አብዛኞቹ የወጣትነት ዘመናቸው ላይ ያሉ፤ ገና ቤተሰብ የመሠረቱ እና ሕይወትን ያላጣጣሙ ናቸው። ይህ አንደምታው ከባድ ነው።"

ምንም እንኳ አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች በዘር ሊተላለፉ የሚችሉ ቢሆኑም፣ በቤተሰባቸው የካንሰር ተጠቂ ታሪክ የሌለባቸውም ወጣቶችም እየመጡ ነው።

አይሊን በእነዚህ ወጣቶች ላይ የሚታየው የካንሰር ዕጢ በ70ዎቹ ዕድሜ ላይ ካሉ ሰዎች በላይ ከባድ እና አደገኛ ነው ይላሉ።

"ለእኛም ለእነሱም አስገራሚ ነገር ነው። አንድ የ40 ዓመት ወጣት እንዴት እንዲህ ያለ ካንሰር ሊያጠቃው/ሊያጠቃት ይችላል?"

የካንሰር ተመራማሪዎች ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው የሚለውን ለማጥናት ደፋ ቀና እያሉ ነው። የላንሴት ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በካንሰር ላይ የተሠራውን ሥራ የሚያወድም እና ወደፊት ከፍተኛ የጤና መቃወስ የሚያመጣ ነው።

ኮምፒውተር ፊት ተቀምጣ ምግብ የምትበላ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አመጋገብ እና ከልክ ያለፈ ውፍረት ለካንሰር ክስተት አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው

ለዚህ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ለመጣው የጤና ዕክል ቀዳሚ ምክንያት ተደርገው የሚወሰዱት ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና የምግብ አወሳሰድ ናቸው።

በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ18 እስከ 40 ባለው ዕድሜ ውስጥ ከመጠን ያለፈ ውፍረት መኖር ለ18 የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች ሊያጋልጥ ይችላል።

በላንሴት መፅሔት የወጣው ጥናት ደግሞ በተለይ በአሜሪካ 10 የካንሰር ዓይነቶች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ጋር የሚያያዙ ናቸው ይላል። የጉበት፣ የኩላሊት እና የጣፊያ ካንሰር ከእነዚህ መካከል ይመደባሉ።

የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሹጂ ኦጊኖ ይህ ሁኔታ "ሕይወታችንን የምንመራበት መንገድ መለወጥ እንዳለበት ይጠቁማል" ይላሉ።

"አንዳንዶቻችን በዘር በካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ዝቅተኛ ቢሆንም ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ ለካንሰር ሊያጋልጠን ይችላል። ስኳር እና የታሸገ ምግብ አብዝቶ መጠቀም የግሉኮስ መጠን እንደሚጨምር እናውቀዋለን። ይህ ደግሞ 'ለስኳር' በሽታ እና ለካንሰር ያጋልጣል።"

ነገር ግን የክብደት መጨመር ብቻ ለካንሰር መስፋፋት ምክንያት ሊሆን አይችልም። አይሊን እንደሚሉት አብዛኞቹ የጣፊያ ካንሰር ተጠቂዎች ጤናማ እና የተስካከለ ቁመና ያላቸው ናቸው።

ከዚህ ቀደም ትምባሆ ማጨስ ለካንሰር እንደሚያጋልጥ በስፋት ቢነገርም የትምባሆ አጫሾች ቁጥር እጅጉን ቀንሷል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ2000 ከሦስት አንድ የነበረው የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁን ከአምስት አንድ ሆኗል።

ተኝታ ስልኳን የምትመለከት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለሰው ሰራሽ ብርሃን አብዝቶ መጋለጥ ከካንሰር ክስተት ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል አጥኚዎች ይናገራሉ

ፕሮፌሰር ኦጊኖ እንደሚያምኑት የእንቅልፍ መዛባት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከአውሮፓውያኑ 1905 እስከ 2008 ባለው ጊዜ በአዋቂዎች እና በሕፃናት ዘንድ የእንቅልፍ መጠን በ60 ደቂቃ ቀንሷል።

በአውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ አውሮፓ እና አሜሪካ 'የሺፍት' ሥራ እየተለመደ መጥቷል። በ2021 የወጣው የእንግሊሽ ሎንግቲውዲናል ጥናት እንደሚጠቁመው እንቅልፍ ማጣት እና ካንሰር ግንኙነት አላቸው።

አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ለሰው ሰራሽ ብርሃን ለምሳሌ ለኤልክትሮኒክስ ዕቃዎች ብርሃን መጋለጥ ከጡት፣ ከአንጀት እና ከማህፀን ካንሰር ጋር ግንኙነት አለው። ይህ የሚሆነው ሰው ሰራሽ ብርሃን የሆርሞን ሜላቶኒንን መጠን ስለሚቀንሰው ነው።

"ከልጅነታችን ጀምሮ ለሰው ሰራሽ ብርሃን እንጋለጣለን" ይላሉ ኦጊና። በተለይ በጃፓን 24 ሰዓት ሙሉ በሥራ ማሳለፍ የተለመደ ሆኗል።

ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት ሰው ሰራሽ ብርሃን ብቻውን ለካንሰር ተጋላጭነት ተጠያቂ ባይሆንም ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ ለካንሰር የመጋለጥ ዕድላችንን ከፍ ሊያደርገው ይችላል።

ተመራማሪዎች ከዚህ በተጨማሪ ለጥቃቅን የፕላስቲክ ምርቶች ቅንጣቶች መጋለጥ፣ አንቲባዮቲክስ መጠቀም ከውፍረት እና ከእንቅልፍ መዛባት ጋር ተዳምረው በወጣቶች ዘንድ የካንሰር በሽታ እንዲስፋፋ ምክንያት ሳይሆኑ አይቀሩም ይላሉ።

ሕክምና የምትከታተል ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቀድሞ ምርመራ ማድረግአስፈላጊውን ሕክምና ለማግኘት ይረዳል