ከዓለም አገራት ሴቶችን በሞት በመቅጣት ተወዳዳሪ የሌላት ኢራን

የፎቶው ባለመብት, Abdorrahaman Boroumand Center
*ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶች አሉት።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ኢራን በከፍተኛ ሁኔታ በሞት የመቅጣት ዘመቻ ላይ ናት። በሐምሌ ወር የመጨረሻ ሳምንት ብቻ 32 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል። ከነዚህ ውስጥ ሦስት ሴቶች ባሎቻቸቸውን ገድለዋል በሚል በስቅላት የተቀጡ ናቸው።
“ኢራን ውስጥ በግድያ ወንጀል ለተከሰሱ የእስራት ቅጣት የለም። ይቅርታ ማድረግ ወይም መግደል ነው ያለው አማራጭ” በማለት በአሜሪካ ተቀማጭነቱን ያደረገው አብዶራህማን ቦሩማንድ ማዕከል የተሰኘው የኢራን የሰብአዊ መብት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሮያ ቦሩማንድ ያስረዳሉ።
ምንም እንኳን ከኢራን በበለጠ የሞት ቅጣት ቁጥር ያለባቸው አገራት ቢኖሩም በዓለም ላይ ካሉ አገራት ሴቶችን በሞት በመቅጣት የሚወዳደራት አገር እንደሌለ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ አሃዛዊ መረጃ ያሳያል። ታዲያ ኢራን በዚህ ደረጃ ለምን ሴቶችን በሞት ትቀጣለች?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሞት ፍርድ
ባለፈው ሳምንት በስቅላት ከተገደሉት ሦስት ሴቶች በተጨማሪ ሌሎች ስድስት ደግሞ በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ መገደላቸውን የአብዶራህማን ቦሩማንድ ማዕከል መረጃ ያሳያል።
እውነት ነው በኢራን ውስጥ የሞት ቅጣት የሚፈጸመው በአብዛኛው በወንዶች ላይ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ ቁጥር ባለው ቅጣት ላይ የዘጠኙ ሴቶች መጨመር አሃዙን ከፍ ያደርገዋል።
“ከ2000 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 233 የሴቶች የሞት ቅጣት መዝግበናል” ሲሉ ቦሩማንድ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
አክለውም “106 ሴቶች በግድያ ወንጀል 96ቱ ደግሞ በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀሎች የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል” ብለዋል።
ሌሎች ቁጥራቸው አነስ ያሉ ሴቶች ደግሞ ከጋብቻ ውጪ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸማቸው ተገድለዋል ተብሎ ይታመናል።
ቦሩማንድ እንደሚሉት ከእነዚህ የሞት ቅጣቶች ውስጥ በይፋ የተገለጹት 15 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፣ ስለሌሎቹ የሞት ቅጣቶች የታወቀው ከፖለቲካ እስረኞች ወይም ከባለሥልጣናት እውቅና ውጪ መረጃዎችን ከሚያሾልኩ የሥራ ኃላፊዎች ነው።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ግድያ ወይም የሞት ቅጣት ቦሩማንድ እንደሚሉት በከፊል ከሕግ ሥርዓቱ ጋር የተያያዘ ነው።
በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት መንግሥት በነፍስ ግድያ ላይ የሞት ፍርድን ማቃለል አይችልም፤ ይቅርታ የመስጠት ውሳኔ የተጎጂዎች ቤተሰብ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እርዳታ የለም
ባለፈው ሳምንት ባለቤቷን በመግደል በሞት ከተቀጡት ሴቶች አንዷ የሆነችው የ40 ዓመቷ አፍጋኒስታናዊት ሳኑባር ጃላሊ በመጨረሻው ሰዓት ይቅርታ እንዲደረግላት ኢራናዊቷ አክቲቪስት አቴና ዴሚ ሞክራለች።
ዴሚ፣ ጃላሊ ይቅርታ እንዲደረግላት ከጃላሊ ባለቤት ቤተሰብ ጋር ለመደራደር ተስፋ አድርጋ ነበር።
“የተገደለውን ግለሰብ ቤተሰቦች ለማግኘትና ለመማፀን ብንሞክርም የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት አልረዱንም። ስልክ ቁጥራቸውን በመንግሥት ለተመደበው ለጃላሊ ጠበቃ ሰጥተው ነገር ግን ጥያቄያችንን ችላ አሉት” ስትል ዴሚ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“የእስር ቤት ባለሥልጣናት አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቡ የደም ካሳ ተቀብሎ ይቅርታ እንዲያደርጉ እና እርቅ እንዲወርድ ይረዳሉ። ነገር ግን ይህንን ሁልጊዜ ተግባራዊ አያደርጉትም።”
ነገር ግን ቦሩማንድ ከሌሎች ተሟጋቾች ጋር በመሆን ሁለት ሰዎችን ከግድያ እንዲሁም ሌሎች ስምንት ሰዎች የአካል ክፍልን ከመቆረጥ ቅጣት ያዳኑበትን አጋጣሚ በመጥቀስ የተወሰኑ ስኬቶችን ይጠቅሳሉ።
ከጃላሊ ጋር በተመሳሳይ ቀን ከተሰቀሉት ሁለት ሴቶች አንዷ ያለ ዕድሜዋ በ15 ዓመቷ ያገባች ግለሰብ ናት። ሌላኛዋ ሦስተኛዋ ግለሰብ ባሏን በመግደል በቁጥጥር የዋለችው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Atena Daemi
ደካማ መከላከያ
ዴሚ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነቷና በምታደርገው እንቅስቃሴ ሰባት ዓመታትን በእስር አሳልፋለች።
የሴቶች ማረሚያ ቤቶች መሠረታዊ መገልገያዎች እንደሌላቸው እና እስረኞች አንዳንድ ጊዜ እንደሚደበደቡ ትናገራለች።
በአገሪቱ ዳኛ የሚሆኑት ወንዶች በመሆናቸውና በአብዛኛውም ጠበቆች እንዲሁም ወንዶች ስለሆኑ ሴቶች በፍርድ ቤቶች ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ አይዳኙም።
የኢራን ፍርድ ቤቶች ተከላካይ ጠበቃ ማቅረብ አለባቸው፣ ነገር ግን ዴሚ እንደምትለው “ከእነዚህ የተመደቡት ጠበቆች መካከል ብዙዎቹ የቀድሞ ዳኞች ወይም ዐቃቤ ሕግ ስለሆኑ ብዙም የሕግ ድጋፍ አይሰጡም” በማለት ታስረዳለች።
“በነፍስ ግድያ ወንጀል ገዳይ ተብለው የተፈረጁ ሰዎች ራሳቸውን ንጹህ ነን ብለው መከላከል ቀላል አይደለም። እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ የተጎጂው ቤተሰብ አባላት ከተከሳሹ ቃል የበለጠ ከፍ ያለ ስፍራ ይሰጣቸዋል” ትላለች ዴሚ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጾተኝነት ሥርዓት
በአሁኑ ወቅት በኖርዌይ ነዋሪነቷን ያደረገችው ኢራናዊቷ ጋዜጠኛ አሲዬ አሚኒ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ሴቶች ጉዳይ በቅርበት ተከታትላለች። አሲዬ የችግሩ መንስኤ ራሱ የሕግ ሥርዓቱ ነው ትላለች።
“በሕጉ መሠረት ወንዶች የቤተሰብ አባላት ማለትም፣ አባት እና ወንድ አያት የቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው። እነዚህም ወንዶች ጋብቻን ጨምሮ የሴት ልጆችን ዕጣ ፈንታ መወሰን ይችላሉ” በማለት አሚኒ ለቢቢሲ ታስረዳለች።
በዚህም መሠረት በወንዶች ቤተሰቦቻቸው አማካኝነት እንዲያገቡ የተገደዱ ታዳጊዎች የቤት ውስጥ ጥቃትን ጨምሮ ከባድ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ እንዲሁም የኢራን ፍርድ ቤቶች ፍቺም እንደማይፈቅዱላቸው ትናገራለች።
የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሴቶች ብዙውን ጊዜ የወላጆቻቸውን ድጋፍ እንኳ ያጣሉ።
“በዚህ ሁኔታ አንዳንድ ሴቶች የጥቃት ሰለባ ሆነው ይቆያሉ” ትላለች አሚኒ።
ሌሎች ደግሞ ባሎቻቸውን ለመግደል ያስባሉ።
“ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ ግድያውን የፈጸሙት ራሳቸው ወይም አንድ ሰው እንደረዳቸው አምነዋል። ነገር ግን ሁሉም ማለት ይቻላል እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችልና ድጋፍ ቢኖራቸው የግድያ ወንጀል አንፈጽምም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል” ብላለች አሚኒ ለቢቢሲ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታዳጊዎች ግድያ
በበርካታ ወንዶች ተደጋጋሚ የመደፈር ጥቃት የደረሰባት አቴፈህ ሳህሌህ የተባለች የ16 ዓመት ታዳጊ በፍርድ ቤት ጉዳይዋ የታየበትን መንገድ ዋቢ በማድረግ አሚኒ ኢ-ፍትሃዊነትን ታስረዳለች።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ለዚህች ታዳጊ መደፈር ፍትህ ከመጠየቅ ይልቅ ዳኞቹ በአውሮፓውያኑ 2004 ከጋብቻ ውጪ ግንኙነት እንደፈፀመች ወስነዋል።
“ታዳጊዋ ብትደፈርም ከአንዳንድ ወንዶች ጋር ወሲብ እንደፈፀመች በመናዘዟ የሞት ፍርድ ተፈርዶባታል” ትላለች አሚኒ።
በኢራን እስላማዊ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ያላገባ ወይም ያላገባች ግለሰብ ከጋብቻ ውጪ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀማቸውን ከተናዘዙ የ100 ጅራፍ ግርፋት እንደሚቀጡ ገልጻለች። ይህ ድርጊት ሦስት ጊዜ ከተደጋገመ፣ በአራተኛው ሞት ሊፈረድባቸው ይችላል።
“በአቴፌህ ጉዳይ ግን ይህ ኢሰብአዊ ሕግ እንኳን አልተተገበረም። ምክንያቱም ዳኛው እንድትገደል ከመወሰናቸው በፊት ሁለት ጊዜ ብቻ 100 ጅራፍ ነው የተገረፈችው” ትላለች አሚኒ።
ሃጂ ረዛኢ የተባሉት ዳኛ በስቅላት እንድትገደል ወሰኑ።
የበቀል ስሜቱ በዚህ ብቻ አያበቃም።
የፀረ ሞት ቅጣት ተሟጋች ናርጅስ መሐመዲ፣ ባሏን በመግደል ወንጀል የተከሰሰች ሴት ግለሰብ ልጅ፣ እናቱ በገመድ የሞት ቅጣት ሲከናወንባት የተረገጠችበትን ዱካ ከእግሯ ሲያነሳ የሚያሳይ ቪዲዮ አጋርታለች።
ልጅየው በአባቱ ቤተሰቦች “የቤተሰቡን ክብር” ለመመለስ በሚል ከፍተኛ ጫና እንዳደረጉበት ናርጅስ ታምናለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማስፈራሪያ መሣሪያ
አሚኒ በሕግ፣ በፍርድ ቤት እና በባህል ውስጥ ያለው መድልዎ “እነዚህን ሴቶች ወንጀለኞች ወይም ተጎጂ እንዲሆኑ ይገደዳሉ” ስትል ምሬቷን ትናገራለች።
ነገር ግን ሴቶቹን በሞት ለመቅጣት ያለው ችኩልነት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለችም።
“በተለያዩ ከእስር ቤቶች ያሉትን የእነዚህን ሴቶች ጉዳይ ስከታተል የኢራን መንግሥት ከእንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት እንዴት እንደሚጠቅም ባሳለፍኳቸው ዓመታት ውስጥ ፈጽሞ አልገባኝም” ትላለች።
ቦሩማንድ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አላቸው።
የኢራን እስር ቤቶች በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም በአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች ተጨናንቀዋል።
እስር ቤቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ባለሥልጣናቱ ውሳኔያቸውን እንዲያፋጥኑ በተገደሉ ግለሰቦች ዘመዶች ላይ ጫና እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።
ይህም ምሕረት እንዲያደርጉ ወይንም የሞት ቅጣት እንዲመርጡ ማለት ነው።
ይህም ሁኔታ በርካታ የሞት ቅጣት እንዲፈጸም ምክንያትም ሆኗል ይላሉ።
ባለሥልጣናቱ ለዚህ ከፍተኛ ቅጣት ስውር ምክንያት እንዳላቸውም ይጠረጥራሉ።
“በቅርብ ጊዜ ቴህራን ውስጥ የአንድ ሰው እጅ ተቆርጧል። ከሌሎች ከተሞች እስረኞችን እያመጡ አካላቸውንም እየቆረጡ ነው” ይላሉ።
“እነሱ በይፋ በሚዲያቸው ላይ እየገለጹት አይደለም። ነገር ግን ስለ ቅጣቱ መረጃ ወደ ሰፊው ሕብረተሰብ እንዲገባ እና በተሟጋቾች ላይ ፍርሃት እንዲፈጠር በሚያስችል መንገድ እያከናወኑት ነው” በማለት ያስረዳሉ።
**የኢራን መንግሥት ለቢቢሲ ጥያቄዎች ምላሽ ባይሰጥም ነገር ግን የኢራን የፍትህ አካላት ቅጣቱ ሕጋዊ እና የኢራንን ዓለም አቀፍ ግዴታዎችና የተፈረሙ ስምምነቶች የማይጥስ ነው ሲል ቀደም ሲል አስታውቋል። የኢራን መንግሥት እንግልት ይፈፅማል የሚሉ ሪፖርቶችን እና የግዳጅ ኑዛዜዎችን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።












