የቤት እንስሳትን እና ባለቤቶቻቸውን ለማሰር የተዘጋጀችው አገር

ውሻ ከአሳዳጊው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"በመልካም እና ውብ ዐይኖቹ ያየኛል። ወጣ ብለን ዞር ዞር እንድንል እየጠየቀኝ ነው። ግን ማድረግ አንችልም። ምክንያቱም ሁለታችንም እንታሰራለን።"

ማህሳ የቴህራን ነዋሪ ናት። በከተማው የቤት እንስሳትን እና ባለቤቶቻቸውን በቁጥጥር ሥር ማዋል እየተለመደ መሆኑን ትጠቁማለች።

የኢራን ርዕሰ መዲና ፖሊስ፣ በከተማዋ ፓርኮች ውስጥ ውሾችን ይዞ መንቀሳቀስ "ወንጀል" መሆኑን በቅርቡ አስታውቋል።

ይህንንም "የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ" ሲባል የተደነገገ የሚል ምክንያት ሰጥቶታል። 

ከወራት ክርክር በኋላ የኢራን የሕዝብ እንደራሴ የቤት እንስሳት ባለቤትነትን የሚገድበውን እና የእንስሳት ጥበቃ ሕዝባዊ መብት ሲል የሰየመውን ሕግ በቅርቡ ያፀደቀው ይሆናል።

ቅጣቶች

አዲስ በታቀደው ሕግ መሠረት የቤት እንስሳት ባለቤትነት ለመሆን በልዩ ኮሚቴው የተሰጠ ፈቃድ ማግኘት ይገባል።

ሕጉ እንደ ድመቶች፣ ኤሊዎች እና ጥንቸሎች ያሉ የቤት እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን "በማስመጣት፣ በመግዛት እና በመሸጥ፣ በማጓጓዝ እና በማቆየት" በትንሹ 800 ዶላር የሚደርስ ቅጣት ያስቀምጣል።

"በዚህ ረቂቅ ሕግ ዙሪያ ክርክሮች የጀመሩት ከአስር ዓመታት በፊት ኢራናውያን የሕዝብ እንደራሴዎች ሁሉንም ውሾች በመውረስ ለእንስሳት ፓርኮች እንዲሰጡ ወይም በረሃ ውስጥ እንዲጣሉ ሕግ ለማስተዋወቅ ሲሞክሩ ነው" ሲሉ የሕጉ ተቃዋሚና የኢራን የእንስሳት ሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓያም ሞሄቢ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሞሄቢ አክለውም "ባለፉት ዓመታት ይህንን ሁለት ጊዜ ቀይረውታል። የውሻ ባለቤቶች ላይ ስለሚጣለው አካላዊ ቅጣትም ተወያይተዋል። ግን የትም ሊደርስ አልቻለም” ብለዋል።

የኢራን የከተሜነት መገለጫ

ውሾችን ማሳደግ በኢራን ገጠራማ አካባቢዎች የተለመደ ነበር። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ እንስሳት የከተማ ሕይወት ምልክትም ለመሆን በቅተዋል።

ኢራን በ1948 የእንስሳት ደኅንነት ሕግን ካፀደቁ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አንዷ ነበረች።

መንግሥትም የእንስሳት መብትን ለመደገፍ የመጀመሪያውን ተቋም በገንዘብ ጭምር ደገፈ። የአገሪቱ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ጭምር ውሾች ነበራቸው።

ነገር ግን እአአ በ1979 የተካሄደው የኢራን ኢስላማዊ አብዮት ሁሉን ነገር ለዋወጠው። 

እንስሳቱ በእስልምና እንደ ርኩስ ይቆጠራሉ።

አዲሱ አገዛዝ ውሾችን “የምዕራባዊነት” ምልክት ስላደረገ፤ ባለሥልጣናት እንስሳትን ለማስቆም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

ነዋሪነታቸው በቴህራን የሆኑት የእንስሳት ሐኪሙ ዶ/ር አሽካን ሸሚራኒ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የውሾች ባለቤት ለመሆን ደንብ አልወጣም።

"ሰዎች ውሾቻቸውን ይዘው በእግር ጉዞ ሲያደርጉ አልፎ ተርፎም በመኪናቸው ይዘው ሲዞሩ፤ የምዕራባዊነት ምልክተት ተደርገው ስለሚታዩ በፖሊሶች ሊያዙ ይችላሉ” ይላሉ።

የእንስሳት ሐኪም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውሻ እስር ቤቶች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“አልፈው ተርፈው ለእንስሳት እስር ቤት ፈጠሩ። ስለ እስር ቤቶቹ ብዙ አስፈሪ ታሪኮችን ሰምተናል" ሲሉ ሐኪሙ አክለዋል።

"የውሾቹ ባለቤቶች ብዙ ዓይነት የሕግ ችግሮች ገጥሟቸው በሚንከራተቱባቸው ቀናት እንስሳቱ ያለ በቂ ምግብ እና ውሃ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ይቀመጡ ነበር” ብለዋል።

ለዓመታት የዘለቀው የምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ያስከተተለው የኢራን ኢኮኖሚያዊ ችግር በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ውስጥም የራሱን ሚና ተጫውቷል።

የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ባለሥልጣናት ከሦስት ዓመታት በላይ የቤት እንስሳት ምግብ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ አግደዋል።

ይህም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር አድርጓል። በተለይም የጥቁር ገበያ እንዲፋፋም ምክንያት ሆኗል።

በማሽሃድ ከተማ የእንስሳት ሕክምና ክሊኒክ ባለቤት የሆኑ ግለሰብ "እኛ በድብቅ ምግብ በሚያስገቡ ሰዎች ላይ ጥገኛ ሆነናል። ዋጋዎቹ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበሩት አምስት እጥፍ ጨምረዋል” ብለዋል።

በአገር ውስጥ የሚመረቱ የቤት እንስሳት ምግቦች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም ይላሉ።

"ጥራቱ በጣም ደካማ ነው። ፋብሪካዎች ርካሽ ሥጋ ወይም ዓሣ ይጠቀማሉ። አንዳንዴም የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ግብዓቶች ይጠቀማሉ።”

አዲሱ ሕግ ውሾች ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። ድመቶችም በእንስሳቱ ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል። አዞዎችም ይገኙበታል።

ኢራን በዓለም ላይ በጣም ዝነኛ ከሆኑት የድመት ዝርያዎች መካከል አንዱ የሆኑት የፋርስ ድመቶች መገኛ በመባል ትታወቃለች።

“አስቡት እስኪ የፋርስ ድመቶችም ጭምር በትውልድ ቀዬያቸው ስጋት ውስጥ ናቸው" ሲሉ በቴህራን የሚኖሩ የእንስሳት ሐኪም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም "ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ምንም ዓይነት አመክንዮ የለም። ባለሥልጣናት ጠንካራ እጆቻቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ" ብለዋል። 

የኢራን የእንስሳት ሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሞሄቢ የታቀደውን ሕግ "አሳፋሪ" ሲሉ ይገልጹታል።

"ፓርላማው ሕጉን ካፀደቀው መጪው ትውልድ ድመቶች ድመቶች ስለሆኑ ብቻ፣ ውሾችም ውሾች ስለሆኑ ብቻ እንዲከለከሉ ሕግ በማውጣታችን ያስታውሱናል።”

እንደ ማሻ ያሉ የቤት እንስሳት ባለቤቶች ስለ ቤት እንስሳዎቻቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከልብ ይጨነቃሉ።

"ለልጄ ፍቃድ ለመጠየቅ አልደፍርም" ትላለች። 

" ማመልከቻዬን ባይቀበሉስ? መንገድ ላይ ልተወው አልችልም" ስትል ሐሳቧን ትቋጫለች። 

የፐርዥያ ድመት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images