የቻይናው መካነ አንስሳት 'ውሻውን ተኩላ ነው' በማለት ሲያስጎበኝ ነበር ተባለ

ተኩላ የተባለው ውሻ

የፎቶው ባለመብት, Beijing News

ከሰሞኑ በማዕከላዊ ቻይና የሚገኝ አንድ መካነ እንስሳት ብዙዎችን አስደንቋል። ይህም አንድ ውሻን ተኩላ ነው በማለት እያስጎበኘ ነው መባሉን ተከትሎ ነው።

ክስተቱ የተፈጠረው ሁቤይ በምትባለው ግዛት ውስጥ ዢንግዣውን የሚል መጠሪያ ያለው መካነ እንስሳት ውስጥ ነው።

ከሰሞኑ አንድ ጎብኝ በመካነ እንስሳቱ ውስጥ ወደሚገኘው የተኩላዎች ማደሪያን እያየ በነበረበት ወቅት ውሻ የሚመስል ተኩላ ያያል።

ሮትዊለር የተባለ የውሻ ዝርያ አይነት ያየው ይሄ ጎብኝ ጠጋ ብሎም "ውፍ ውፍ! ተኩላ ነህ?" ብሎ ሲጠይቀው የሚያሳይ አጭር ቪዲዮም በርካቶች ተጋርተውታል።

ይህም ሁኔታ ለብዙዎች ቀልድ መነሻ ሆኗል።

ቪዲዮውን የቀረፀው ሹ የተባለው ግለሰብ በተኩላው ማደሪያ ውሻ እንደተኛ ለፓርኩ ሰራተኞች ማሳወቁን ለቤጂንግ ኒውስ ተናግሯል።

የፓርኩ ሰራተኞች ተኩላው በዚያው ስፍራ ውስጥ ይኖር እንደነበርና አርጅቶም እንደሞተ ነግረውታል።

በፓርኩ ውስጥ እንደ ጠባቂ ሆኖ የሚያድገው ይህ ውሻ በተኩላው ማደሪያ ውስጥ በጊዜያዊነት እየኖረ መሆኑንም አንድ የፓርኩ ሰራተኛ ለአገሪቱ ሚዲያ ተናግረዋል።

ነገር ግን ሻይን ሲኤን የተባለው ድረ ገፅ በበኩሉ እንደዘገበው መካነ እንስሳቱ በከፍተኛ ሁኔታ በገንዘብ ድርቅ እንደተመታና ቦታውም በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲሰራ በቂ ጎብኝዎች የሉትም በማለት ሰራተኛው ጠቆም ማድረጋቸው ተዘግቧል።

ፓርኩ 15 ዩዋን አካባቢ ወይም 85 ብር አካባቢ የሚያስከፍል ሲሆን በቦታው አንበሶችና ነብሮችም አሉት ተብሏል።

ይህ ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ መወያያም ሆኗል። በርካታ የሲና ዊቦ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሁኔታውን "አስቂኝ"፣ "አስደንጋጭ"ና "አሳዛኝም" ብለውታል።

አንዳንዶችም "ከተኩላ ጋር ቢያንስ የሚመሳሰል የውሻ ዝርያ አያስመጡም ነበር" በሚል አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ።

ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2019 በጅዩፈንግሻን ፎረስት ፓርክ ውስጥ አንድ ውሻ ተኩላ ነው ተብሎ ሲጎበኝ እንደነበርም ተዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አህዮች ቀለም እየተቀቡ የሜዳ አህዮች እየተባሉ እንደሚጎበኙም ተነግሯል።