ትግራይ፡ "እኛ መንግሥት ነን፤ ምን እያደረክ እንደሆነ እናውቃለን"

የቢቢሲው ዘጋቢ ግርማይ ገብሩ በቅርቡ በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች መካከል ሲሆን ስለተፈጠረው ነገር በአንደበቱ እንዲህ ሲል ያስረዳል።
በቁጥጥር ስር የዋልኩት በልደቴ ዕለት አመሻሽ ላይ ነበር።
በወቅቱ ከጓደኞቼ ጋር እንደተለመደው ሰኞ ዕለት እየተጨዋወትን ነበር።መሳሪያ የታጠቁት ወታደሮች ቡና የምጠጣበትን ቤት በድንገት ሲከቡ ምናልባት ሌላ ሰው ፈልገው ነበር የመሰለኝ።
አንድ ወታደር መጣና ተረጋጉ ሲለን ወደጨዋታችን ተመለስን። ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የሲቪል ልብስ የለበሱ የደኅንነት አባላት ቀረቡን።
"ማን ናችሁ?'' ሲል አንደኛው ጮኽ።
"ስማችሁን ንገሩን!"
"እኔ ግርማይ ገብሩ እባላለሁ'' አልኩኝ።
ያልጠበኩት ነገር ሆነ።
"በትክክል፤ ስንፈልግ የነበረው አንተን ነው" ከዚያም ከጓደኞቼ ጋር ወደውጪ እንድንወጣ ተደረግን።
በርካቶች በአግራሞት ሲመለከቱን የነበረ ሲሆን የቀበሌ መታወቂያዬንና የቢቢሲ መታወቂያዬን ሰጠኋቸው። ወዲያው አንደኛው የደኅንነት አባል ፊቴ አካባቢ በጥፊ መታኝ።
አንድ ወታደር በመሀል ጣልቃ ገባና እንዲተወኝ ነገረው። ከዚያም ወደ መኪና ጫኑኝ። ሁሉም ነገር በፍጥነት እየተከናወነ ስለነበር ለምን እንደወሰዱን እንኳን ለመጠየቅ ጊዜ አላገኘንም።
በከተማው በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ከደረስን በኋላ እንኳን ማንም ስለምንም የነገረን አልነበረም።

የትግራይ ግጭት
- • ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ግጭቱ ተጀመረ
- የህወሓት ወታደሮች የፌደራሉን ወታደራዊ ካምፕ ማጥቃታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ ጀመረ
- በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዱ
- ኢንተርኔትና የስልክ መስመሮች ተቋርጠው የነበረ ሲሆን ጋዜጠኞችም ቢሆኑ ወደ ክልሉ ገብተው መዘገብ አልቻሉም ነበር
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ኅዳር ወር ላይ ጦርነቱ እንዳበቃ ቢናገሩም ግጭቱ ግን ቀጥሏል
- በክልሉ ግጭቱን ተከትሎ ሰብአዊ መብቶች እንደተጣሱ የሚሰጋ ሲሆን ሰብአዊ ቀውሱም ከፍተኛ ነው

ነገር ግን ከደኅንነት አባላቱ አንደኛው ቀረብ ብሎ "ግርማይ እኛ መንግሥት ነን፤ እናም በየቀኑ የምታደርገውን በሙሉ እናውቃለን። ምን እንደምታወራ፣ ምን አይነት መልዕክቶች እንደምትልክ እናውቃለን። ቁርስ፣ ምሳና እራትህን ምን እንደምትበላም እናውቃለን'' አለኝ።
"ምን ሳደርግ እንደነበር እስቲ ንገረኝ'' አልኩት። "ምን አይነት መልዕክቶችን ስልክ እንደነበር ንገረኝ።''
ጥቅምት ላይ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለቢቢሲ ምንም አይነት ዘገባ ሰርቼ አላውቅም። በወቅቱ ለደኅንነቴ ተብሎ ዘገባዎችን እንዳልሰራ ተነግሮኝ ነበር።
"ምን ስትል እንደነበርና ምን ስታስብ እንደነበር የምትነግረን አንተ ነህ። በኋላ ላይ ትነግረኛለህ" አለኝ።
አንድ የስልክ ጥሪ ብቻ
ይሄ ምርመራ ሳይሆን ማስጠንቀቂያ ነው።
መጀመሪያ ላይ የሁላችን ስልክ ተወስዶብን የነበረ ሲሆን አንድ ወታደራዊ ኃላፊ ግን ስልካችንን መለሰልንና አንድ ጊዜ እንድንደውል ነገረን።
ልክ ለባለቤቴ ደውዬ ስለሆነው ነገር ስነግራት በጣም ደንግጣ ነበር። ነገር ግን ደህና እንደሆንኩ እና ምንም እንዳታስብ ነገርኳት።
በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ ካሉት ሌሎች ሰዎች ከሞላ ጎደል በተሻለ መልኩ ነበር የተስተናገድነው። ነገር ግን ስድስታችንም የምንተኛው በአንድ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ ነበር። ለመጸዳጃ ደግሞ የፕላስቲክ ኮዳ ነበር የሚሰጠን።
ሁላችንም በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስረላላወቅን በጣም ደንግጠንና ግራ ተጋብተን ነበር። እኔ መተኛት አልቻልኩም።
ጠዋት ላይ የደኅንነት አባላቱ መጥተው እቤቴ በመሄድ ብርበራ ማድረገው እንደሚፈልጉና በላፕቶፔ እና በስልኬ ውስጥ መረጃ ካለ ማጣራት እንደሚፈልጉ ነገረኝ። ነገር ግን ቤቴን አልፈተሹም ነበር።
የሚፈልጉት መረጃ በሙሉ ጭንቅላቴ ውስጥ ስለሚገኝ በጥያቄ ምርመራ ሊያደርጉብኝ እንደሚፈልጉም ነገሩኝ።
ነገር ግን እስከዚያ ሰዓት ድረስ ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋልን አልነገሩንም ነበር።
ምንም ይሁን ምን የፈጸሙኩት ጥፋት እንደሌለ ግን እርግጠኛ ነበርኩ።
"እኔ ጋዜጠኛ ነኝ። ነጻ ሰው ነኝ፤ እናም የፈለጋችሁትን ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ'' አልኩኝ።
ነገር ግን ማንም አልጠየቀኝም። እንደውም ማክሰኞ ጠዋት ላይ መቀለ መሀል ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን። ሁኔታው እዚያ የከፋ ነበር።
አልጋ የሌለበት አንድ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ። ክፍሏ 2.5 ሜትር በ3 ሜትር ትሆናለች፤ በውስጧ ግን ሌሎች 13 ሰዎች ነበሩ። በጣም ይሞቅ ነበር፤ በአቅራቢያ ከነበረው የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ማጠራቀሚያ የሚመጣው ሽታ ደግሞ ነገሮችን በጣም ከባድ አደረገው።
"የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እሰጥ ነበር''
ምናልባት ሌሊት ላይ መጸዳጃ ቤት መሄድ ካስፈለገን ተብሎ አሁንም የፕላስቲክ ኮዳ ተሰጠን። ነገር ግን ቀኑን ሙሉ የበላሁት አንዲት ብርቱካን ስለነበረች ኮዳው እንደማያስፈልገኝ ገብቶኝ ነበር።
ከበስተግራዬ በኩል አንድ ሰው ያስል ስለነበር ኮሮናቫይረስ እንዳይዘኝ ሰግቼም ነበር። እንደ እድል ሆኖ የት እንደምገኝ የሰሙ ጓደኞቼ ያለሁበት ድረስ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም ሳኒታይዘር አመጡልኝና በክፍሉ ለነበሩት በሙሉ አከፋፈልኩኝ።
ረቡዕ ጠዋት ላይ አንድ ፖሊስ ተጠግቶኝ እቃዎቼን እንደሰብስብና ወደቤቴ መሄድ እንደምችል ነገረኝ።
ነገር ግን ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋልኩ ምንም አይነት ማብራሪያ አልተሰጠኝም ነበር። ቢቢሲም ቢሆን ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋልኩ መንግሥትን እንደጠየቀ አውቃለው።
እኔ ወደቤት ስመለስ ባለቤቴ፣ እናቴ እና ልጆቼ አንድ ላይ ነበሩ። በደስታ ሲያለቅሱ አየኋቸው።
በጣም ያሳሰበኝ ነገር ፖሊስ ጣቢያ እያለሁ እንዳልታመም ነበር። አሁን ተረጋግቻለሁ፤ ትንሽ እረፍት እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ።












