ትግራይ፡ የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቋም መያዙ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አንድ አይነት አቋም መያዙን የአስተዳደሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ካሳ እንዳሉት የኤርትራ ሠራዊት በክልላቸው ውስጥ እንዳለ ከመግለጻቸው በተጫማሪ "በክልሉ ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል። ወንጀሎችንም ፈጽመዋል" ሲሉ ከስሰዋል።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የኤርትራ ሠራዊት በክልሉ ውስጥ እንደሚገኝ ቢገልጹም የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት ጉዳዩን ሲያስተባብሉ መቆየታቸው ይታወሳል።
የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ መኖራቸውን በተመለከተ "ሕዝቡ በዓይኑ ያየው እውነታ ነው" ያሉት አቶ ገብረ መስቀል፤ "ስለዚህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወታደሮቹ ከክልሉ መውጣት አለባቸው ሲል አቋም ይዟል" በማለት በአንድ ድምጽ መወሰናቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት ትግራይ ውስጥ ይገኛሉ ያላቸውን የኤርትራ ወታደሮችን የአማራ ክልል ኃይሎች እንዲወጡ የጠየቀ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ተወያይተዋል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአገሪቱ መከላከያ ኃይል እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።
ከዚያ በኋላም ጠቅለይ ሚኒስትር ዐብይ በክልሉ እየተካሄደ የነበረው "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ መጠናቀቁን አስታውቀው ነበር።
ነገር ግን ከዚያ በኋላም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆኑን የዓለም አቀፍ ተቋማት የገለፁ ሲሆን ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሱዳን ሲሰደዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ የእለት ምግብ እርዳታ እየተሰጣቸው ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በትግራይ ክልል ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን አረጋግጦ፤ በአክሱም ከተማ ውስጥ በወሰዱት እርምጃ ከ200 በላይ ሰዎችን ገድለዋል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የጽህፈት ቤት ኃላፊው በአማራ ክልል ኃይሎች የክልሉ ግዛቶች መያዛቸውን ገልጸው፤ ይህንንም በተመለከተ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግልጽ አቋም እንዳለው አመልክተዋል "አስተዳደሩ ህወሓት ያስተዳድረው ከነበረው ግዛት በሴንቲሜትር የቀነሰ ክልልን አያስተዳድርም" ብለዋል።
አቶ ገብረ መስቀል እንዳሉት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጸውን የትግራይ ክልልን እንደሚያስተዳድር ገልጸው፤ "እነዚህን ቦታዎች ከሕግ ውጪ የያዙ ኃይሎች የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እየተጻረሩ ነው" ብለዋል።
አጠቃላዩ ምዕራባዊ የትግራይ ክፍል እንዲሁም በደቡብ አላማጣ፣ ኮረምና ሌሎች የገጠር አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ስር መሆናቸውን አመልክተው፤ ይህንንም ለፌደራል መንግሥቱ ሪፖርት ተደርጎ ኃይሎቹ ከአካባቢዎቹ እንዲወጡ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
"ግፊት የምናደርገው የተሰማራው ኃይል እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዎቹ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲቆሙና ፈጻሚዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ ነው" ሲሉ አቶ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ቀደም ሲል በተካሄደው የክልል አወቃቀር ወቅት ያለአግባብ ከግዛቱ ተወስደው ወደ ትግራይ የተካለሉ አካባቢዎች መኖራቸውን ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአድዋ ድል በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ መድረክ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ አገኘሁ ተሻገር ባደረጉት ንግግር "በወልቃይት ጠገዴ የተደረገው ውጊያ ማንነትን ለማረጋገጥ እንጂ መሬት ለመውረር አይደለም፤ ከዚህ በኋላ ነፃ ወጥተናል" ሲሉ ተናግረው ነበር።
የአማራ መገናኛ ብዙሃን ርዕሰ መስተዳደሩን ጠቅሶ እንደዘገበው "በማይካድራ፣ በሁመራ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በዳንሻ፣ በራያ፣ በአላማጣ፣ በኮረም እና በሌሎች አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ" በህወሓት አማካኝነት ተፈናቅለዋል ሲሉ ለሚቀርበው ክስ ምላሽ ሰጥተዋል።
በክልሉ ያጋጠመውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ተፈጽመዋል ከተባሉ ጥቃቶች መካከል በሴቶች ላይ የደረሰውን ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በተመለከተ መረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑን የተናገሩት አቶ ገብረ መስቀል "ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው መካከል በርካቶቹ ወደ ህክምና ተቋማት አልመጡም" ብለዋል።
አቶ ገብረ መስቀል ካሳ አክለውም "ሕግ ማስከበር የተባለው ወታደራዊ ዘመቻ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሏል" በሰዎች ላይ ሁሉም አይነት ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብለዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም በትግራይ ካለው የአስቸኳይ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አደጋዎችና ወንጀሎችን እንዲያስቆሙ ከፌደራል መንግሥቱና የፌደሬሽን ምክር ቤትን መጠየቁን ገልጸዋል።
ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መስተዳደር እንዲፈርስ መወሰኑ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ የተለያዩ ወገኖች ተሳታፊ የሆኑበት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ተደርጎ ክልሉን የማስተደደር ሥራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።















