ትግራይ፡ በአክሱም የሚጠቀሰው የሟቾች ቁጥር እኛ ከያዝነው በላይ ነው-አምነስቲ

የአክሱም ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአክሱም ከተማ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባካሄደው ምርመራ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ አስታወቋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአክሱም ሕዳር 19 እና 20 2013 ዓ.ም በሰብዓዊ ዜጎች ላይ ስለደረሰው ጭፍጨፋ ተቋማቸው ያወጣውን ሪፖርት በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።

ቢቢሲ-ላለፉት ሁለት ወይም ሶስት ወራት የአክሱም ፅዮን ቅድት ማሪያም ቤተ ክስርቲያን ውስጥ 750 ሰዎች ተገድለዋል የሚሉ ክሶች ነበሩ። ይህም በአመታዊው የንግስ ዕለት እንደነበር በተለያዩ ቡድኖች እና ሰዎች ተገልጿል። የእናንተ ሪፖርት በቤተ ክስርትያኑ ውስጥ ይህ ስለመፈፀሙ የሚያሳየው ነገር የለም። መረጃው ስህተት ነበር ማለት እንችላለን?

አምነስቲ- በማህበራዊ ሚዲያ በአክሱም ጽዮን ያለውን ጽላት የኤርትራ ወታደሮች ለመውሰድ ሲሞክሩ በተፈጠረ ግርግር የሰው ህይወት ጠፍቷል በሚል ሲሰራጭ የነበረውን መረጃ የሚያረጋግጥ መረጃ አላገኘንም። ይልቁንም ከተጠቀሰው ዕለት ቀደም ብለው ባሉት ሁለት ቀናት፤ ማለትም ኅዳር 19 እና 20 አስከፊ የተባለ ጭፍጨፋ መካሄዱን ነው ያረጋገጥነው።

ኅዳር 19 የተወሰኑ የህወሓት ሚሊሻዎች አክሱም ጽዮን ቤተ-ክርስቲያን አጠገብ ካለች አንድ ተራራ ወይም ጉብታ ላይ ወደ ኤርትራ ወታደሮች ላይ በከፈቱት ተኩስ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር። ይህ ካበቃ በኋላ እዛው የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ሌላ ተጨማሪ ኃይል እና የጦር መሳሪያ ተጨምሮ (ታንኮችን ጭምር) ጥቃት ሰነዘሩ። በመንገድ ላይ ያገኙትን እና በየቤቱ እያገቡ ያገኙትን ጎረምሳ ወንዶች ሲገድሉ እደነበረ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

በማግስቱም [ኅዳር 20] ይህ ድርጊት ቀጥሎ ነበር። አስከሬን ማንሳንትም አይቻልም ነበር። ኅዳር 21 2013 ዓ.ም. በአክሱም ጽዮን ክብረ በዓል ዕለት ነው እንዲቀበሩ የተደፈቀደው። ስለዚህ የነበረው ይሄ ነው። በ 21 ትልቅ ግድያ እንደነበረ የሚያስረዳ ነገር የለም፤ ይልቁንም አስከሬን መቅበር የተጀመረውም በእዛው ዕለት ነው።

ቢቢሲ-ስለዚህ ከዚህ ቀደም ከጽላቱ ጋር የተያያዘው መረጃ ትክክል አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል?

አምነስቲ- አዎ። አክሱም ጽዮን ላይ ከፅላቱ ጋር በተያያዘ ያለመግባባት እንደነበረ ነግረውናል። ብዙዎቹ ሰዎች የሚሉት ይህ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ ከነበሩት ቀናት በኋላ ነው ይህ ያለመግባባት የተከሰተው፤ ነገር ግን ወደ ግድያ አላመራም።

የቤተ-ክስርቲያኑ አባቶች ‹‹ወደ ቤተ-ክርስቲኑ የምትገቡ ከሆነ ደወል (መረዋ) እንደውላለን፤ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ ይወጣል፤ ይህም ትልቅ እልቂት ይፈጥራል›› በማለታቸው ሳይገቡ መቅረታቸውን ተረድተናል። እንግዲህ አክሱም ውስጥ ያሉ ብዙ ትልልቅ ሰዎችን ነው ያናገርነው።

ቢቢሲ-መረጃ እና ማስረጃዎቻችሁን የሰበሰባችሁበት ስልት እና ያመሳከራችሁበት ሂደት ምን ይመስል ነበር?

አምነስቲ- በቁጥር ብዙ ያለው ሰው ነው ያናገርነው። 23ቱ ሰዎች ከአክሱም ወደ ሱዳን ሸሽተው የገቡ ናቸው። በተለይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ፣ ዘረፋ እና ግድያ ሲካሄድ አክሱም ውስጥ የነበሩ እንዲሁም ቀብር ላይ የተሳተፉ ናቸው። ሌላው አክሱም ስልክ ሲከፈት 18 የሚሆኑ የሟቾች ቤተሰቦችን፣ የአክሱም ነዋሪዎችን እና ትልልቅ ሰዎችን አነጋግረናል።

በዚህም ሂደት በቅድሚያ የሟቾችን የስም ዝርዝር ሰብስበናል። ይህም አንዱን ከሌላው በማስተያየት ለማረጋገጥ ሞክረናል። ምንም እንኳን እኛ ያገኘነው የስም ዝርዝር 240 አካባቢ ቢሆንም ቁጥሩ ከዚህ ሊልቅ ይችላል።

ሌላው በተለያዩ ግዜያት የተወሰዱ የሳተላይት ምስሎችን ተጠቅመናል። በተለይም የከባድ መሳሪያ ድብደባዎችን እና ሰዎች የተቀበሩባቸውን ቤተ-ክርቲያናት ላይ አዳዲስ የመቃብር ቦታዎችን በእዛ ዕለት ላይ አሳይተውናል። ስለዚህ ይህንን ተጠቅመን ነው ለማረጋገጥ የሞከርነው።

ቢቢሲ-የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ራዊት አብረው የአክሱም ከተማን ተቆጣጥረዋል ይላል ሪፖርቱ። ይህ ኅዳር 10 ማለት ነው። ከዛ በኋላ ሪፖርቱ ስለ ኢትዮጵያ ራዊት የሚገልፀው ነገር የለም። ራዊቱ ድርጊቱን ለማስቆም ወይም በተቃራኒው ያደረገው ተሳትፎን የተመለከተ ማስረጃ አላገኛችሁም?

አምነስቲ- ባገኘው መረጃ መሠረት አብረው [የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠራዊት] ነው የተቆጣጠሩት። ከዛ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት እስከ ኅዳር 30 ድረስ አልታየም። ሙሉ በሙሉ የአክሱም ከተማ በቁጥጥር ስር የነበረው በኤርትራ ሰራዊት ስር ነበር።

የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማትን የኢትዮጵያ ወታደሮች እጅግ ባነሰ ኃይል ሆነው ሲጠብቁ እንደነበር ተረድተናል። በዋነኛነት የከተማውን ፀጥታ መቆጣጠር እና የማስተዳደር ስራ ይሰራ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት እንደነበር ነው እማኞች የነገሩን።

ስለዚህ በተለይ በ ኅዳር 19 እና ከዛ በፊት በነበሩት ግድያዎች እና ዘረፋዎች ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ተሳትፎ እንደነበራቸው የሚያሳይ ነገር አላየንም።

ቢቢሲ-የተቋማችሁ ጥናት መደምደሚያ ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ራዊት የአክሱም ከተማን ሲቆጣጠሩ የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል የሚል ነገር ተካቶበታል። የዚህ ጦርነት አንድ አካል የነበረው ህወሓትን የተመለከተ ግን ምንም መረጃ የለውም። ይህ ራዊት የፈፀመው የጦር ወንጀል የለም?

አምነስቲ- ይህ ጥናት የሚያስረዳው ስለ አክሱም ብቻ ነው፤ ይህ ማለት ሌላው አካባቢ ላይ የህወሓት ሠራዊት ወንጀል አልፈፀመም የሚል አይደለም። ነገር ግን በአክሱም ከተማ በህወሓት የተፈፀመ የጦር ወንጀል አላገኘንም።

ያም ሆኖ ግን የእኛ ትልቁ ጥረታችን እነዚህ ተፈጽመዋል የተባሉ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ ተፈፅመዋል የተባሉ ወንጀሎች ላይ አስፈላጊ የሆነው ምርመራ በተባበሩት መንግስታት ተመርቶ እንዲደረግ ነው። ያ ምርመራ ሲደረግ በተለይ በአካል ቦታው ላይ ሆነን ስንመረምር ተጨማሪ ማስረጃ ይገኝ ይሆናል። አሁን ባለን ማስረጃ መሠረት ግን አክሱም ላይ ያንን የሚያመለክት ማስረጃ አላገኘንም።

አምንስቲ ኢንተርናሽናል

የፎቶው ባለመብት, Amnesty

ቢቢሲ-በትግራይ ክልል ጦርነት ላይ የሚነሳ አንድ የም አቀፍ የጦርነት ሕግ ጥሰት ጉዳይ አለ። ይህም በሁለቱም ወገን የደንብ ልብስ የማይለብሱ የሚሊሻ ይል ተሳትፎ ነው።በዚህ ጦርነት ሰላማዊ ሰዎችን እና ከተዋጊዎች ለመለየት አስቸጋሪ አድርጎታል ይባላል። ይህ የእናንተ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰው ቁጥር እና ተግባራት ጫና እንዳያመጣ ምን ጥንቃቄዎች አድርጋችኋል?

አምነስቲ- ይህንን ከግምት ውስጥ ከተናል። ሚሊሻም ቢሆን አንድ አረንጓዴ ዩኒፎርም አላቸው። በነበረው ጦርነት ወቅት ልዩ ኃይሉም የራሱ መለያ ልብስ አለው። ነገር ግን የሞቱትን ሰዎች ስንመለከት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ህፃናቶች፤ ትልልቅ አዛውንቶች እና አልፎ አልፎም ሴቶች ከቤታቸው እየወጡ ነው የተገደሉት።

ያ ዩኒፎርም አላደረጉም ተብሎ የሚያስገድል ነገር የለውም። ዩኒፎርም አለማድረግ የዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግ ጥሰት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዩኒፎርም ስላላደረጉ ነው ሰላማዊ ሰዎችን የገደልነው የሚለው ድርጊቱን አሳማኝ አያደርገውም ወይም አያስተባብለውም። አንደኛው ወገን ሕጉን ሰላላከበረ እኔም ሕጉን አላከብርም የሚል ምክንያት ውጤት አያመጣም።

ቢቢሲ- ይህ ጥያቄ የተሰነዘረው የተፈጸመውን ድርጊ ያስተባብላል ሳይሆን ሲቪሎች ተብለው የተጠቀሱ የሟቾች ቁጥር ላይ እንዲሁም ድርጊቶች ላይ ጫና ካሳረፈ በሚል ነው። ከዛ አንፃር እንደ ውሱንነት ሊነሳ ይችላል?

አምነስቲ- እኛ በደንብ ማረጋገጥ የቻልነውን እና ስማቸውን ማግኘት የቻልነውን ሲቪሎችን ነው የጠቀስነው። ከዛ ውጪ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች ይኖራሉ። የሚጠቀሰው ቁጥር እኮ እኛ ከያዝነው የሥም ዝርዝር በላይ ነው። እኛ ከያዝነው የሥም ዝርዝር ውስጥ ሲቪል የለበሱ ተዋጊዎች ይኖሩ ይሆን የሚለውን ግን፤ እሱ ላይ እኛ ያረጋግጠነው ነገር የለም።

ቢቢሲ- የእናንተ ጥናት የተገደበበትን ሁለት ቀናት ተነስተን ስናሰላ አሁን ሶተኛ ወር ላይ ነን። ከዛ በኋላ በአክሱም ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? የኤርትራ ራዊት አሁንስ አክሱም አለ? ድረጊቱ ቆሟል? ከቆመስ እንዴት?

አምነስቲ- ጥቃቱ የቆመው የኢትዮጵያ ሠራዊት ለአክስም ጽዮን ክብረ በአል ወደ አክሱም ከጋዜጠኞች ጋር ሄዶ ነበር። በዛ ግዜ ነበር በዋነኝነት ጥቃቱ የቆመው። ከዛ አንድ ቀን ቀድሞ በ20 ሽማግሌዋች የኤርትራ ሠራዊት አዛዥን ሄደው ጥቃቱንም እንዲያቆሙ የሞቱትንም እንዲቀብሩ እንደለመኗቸው እና ይህም በእለቱ ለነበረው ድርጊት መቆም ድርሻ እንደነበረው ያለን ማስረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በጣም እንደደነገጡ የሚያሳይ ነገር አለ። ይህንን ተከትሎም ከአንድ ከሁለት ቀን በኋላ የአክሱም ከተማን ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ተረድተናል። ይሄ ማለት ግን አክሱም አካባቢ ግን ጥቃቶች አልነበሩም ማለት አይደለም።

ሪፖርታችን ላይ አላካተትነውም እንጂ አክሱም አካባቢ ላይ ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ እንደሆነ እና ያንን የሚፈጽሙት የኤርትራ ወታደሮች እንደሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። በዚህ ላይ ግን ብዙ ማለት አልችልም፣ ገና እየመረመርነው ስለሆነ።

ቢቢሲ-የጥናታችሁ ምክረ ሃሳቦች ሁለት ናቸው። አንዱ የኢትዮጵያ መንግት የትግራይን በሮች ይክፈት የሚል ነው። ከትላንት በስቲያ የጠቅላይ ምስትሩ / ቤት ይህንን መፍቀዱን የሚያሳይ መግለጫ ሰጥቷል። ይህ ከሪፖርታችሁ ጋር የሚገናኝ ይመስልዎታል?

አምነስቲ- የሪፖርታችንን ግኝት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከመታተሙ ቀድመን አጋርትናል፤ እሱን አይተውት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት እሱን መናገር አይልም። መንግሥት በተለይም 11 የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዲገቡ እና አንዲዘግቡ መፍቀዱን እና የተወሰኑትም እየሄዱ እንደሆነ እናውቃለን።

ይህ ጥሩ መሻሻል ነው። መሄዱ ብቻ ሳይሆን በነፃነት ተንቀሳቅሰው መረጃ እንዲሰበስቡ እና ሪፖርት እንዲያደርጉ አስፈላጊው ትብብር ሊደረግላቸው ይገባል እላለሁ።

ሌላው ሰብአዊ እርዳታ ለሚሰጡ ተቋማት ያለው የቢሮክራሲ ችግር ይታወቃል። በሱ ላይም እንደተባለው ለውጥ ተደርጎ ከሆነ ጥሩ ነው። ባለፈው በዚሁ ጉዳይ ላይ ትልቅ ዘመቻ አድርገን ነበር። ከዛ በኋላ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል፤ እንዲገቡ ተፈቅዷል ተብሎ ነበር። እነዚህ የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ግን ችግሩ እስካሁን እንደቀጠለ እየገለፁ ነው። ስለዚህ ያለው ሁኔታ ከተሻሻለ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ተከታትሎ የተባሉትን ነገሮች ተፈፅመዋል የሚለውን መከታተል ያስፈልጋል።

ቢቢሲ-ሪፖርታችሁ ለተፈጸመው ጭፍጨፋ ፈጻሚ ብሎ የጠቀሰው የኤርትራ ራዊትን ነው። በምክረ ሃሳባችሁ ላይ ግን ለኤርትራ መንግስት ምንም ምክረ ሃሳብ አላስቀመጣችሁም። የህግ ባለያ እንደመሆንዎ፤ ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ የሚሆነው ማነው?

አምነስቲ- ይህ ጥያቄ ውስብስብ ወደ ሆነ የሕግ ፅንሰ ሃሳብ ይወስደናል። ግን የሰብአዊ መብት ሕጎች ግዛት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በአንድ አገር የግዛት ወሰን ውስጥ ለተፈጸሙ ተግባራት ተጠያቂ የሚሆነው ግዛቱን የሚያስተዳደረው መንግሥት ነው። ይህ አንግዲህ ዋናው መርህ ነው። ግን ግዛቱ ላይ ሙሉ ቁጥጥር የማይኖርበት ጊዜ ይኖራል። ለምሳሌ የውጪ ወረራ ሲኖር ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት ሲኖር ያለው መንግሥት የተሟላ ቁጥጥር ወይም ስልጣን ሳይኖር ሲቀር የተቆጣጠረው አካል ተጠያቂ ይሆናል።

አሁን በምንነጋገርበት ጉዳይ ግን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት በጋራ በመሆን ህወሓትን የጋራ ጠላት አድርገው ነው እየተዋጉ የነበር። ስለዚህ የኤርትራ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ የገባው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን እና አንድ ላይ በመሆን ለመዋጋት ነው። በዚህ ምክንያት የኢትየጵያ ሠራዊት ውጤታማ ቁጥጥር አልነበረውም ማለት አይቻልም።

ስለዚህ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ስለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛ ሃላፊነቱን የሚወስደው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ስለዚህ አብሮት የሚዋጋውን የኤርትራን ሠራዊትም ቢሆን እነሱ በሚዋጉበት ግዜ የጦርነትንም ሆነ የሰብአዊ መብቶች ሕጎችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሃላፊነት የኢትዮጵያ መንግሥት ነው።

ቢቢሲ-ሪፖርቱ ሕብረተሰቡ ከህወሓት ወታደሮች ጋር እንደ ዱላ፣ ቢላ እና ድንጋይ ያሉ መሳሪያዎችን ተጠቀሞ የኤርትራ ራዊት ላይ ጥቃት ሰንዝሯል ይላል። ህወሓት የሰነዘረው ጥቃት ላይ የሲቪሎች ተሳትፎ ነበረው ?

አምነስቲ- የሲቪሎች ተሳትፎ ነበረው። በተለይ የማይኮው ጥቃት ላይ የተወሰኑ ወጣቶች የእጅ መሳሪያዎችን ይዘው ተሳትፈው ነበር። ያ ግን ስልጠናም ሆነ መሳሪያ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ሌላም ከአክሱም ነዋሪ ሲቪል ወጣቶች ለህወሓት ሚሊሻ ምግብ የማቅረብ ነገር ነበር። በወቅቱ በዚያ ምክንያት የተገደሉ ሰዎች አሉ፤ ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ቤት ለቤት እየሄዱ የመግደል ነገር ነበር።

ቤት ለቤት እየሄዱ ብሎም በየመንገዱ ያሉትንም የመግደሉ ነገር በዛ ምክንያት ይመስላል። የህወሓት ሠራዊትን ደግፈው ዱላ ይዘው ምግብ ስላቀረቡ የዛ ብቀላ የሚመስል ነገር አለ።

ቢቢሲ- እንዲህ ከሆነ ለምአቀፍ የጦርነት ሕጉ ተዋጊዎችን ከሲቪሎች የሚለይበት መንገድ አለ። በሪፖርታችሁ ለህወሓት ራዊት ምግብ ሲያቀርብ የነበረ ሰውን አነጋግራችኋል። በጦርነቱ ውስጥ አንዱን ቡድን በሎጂስቲክ ሲረዳ የነበረ ሰው እንደማነጋገራችሁ የሪፖርቱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ አይከተውም?

አምነስቲ- ይሄ ልጅ ከዛ ሁሉ ሰው አንድ ምስክርነት ነው። የሱ ምስክርነት አይደለም ሪፖርቱን የቃኘው። ሌሎች ሰዎችን አነጋግረናል፤ የበለጠ ሪፖርቱን ያቆሙት ሌሎቹ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ የሱ ምስክርነት የሪፖርቱ ተአማኒነት ላይ የሚያመጣው ነገር የለም።