ባይደን ከኬንያው ፕሬዝደንት ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ተነጋገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰሜን ኢትዮጵያ ስለተከሰተው ቀውስ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ከዋይት ሐውስ በወጣው መግለጫ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በስልክ በነበራቸው ወይይት፤ "በትግራይ ክልል እየተባባሰ ስለመጣው የሰብዓዊ ቀውስና የሰብዓዊ መብት ጥሰት" ተነጋግረዋል ብሏል።
መሪዎቹ በትግራይ "ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ መከላከልና የሰብዓዊ ድጋፍ መድረስ አስፈላጊነት ላይ" ተነጋግረዋል ሲል የዋይት ሐውስ መግለጫ አመልክቷል።
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ትናንት በነበራቸው ውይይት ከኢትዮጵያ ጉዳይ በተጨማሪ በአሜሪካና ኬንያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረዋል። ባይደን በቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከኬንያ ጋር አብሮ ለመስራት አሜሪካ ጽኑ ፍላጎት አላት ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን የኬንያን የአፍሪካ ቀንድ መሪነትን፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የጸረ-ሽብር እንቅስቃሴዋን እና በአየር ጸባይ ለውጥ ላይ እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
በተያያዘ ዜና የካናዳው ጠቅላይ ሚንሰትር ጀስቲን ትሩዶ ከጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ ጋር መወያየታቸውን የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።
ሁለቱ መሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በኢትዮጵያና በካናዳ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች እንዲሁም በወረርሽኙ መስፋፋት ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መደረግ ስላለበት ድጋፍ መወያየታቸው ተገልጿል።
መሪዎች የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ እየተደረጉ ያሉ ዓለም አቀፍ ትብብሮች አስፈላጊነት ላይ መነጋገራቸውም ተገልጿል።
የጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ጽ/ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ ጨምሮ እንደገለጸው፤ ሁለቱ መሪዎች በትግራይ ስለተከሰተው ጉዳይም ተወያይተዋል።
መሪዎቹ በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና የሰብዓዊ መብት መከበር አስፈላጊነት ላይ መክረዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረትና ጋዜጠኞች ወደ ስፍራው እንዲጓዙ መፍቀዱን አበረታች ነው ያሉ ሲሆን፤ ካናዳ በኢትዮጵያ ሁሉን አካታች የሆነ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።












