ዩናይትድ ኪንግደም በኢትዮጵያ ዳግም የሚጀመር ግጭት ለቀጣናው ጭምር አውዳሚ እንደሚሆን አስጠነቀቀች

ታንክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ በድጋሚ የሚጀመር ግጭት ለትግራይ ክልል፣ ለኢትዮጵያ እና ለቀጣናው "አውዳሚ ይሆናል" ሲል አስጠነቀቀ።

የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ሁኔታ "በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለው" መሆኑን ገልጾ፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን "አደጋ ላይ የሚጥሉ እርምጃዎች" እንዳይወሰዱ አሳስቧል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ማሳሰቢያ የሰጠው ዛሬ አርብ ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም. ባወጣው አጭር መግለጫ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም ትግራይ ክልል ውስጥ የሚታዩ ክስተቶችን "በቅርበት" እየተከታተለች መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ ከፕሪቶሪያ ስምምነት "መንፈስ ወይም ማዕቀፍ ውጪ የሆኑ እርምጃዎችን አናበረታታም" ብሏል።

የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም. ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በክልሉ ያለው ውጥረት "በአስቸኳይ እንዲረግብ" ጠይቋል። ሕብረቱ፤ "ትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ እየታዩ ያሉ ሁኔታዎችን በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለ" መሆኑን ገልጿል።

አውሮፓ ሕብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም መግለጫዎችን ያወጡት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከስድስት ዓመት በፊት ክልሉ በተናጠል ባካሄደው ምርጫ የተመሠረተው ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ መወሰኑ ግጭት ይፈጠራል የሚል ስጋት በድጋሚ እንዲያገረሽ ካደረገ በኋላ ነው።

ህወሓት፤ ፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ቆይታ "ለብቻው" ባስተላለፈው ውሳኔ በማራዘም የፕሪቶሪያ ስምምነትን "አፍርሷል" በማለት ይከስሳል።

የሌተናንት ጄነራል ታደሰ የቆይታ ጊዜ የተራዘመበት መንገድ "ሕጋዊ" መሆኑን በወቅቱ የገለጸው የፌደራል መንግሥት እስካሁን ድረስ ስለ ህወሓት ውሳኔ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የብሪታኒያ ኤምባሲ በዛሬው መግለጫው፤ ውጥረት "እንዲረግብ እና ዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነት ትግበራን በተመለከተ በአስቸኳይ ወደ ንግግር እንዲመለሱ ጥሪ እናቀርባለን" ብሏል።

ኤምባሲው "የግጭት እንደ አዲስ መጀመር ለትግራይ፣ ኢትዮጵያ እና ሠፊው ቀጣና አውዳሚ ይሆናል" ሲል አስጠንቅቋል።

ትናንት መግለጫ ያወጣው የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ "ውጥረት እንዲረግብ እና በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውም እርምጃዎች እንዲወገዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን" ብሏል።

"ሌላ አስከፊ ግጭትን ማስወገድ እና በ[ሁሉም] ወገኖች መካከል ያሉ ልዩነቶችን በፖለቲካዊ ንግግር መፍታት አስፈላጊ ነው" ሲልም ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

የአውሮፓ ሕብረት የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ የሚጠይቅ መግለጫ ያወጣው በትግራይ ጦርነት ምክንያት አቋርጦ የነበረውን ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የቀጥታ በጀት ድጋፍ በድጋሚ ማስጀመሩን ባስታወቀ በቀናት ልዩነት ነው።

የሕብረቱ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ለኢትዮጵያ መንግሥት 140 ሚሊዮን ዩሮ በመስጠት ከአምስት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ተቋርጦ የቆየው ቀጥታ በጀት ድጋፉን በድጋሚ መጀመሩን አስታውቋል።

የሕብረቱ የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነት የሆኑት ጆሴፍ ሲኬላ "የበጀት ድጋፉ በድጋሚ መጀመር በኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ ያለንን መተማመን እና ለዚህ አጋርነት ያለንን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

ይህ የአውሮፓ ሕብረት እርምጃ ግን ከዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።

ሂውማን ራይትስ ዎች፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ጦርነት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማስፈን "ትርጉም ያለው" እርምጃ አለመውሰዱን እንዲሁም በህወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካከል የግጭት ስጋት በድጋሚ ማንዣበቡን ጠቅሷል።

እነዚህ እና ሌሎች የመብት ጥሰቶችን የጠቀሰው ተቋሙ፤ የበጀት ድጋፉን በድጋሚ መጀመሩ ሕብረቱ ከዚህ ቀደም ያቀረባቸውን "የፍትሕ እና የሰብአዊ መብቶች መከበር ጥሪዎችን የሚክድ ነው" ብሏል።