ትራምፕ ከሩሲያ ነዳጅ ለመግዛት ከስምምነት ሲደርሱ ዜሌንሲኪ ቅሬታቸውን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Anna Moneymaker/Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ ከፍተኛ ጫና እየገጠማቸው ባለበት በአሁኑ ወቅት ከሩሲያ የናፍጣ ዘይት ወደ አሜሪካ ለማስገባት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ እንዳሉት ፑቲን 300,000 ቶን ናፍጣ ከአሁን ጀምሮ "ለአሜሪካ እና ለዓለም ገበያ" ለመልቀቅ ተስማምተዋል። በኅዳር ወር 500,000 ቶን እና ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ ሚሊዮን ቶን ናፍጣ ዘይት ለመልቀቅ ፑቲን ከአሜሪካ ጋር ተስማምተዋል።
አርብ ዕለት በአሜሪካ እና ሩሲያ መካከል የተደረሰው ስምምነት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን አስቆጥቷል።
ዜሌንስኪ ስምምነቱን ይህ ለፑቲን የተሰጠ ስጦታ ሲሉ ገልጸውት "ሊራዘም ሳይሆን ሊቆም የሚገባው ጦርነት ላይ የሚፈስ መዋዕለ ነዋይ" በማለት ኮንነውታል።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር እስከ ሚያዚያ 7 ድረስ በሩሲያ የናፍጣ ምርት ላይ ተጥለው የነበሩትን ማዕቀቦች በስምምነቱ መሠረት ለጊዜው ማቋረጡ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን በአሜሪካ ባንኮች ውስጥ ያሉ ሌሎች ሀብቶች አሁንም ታግደዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ባጋሩት መልዕክታቸው ላይ ተጨማሪ ሦስት ሚሊዮን ቶን የሩሲያ የናፍጣ ዘይት "በአጭር ጊዜ ውስጥ" እንደሚደርስ አክለው ገልጸዋል። ይህም በዩክሬን ጥቃት በተፈፀመባቸው የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ነው።
ፑቲን ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ አገራቸው በናፍጣ ላይ የምታደረገውን የውጭ ንግድ ላይ ማዕቀብ ቢጣልም ለአሜሪካም ሆነ ለዓለም ገበያዎች የናፍጣ እና ነዳጅ ዘይት ምርቶችን ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ መጠኑ ምን ያህል እንደሚሆን ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።
ተንታኞች ግን ሩሲያ ያንን ያህል መጠን ያለው ናፍጣ ዘይት ማቅረብ ትችል እንደሆነ እና ይህን ማድረግ ለአሜሪካ ሸማቾች ምን ያህል ዋጋውን እንደሚቀንስ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
የኩዊልተር ቼቪዮት የኢንቨስትመንት ስትራቴጂስት የሆኑት ቲም አርሚቴጅ ትራምፕ የጠቀሷቸው ቁጥሮች "በአንፃራዊነት ትንሽ" ናቸው ብለዋል።
የመጀመሪያው ክፍል በግምት 2.25 ሚሊዮን በርሜል የሚጠጋ ሲሆን የአሜሪካ ዕለታዊ ፍጆታ ደግሞ 3.8 ሚሊዮን በርሜል እንደሚደርስ ተናግረዋል።
"ስለዚህ በአሜሪካ ውስጥ ባለው የነዳጅ ዋጋ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም" ብለዋል።
"እርግጥ ነው፣ ሁለት ተጨማሪ ዙር ሽያጭ ይኖራል፣ ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚያደረጉት ጥረት ተስፋ የመቁረጥ እርምጃ ይመስላል።"
ቢቢሲ ዋይት ሐውስን ሩሲያ ከዚህ ስምምነት ምን እንደምታገኝ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ አቋማቸው ግልጽ መሆኑን እና ዩክሬንን ለመደገፍ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
"ዩኬ እስካሁን በጣለችው እጅግ በጣም ከባድ ማዕቀብ ሩሲያ ላይ የምናደርገውን ጫና እንቀጥላለን፣ ይህም የፑቲንን ጥቃት ዋጋ ከፍ ያደርገዋል እና ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል።"
ዓርብ ዕለት ይፋ የተደረገው ይህ ስምምነት ትራምፕ በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ ያደረጉት የቅርብ ጊዜ ጥረት ነው።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ ላይ የተጀመረው የኢራን ጦርነት በአገሪቱ ላይ ካስከተላው ፖለቲካዊ መዘዝ ባሻገር በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ያሳድረውን ተጽዕኖ ለመፍታት ለወራት ሲታገሉ ቆይተዋል።
ይህ ግጭት በቅርብ ወራት ውስጥ በአሜሪካ የነዳጅ በተለይም የናፍጣ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
የዩክሬን ድሮን ጥቃቶች የነዳጅ ማጣሪያዎቿን በመምታታቸው፣ ሩሲያ በዚህ ዓመት ሁለት ዋና ዋና የነዳጅ እጥረቶች አጋጥመዋታል። ዓለም አቀፉ የኤነርጂ ኤጀንሲ እንደገመተው፣ የሩሲያ የናፍጣ ዘይት ምርት በ30 በመቶ ገደማ ቀንሷል።
ትራምፕ የዩክሬንን ጥቃቶች በመተቸት፣ ለነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት ናቸው ሲሉ ወንጅለዋል።
ሆኖም ዜሌንስኪ አርብ ዕለት ጥቃቶቹን በመከላከል፣ እነዚህ ጥቃቶች ሩሲያ ለዓመታት በዩክሬን የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ለፈጸመችው የተሰጡ ምላሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሩሲያ የዩክሬንን የኃይል መሠረተ ልማት ማውደሟን ካቆመች፣ ዩክሬንም በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እንደምታቆም ተናግረዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ያጋሯቸው ልጥፎች ብዙውን ጊዜ ሩሲያ ይህንን ነዳጅ ለዓለም ገበያ እንዴት እያቀረበች እንደሆነ እና በምላሹ ምን እንደምታገኝ የተሟላ መረጃ አይሰጡም።




































