ሌዲ ጋጋ የተሰረቁ ውሾቿን ለሚመልስ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እውቅ የሙዚቃ ሰው ሌዲ ጋጋ ሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ የተሰረቁ ውሾቿን ለመለሰ ሰው ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች።
አንድ ታጣቂ ረቡዕ ምሽት የሌዲ ጋጋ ሶስት ውሾችን ሲያናፍ የነበረ ተንከባካቢን በጥይት መትቶ ካቆሰለ በኋላ ሁለት ውሾች ይዞ ተሰውሯል።
በአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ውሾቹን ሲያናፍስ የነበረው ሪያን ፊሸር በሚል ስሙ የተገለጸው ሲሆን፤ በጥይት መመታቱን ተከትሎ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ፖሊስ የደረሰበት የጉዳት መጠን አልገለጸም።
ሌዲ ጋጋ ኮጂ እና ጉስታቭ የሚባሉትን የፈረንሳይ ዝርያ ያላቸውን ሁለት ውሾቿን የት እንዳሉ ለሚጠቁም ወረታ እንደምትከፈል ገልጻለች።
ሚስ ኤሲያ የተባለችው ሦስተኛው ውሻ ሮጣ ከስፍራው ካመለጠች በኋላ ፖሊስ አግኝቶ መልሷታል።
በእውነተኛ ስሟ ስቲፋኒ ጀርማኖታ ተብላ የምትታወቀው ሌዲ ጋጋ በወቅቱ ሮም ውስጥ በፊልም በመሥራት ላይ ነበረች። ውሾቹን ለሚመለስ ለማንኛውም ሰው 500,000 ዶላር ወረታ ለመስጠትም ቃል ገብታለች።
የፕሬስ ወኪሏ ውሾቹ ስላሉበት ቦታ መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው መረጃ እንዲሰጣቸው በውሾቹ ስም የተከፈተ የኢሜይል አድራሻ አስተዋውቀዋል።
የውሾቹ ዝርያ ውድ ከሚባሉት መካከል ሲሆኑ የአንድ ቡችላ ዋጋ ከ2 ሺህ እስከ 10 ሺህ ዶላር ሊጠየቅባቸው ይችላል።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ ረቡዕ ምሽት "ከማይታወቅበት ቦታ ተኩሶ ተጎጂውን ያቆሰለውን" ሰው እየፈለገ መሆኑን አረጋግጧል።"ተጠርጣሪ ሊሆን ይችላል" የተባለው ግለሰብ ወንጀሉን ፈጽሞ በነጭ ተሽከርካሪ ሸሽቷል ሲልም ፖሊስ አክሏል።
የሌዲ ጋጋ ውሾች በጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ ስለመሆናቸው ግልጽ አይደለም።
ጋጋ ውሾቿን በመንከባከብ የምትታወቅ ሲሆን በአሜሪካ የሙዚቃ ሽልማት መድረኮች እና በሱፐር ቦውል ትርኢት ላይ ውሾቿን ይዛ ተገኝታ ነበር።
ከጥቃት አድራሹ ያመለጠችው ሚስ እስያ የተባለችው ውሻ ይፋዊ የኢንስታግራም ገጽ ያላት ሲሆን በገጿ ከ224ሺህ በላይ ተከታዮች አሏት።












