ቢል ጌትስ ቢትኮይን ላይ ገንዘቤን አላፈስም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማይክሮሶፍት ፈጣሪ ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ ቢትኮይን ላይ ገንዘባቸውን እንዳላፈሰሱ ተናገሩ።
ባላሃብቱ ይህን ያሉት ክለብሃውስ የተሰኘው ማሕበራዊ ድር-አምባ ላይ ቀርበው ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጌትስ፤ ቢትኮይን ላይ ገንዘባቸውን ከሚያፈሱ ይልቅ "ምርት ባላቸው" ኩባንያዎች ላይ ፈሰስ ቢያደርጉ እንደሚመርጡ አስታውቀዋል።
ለምሳሌ የወባና ኩፍኝ በሽታዎች ክትባት ላይ ገንዘባቸውን ቢያውሉ እንደሚመርጡ ተናግረዋል።
ጌትስ ከዚህ በፊት በአሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች አምራች የሆነው ቴስላ ባለቤት ኢላን መስክ ገንዘቡን ቢትኮይን ላይ ማዋሉን አስመልክቶ በቅርቡ ሐሳባቸውን ሰጥተው ነበር።
"በቢትኮይን ላይ ያለኝ አጠቃላይ ትንተና ምንድነው ከኢላን መስክ ያነሰ ገንዘብ ካላችሁ ተጠንቀቁ ማለት ነው የምሻው" ሲሉ ለብሉምበርግ ተናግረው ነበር።
"ኢላን በርካታ ገንዘብ አለው። ደግሞም እሱ በጣም ውስብስብ ሰው ነው። እኔም የሱ ቢትኮይን መጠን ድንገት ተነስቶ ይቀንሳል ወይም ይጨምራል የሚል ግምት የለኝም።"
ቴስላ 1.5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን መግዛቱን ካሳወቀ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ 50 በመቶ ጨምሯል።
ቴስላ አክሎም ቢትኮይንን እንደመገበያያ ገንዘብ እንደሚቀበል ይፋ አድርጓል።
ነገር ግን የቢትኮይን ዋጋ ኋላ ላይ በ20 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት የሌን መገበያያውን "በጣም ብቁ ያልሆነ ነው" ሲለ ገልፀውት ነበር።
ቢል ጌትስ ለረዥም ጊዜ በቢትኮይን ላይ ያላቸው እምነት ዝቅ ያለ መሆኑን ሲናገሩ ነበር።
ቢትኮይን ምንድነው?
ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታልገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል።
ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።
ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው።
ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል።
ቢትኮይንን የፈጠረው ግለሰብ/ቡድን በዓለም ላይ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ እንዲፈጠሩ ገደብ እንዳስቀመጡ ይታመናል።
የብሎክቼይን መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን 17 ሚሊዮን ያህል ቢትኮይኖች ማይን ተደርገዋል።












