ለሳዑዲው ንጉሥ ስልክ የመቱት ባይደን ስለ ሰብዓዊ መብት አነሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሳዑዲ አራቢያው ንጉሥ ሳልማን ጋር ስለሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ተነጋገሩ።
ባይደን የአሜሪካ 'ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅ' ከሆነችው ሳዑዲ ጋር በአዲስ መልክ ግንኙነት መጀመር ፈልገዋል።
ባይደን አሜሪካ "በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችና የሕግ መከበር" ዙሪያ ያላትን አቋም "አስረግጠው ተናግረዋል" ብሏል ዋይት ኃውስ።
ባይደን ወደ ሳዑዲ ስልክ የደወሉት የጃማል ካሾግጂን ግድያ የተመለከተ አንድ ምስጢራዊ መረጃ ካነበቡ በኋላ ነው።
በቅርቡ ይለቀቃል የተባለው መረጃ በጃማል ኻሾግጂ ግድያ ዙሪያ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ እጅ አለበት ወይ የሚለውን የሚዳስስ ነው ተብሏል።
ከባይደን በፊት አሜሪካን የመሩት ዶናልድ ትራምፕ ከሳዑዲ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው።
መረጃው በ2018 ወጥቶ የነበረና በሲአይኤ የተገኘ ሲሆን ነገር ግን የወቅቱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተባብለውት ነበር።
ባይደን ከሳዑዲ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት በአንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንከር ያለ አቋም ያንፀባርቃሉ ተብሏል።
ጋዜጠኛው ጃማል ኻሾግጆ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ሰውነቱ ተቆራርጦ መገደሉ ቢዘገብም የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ እጄ የለበትም ሲሉ በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት ኻሾግጂን በሕይወት ይዘው እንዲመለሱ የተላኩ ሰዎች ናቸው በጭካኔ የገደሉት በማለት የሚቀርብባቸውን ክስ ያስተባብላሉ።
የሳዑዲ መንግሥት በግድያው ተሳትፈዋል ያላቸውን አምስት ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ከወሰነ በኋላ ወደ 20 ዓመት እሥር እንዲቀልላቸው አድርጓል።
ባይደን ምን አሉ?
ዋይት ኃውስ እንዳለው የኻሾግጂ ስም በስልክ ልውውጡ ላይ ባይነሳም "ፕሬዝደንቱ በቅርቡ ሳዑዲ የመብት ተሟጋቾችን ከእሥር በመልቀቋ አመስግነው፤ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይነት ላይ ያለትን አቋም አንፀባርቀዋል።"
የሳዑዲ ሴቶች መብት አቀንቃኝ የሆነችው ሉጄይን ሃትሉል ከሶስት ዓመት እሥር በኋላ የተለቀቀችው በቅርቡ ነው።
ነገር ግን ወደ ውጭ ሃገር መጓዝም ሆነ ለመገናኝ ብዙሃን ድምጿን መስጠት አትችልም።
ሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እንዴት ማጠንከር እንደሚቻል እንዲሁም በኢራን የሚደገፉ የሳዑዲ ጠላቶችን እንዴት መመከት እንደሚቻል መክረዋል።
ምንም እንኳ ዋይት ኃውስ የስልክ ልውውጡን ሙሉ ፅሑፍ ይፋ ባያደርግም የሁለቱ መሪዎች የስልክ ንግግር ከዚህ በፊቱ ለየት ያል ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ይገምታሉ።
ባይደን የኻሾግጂን ግድያ የተመለከተ ምስጢራዊ መረጃ ከደረሳቸው በኋላ ለሳዑዲው ንጉሥ ስልክ መምታቸው ግጥጥሞሽ አይደለም የሚሉ በርካቶች ናቸው።
የሲአይኤው መረጃ ኤምቢኤስ በተሰኘ ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን፤ በኻሾግጂ ግድያ እጃቸው እንዳለበት ያመለክታል ሲሉ በርካቶች ዘግበዋል።
የኻሾግጂን ስም በግላጭ ማንሳት የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት የበለጠ ሊያሻክረው ይችላል ተብሏል።
ባይደን የሳዑዲው አልጋ ወራሽና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጫና ይደርስባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ልዑል አልጋ ወራሽ አንድ ቀን ምናልባትም በቅርቡ የሳዑዲ ንጉሥ ሆነው ሊሾሙ ይችላሉ።
ጃማል ኻሾግጂ እንዴት ነበር የተገደለው?
የ59 ዓመቱ ጋዜጠኛ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ቱርክ፤ ኢስታንቡል ወደሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ቅጥር ግቢ ሲገባ ነበር።
ኻሾግጂ ወደ ቆንስላ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2/2018 ያመራው ቱርካዊቷን ዕጮኛውን ለማግባት የሚያስችሉ ወረቀቶች ለመቀበል ነበር።
እንደ ሳዑዲ አቃቤ ሕግ 'ከሆነ ካሾግጂ በግዳጅ ከግቢው እንዳይወጣ ተደርጓል፤ መጠኑ ከፍ ያለ መድኃኒትም ተሰጥቶታል። ለሞቱ ምክንያት የሆነውም ይህ ነው። ከዚያም ሬሳው ተቆራርጦ ከቆንስላው ውጭ ላለ 'ተባባሪ' ተሰጥቶ ነበር። ቅሪቱ እስከዛሬ አልተገኘም።'
ኻሾግጂ በአንድ ወቅት የሳዑዲ መንግሥት አማካሪና የንጉሣዊው ቤተሰብ ቅርብ ሰው ነበር።
ነገር ግን ከሳዑዲ አገዛዝ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት በፈረንጆቹ 2017 ሃገሩን ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ የሚወጣ የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድን ፖሊሲዎች የሚተች ወርሃዊ ዓምድ ያሳትም ነበር።
ኻሾግጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣው ላይ ባሳተመው ፅሑፍ የሳዑዲ መንግሥት ሊያስረኝ ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳለው ፅፎ ነበር።
በመጨረሻው ፅሑፉ ደግሞ የሳዑዲን መንግሥት በየመን ግጭት ጣልቃ በመግባቱን ተችቶት ነበር።












