ትግራይ ፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ መግባት የለባትም አለ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለባትም ሲል ምላሽ ሰጠ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር "አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ማውጣቷ በተለይም የአማራ ክልል ኃይሎች ስምሪት በመግለጫው መጠቀሱ የሚያሳዝን ነው" ብሏል በመግለጫው።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ያለው ትናንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይል ከትግራይ ክልል መውጣት አለባቸው የሚል መግለጫን ማውጣቱን ተከትሎ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለዚህ በሰጠው ምላሽ "እንደ ሉዓላዊት አገር ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ኃላፊነት ነው ያለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የትኛውንም የጸጥታ መዋቅር ማሰማራት የመንግሥት ኃላፊነት ነው" ብሏል በመግለጫው።
"የፌደራሉ መንግሥት በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሰላም እና ደኅንነትን በማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ያስከብራል" ያለው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ፤ ይህን ኃላፊነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ "በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ተልዕኮ መካሄዱን" አስታውቋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በትናንቱ መግለጫው የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ተሰማርቷል ስለመባሉ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትም ሆነ የኤርትራ መንግሥት በትግራዩ ጦርነት ኤርትራ ተሳትፎ የላትም ብለዋል።
ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጽ/ቤት የወጣው የአሜሪካ መግለጫ፤ "የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ መውጣታቸው ወሳኝነት ያለወቅ ቀዳሚ እርምጃ ነው" ካለ በኋላ፤ "በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት እራሳቸውን ከኃይል እርምጃዎች ቆጥበው በትግራይ ክልል ውስጥ ድጋፍ የሚያሻቸው ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው መፍቀድ ይኖርባቸዋል" ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ፤ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እና 3 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር መድረስ መቻሉን ገልጿል።
ጨምሮም መንግሥት 70 በመቶ ድጋፍ በራሱ እያደረገ መሆኑ እና ቀሪውን 30 በመቶ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው ብሏል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በመግለጫቸው በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ማስቆም አስፈላጊነት ላይ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ፣ እንዲሁም ተፈጽመዋል የተባሉ ግፎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር የተሟላ፤ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድን እንዲገባ መፍቀድን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተደጋጋሚ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመሆኑ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ያለገደብ ወደ ክልሉ ገብተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ፈቅጃለሁ ብሏል።
እንደማሳያም የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻል ማሳየቱን እና ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መጠቆማቸውን በመግለጫው ተመልክቷል።
ተፈጽመዋል ስለተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም በተመለከተ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጾ፤ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ አጥፊዎች ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነት እንዳለው አስታውቋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በመግለጫው መንግሥት "ዝርዝር ምርመራ አድርጎ" ተጠያቂዎችን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም መንግሥት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድጋፍን ከመቀበል በሻጋር፤ አግባብ ካለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካል ጋር በጥምረት ምርመራ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ አመላክቷል።
በመግለጫው ላይ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥያቄዎች ሁለት መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን ፤ እነዚህም፤ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ያልተገደበ ፍቃድ መስጠት እና ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ይጣሩ የሚሉ ናቸው።
እነዚህ ሁለት አበየት ጉዳዮች በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የተነሱ መሆኑን ያስታወሰው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ፤ መንግሥት አዎንታዊ እና ገንቢ በሆነ መልኩ ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትግራይ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአክሱም ከተማ በኤርትራ ወታደሮች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ነበር።













