ትግራይ፡ አሜሪካ የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ መውጣት አለባቸው አለች

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር አንቶኒ ብሊንከን

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትግራይ ይገኛሉ ያላቸው የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይል ከክልሉ መውጣት አለባቸው አለ።

አሜሪካ ይህን ያለችው በትግራይ ክልል ውስጥ ግድያዎች ስለመፈጸማቸውና በክልሉ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የሚገልጹ ሪፖርቶች በእጅጉ አሳስበውኛል ባለችበት መግለጫ ላይ ነው።

የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ መውጣታቸው ወሳኝነት ያለወቅ ቀዳሚ እርምጃ ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ፤ በዚህም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት እራሳቸውን ከኃይል እርምጃዎች ቆጥበው በትግራይ ክልል ውስጥ ድጋፍ የሚያሻቸው ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው መፍቀድ ይኖርባቸዋል ብሏል።

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትም ይሁን የኤርትራ መንግሥት በትግራዩ ጦርነት ኤርትራ ተሳትፎ የላትም ቢሉም፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከዚህ ቀደም የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን የሚገልጽ መረጃ ማውጣቱ ይታወሳል።

በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ የክልል ልዩ የፖሊስ ኃይሎች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ልዩ ኃይል የፈደራሉ ሠራዊት ከህወሓት ኃይሎች ጋር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሆን ተሳታፊ እንደነበር በወቅቱ ተገልጿል።

የአሜሪካ ውች ጉዳይ ኃላፊ የአንቶኒ ቢልንከን መግለጫ የወጣው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከ200 በላይ ሰዎች በአክሱም ከተማ በኤርትራ ወታደሮች ተገድለዋል የሚል ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ነው።

"በተለያዩ ወገኖች የሚፈጸሙት ግድያዎች፣ በኃይል ማፈናቀልን፣ ጾታዊ ጥቆቶች እንዲሁም ሌሎች አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጥብቀን እናወግዛለን" ብሏል ትናንት የወጣው መግለጫ።

አምነስቲ ዓርብ ዕለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ የፈጸሙት ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን ይችላል ብሏል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህ በአምነስቲ የወጣው ሪፖርት "ባልተሟላ መረጃና ውስን በሆነ የጥናት ዘዴ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው" ሲል ተችቷል።

ሚኒስቴሩ ለሪፖርቱ ግብአትንት ጥቅም ላይ የዋሉት መረጃዎች በምሥራቃዊ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞችና አክሱም ውስጥ ካሉ ግለሰቦች በስልክ የተሰበሰበ ቁንጽል መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ፤ ከስደተኞች መካከልም አንዳንዶቹ የህወሓት የቀድሞ ተዋጊዎች የነበሩ ናቸው ብሏል።

በተመሳሳይ ኤርትራ የአምነስቲን ሪፖርት እንደማትቀበለው ገልጻለች። የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ ሪፖርቱ በአብዛኛው መሠረት ያደረገው ሱዳን መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያሉ 31 ግለሰቦችን ነው ብለዋል።

"በዚህ መጠለያ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን በተገደሉበት የማይካድራው ጭፍጨፋ ተሳታፊ ሆነው የሸሹ የህወሓት ሚሊሻዎች መሆናቸው ይታወቃል" በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር አንቶኒ ብሊንክን በትናንትናው መግለጫቸው በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ማስቆም አስፈላጊነት ላይ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ፣ እንዲሁም ተፈጽመዋል የተባሉ ግፎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር የተሟላ፤ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድን እንዲገባ መፍቀድን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተደጋጋሚ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው ህወሓት በማዕከላዊው መንግሥት ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከተሎ ከተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ "ገለልተኛና ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግና ጠፋተኞች ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ብሏል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ፤ ዓርብ ዕለት የጠቅላይ ሚንሰትሩ ጽ/ቤት እና የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎችን ለመመርመር ዓለም አቀፍ ድጋፍን ለመቀበልና ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለማመቻቸት እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የገቡትን ቃል በበጎ ጎኑ እንደሚቀበለው አመልክቷል።

አሜሪካም ይህን ግብ ለማሳካት ከሌሎች የዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጿል። ለዚህም የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) አንድ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ህይወት አድን የእርዳታ ሥራ ላይ እንደሚሰማራ ተገልጿል።

መግለጫው የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች አጋሮችን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የአፍሪካ ሕብረት እና የቀጠናው አጋሮች በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ከአሜሪካ ጋር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመገንባት አሁንም ቁርጠና መሆኗን ገልጸዋል።

line

ከቀናት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰሜን ኢትዮጵያ ስለተከሰተው ቀውስ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በስልክ በነበራቸው ወይይት፤ "በትግራይ ክልል እየተባባሰ ስለመጣው የሰብዓዊ ቀውስና የሰብዓዊ መብት ጥሰት" መነጋገራቸውን ዋይት ሃውስ ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል። መሪዎች

መሪዎቹ በትግራይ "ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ መከላከልና የሰብዓዊ ድጋፍ መድረስ አስፈላጊነት ላይ" ተነጋግረዋል ሲል የዋይት ሐውስ መግለጫ አመልክቷል።