ዘመናዊው የሒሳብ ቀመር ከጥንታዊው እስላማዊ ቤተ-መጽሐፍት

የሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል-ክዋርዚም ሐውልት በኡዝቤኪስታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል-ክዋርዚም ሐውልት በኡዝቤኪስታን

የጥበብ ቤት (ባይት አል-ሂክማህ) ተብሎ የሚጠራውና በ13ኛው ክፍለ ዘመን የፈረሰው የዚህ ጥንታዊ ቤተ-መጽሐፍት ምንም ቀሪ ፍርስራሽ የለም። ስለዚህም ይህ ቤተ-መጸሕፍት በትክክል የት እንደነበር ወይም ምን ይመስል እንደነበር እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ይህ የጥበብ ቤት በእስላማዊው ወርቃማ ዘመን በባግዳድ ቀዳሚው የምሁራን ቤት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ባይት አል-ሂክማ የዘመናችን "አረብኛ" ቁጥሮችን ጨምሮ የሒሳብ ፅንሰ-ሀሳቦች መነሻ ነው።

በስምንተኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በሀሩን አል-ራሺድ የተቋቋመው በይት አል-ሂክማ አሁን ላይ ከአራቱም የዓለም ጫፍ ተመራማሪዎችን ወደ ባግዳድ እንዲመጡ ያስገድዳል።

በለንደን የሚገኘውን የብሪታንያ ቤተ-መጻሕፍት ወይም የፓሪስ ቢብሊዮቴክ ናሽናሌን የሚያህለው የጥበብ ቤት የሒሳብ፣ የሥነ ፈለክ፣ የህክምና፣ የኬሚስትሪ፣ የጂኦግራፊ፣ የፍልስፍና፣ ሥነ-ጽሑፍ እና ሥነ ጥበባትን ጨምሮ እንደ ኮከብ ቆጠራ ያሉ ተጨማሪ ትምህርቶች ይሰጡበታል።

አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል አካዳሚው የሒሳብ ትምህርትን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር እሳቤን አስገኝቷል።

ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ይህ የጥበብ ቤት እአአ በ1258 ባግዳድ ውስጥ ወድሟል

ይህ የጥበብ ቤት እአአ በ1258 ባግዳድ ውስጥ ወድሟል። በአፈ ታሪክ እንደሚባለው ብዙዎቹ ጽሑፎች ወደ ጤግሮስ ወንዝ በመጣላቸው የወንዙ ውሃ ቀለም ጥቁር ሆኖ ነበር ይባላል። የወንዙ ጥቁር ቀለም የያዘው መጽሐፍቱ የተጻፉበት ቀለም ጥቁር ስለነበረ ነው።

በኋላ ላይ ግን እዚያ የተደረሰባቸው ግኝቶች በእስላማዊው ኢምፓየር፣ በአውሮፓ እና በመላው ዓለም ተቀባይነት ያገኘውን ረቂቅ የሒሳብ ቋንቋ ወልዷል።

ወደ ቀዳሚው ጊዜ መራመድ

"ዋናው ቁም ነገር የጥበብ ቤቱ የት እና መቼ እንደተጀመረ ዝርዝር ነገር ማወቅ አይደለም። ትልቁ ጉዳይ የመዳበሩ ሳይንሳዊ ሀሳቦቹ ነው" ሲሉ በሱሬይ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂም አል-ካሊሊ ይናገራሉ።

የጥበብ ቤትን የሒሳብ ትሩፋት ለመፈለግ ትንሽ ወደ ቀደመው ጊዜ መራመድን ይጠይቃል።

በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት አንድ ስም በአውሮፓ ውስጥ ከሒሳብ ጋር አብሮ ይነሳ ነበር፤ ሊዮናርዶ። ህይወቱ ካለፈ በኋላ ፊቦናቺ ተብሎ ይጠራል።

በጎርጎሮሳዊያኑ 1170 ፒሳ ውስጥ የተወለደው ጣሊያናዊው የሒሳብ ሊቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በሰሜን አፍሪካ ባርበሪ የባህር ዳርቻ በሚገኘው የንግድ አካባቢ በሆነችው ቡጊያ ነው።

በ 20ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜው ላይ ፊቦናቺ ከሕንድ በፋርስ በኩል ወደ ምዕራብ በመጡ ሐሳቦች ተማረኮ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተጓዘ። ፊቦናቺ ወደ ጣሊያን ሲመለስም የሂንዱ-አረብኛ የቁጥር ሥርዓትን ከሚገልጹ የመጀመሪያዎቹ የምዕራባውያን ሥራዎች አንዱ የሆነውን 'ሊበር አባቺን' አሳተመ።

ሊዮናርዶ ዳ ፒሳ። ህይወቱ ካለፈ በኋላ ሊዮናርዶ ፊቦናቺ በሚለው መጠሪያው ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሊዮናርዶ ፊቦንቺ

ሊበር አባቺ በ1202 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታተም የሂንዱ-አረብ ቁጥሮች በጥቂት ምሁራን ብቻ ይታወቁ ነበር። የአውሮፓ ነጋዴዎች እና ምሁራን የሮማውያንን ቁጥሮች የሙጥኝ ብለው ነበር። ይህም ማባዛት እና ማከፈልን በጣም ከባድ አድርጎታል (እሰቲ MXCI ን በ LVII ለማባዛት ይሞክሩ)።

የፊቦናቺ መጽሐፍ በሒሳብ ሥራዎች ውስጥ የቁጥር አጠቃቀሞችን አሳይቷል። ይህም እንደ ትርፍ ልዩነት፣ የገንዘብ መለወጥ፣ ክብደት መለወጥ እና ወለድ ባሉ ተግባራዊ ጉዳዮች ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ ቴክኒኮችን ያየዘ ነው።

"የማስላት ጥበብን ለማወቅ በእጅ ጣቶች ቁጥር ማስላትን ማወቅ አለባቸው" ሲሉ ፊኖባቺ ጽፏል። በአሁኑ ወቅት ልጆች በትምህርት ቤት ሒሳብ ማስላትን ሲጀምሩ በጣቶቻቸው መማር እንዲጀምሩ ይደረጋል።

"በእነዚህ ዘጠኝ ቁጥሮች እና በዜሮ (0) ማንኛውም ቁጥር መጻፍ ይቻላል" ይላል።

የፊቦናቺ ብልህነት በሒሳብ ሊቅነቱ ፈጠራ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በሙስሊም ሊቃውንቶች ዘንድ የሚታወቁትን ጥቅሞች በሚገባ መረዳቱ ነበር። ይህም የሒሳብ ቀመሮቻቸውን፣ የአስርዮሽ ቦታ ሥርዓታቸውን እና አልጀብራቸውን ያካትታል።

በእርግጥ ሊበር አባቺ በዘጠነኛው ክፍለዘመን የሒሳብ ሊቅ አል-ክዋርዝሚ የቀመር ስልት ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ ነበር። አብዮቱ ኩዋድራቲክ ኢኩዌዥንን ለመፍታት የሚያስችል ስልት ለመጀመሪያ ጊዜ አቅርቧል።

በግኝቶቹ ምክንያትም አል-ክዋርዝሚ በብዛት የአልጄብራ አባት ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን በ821 ደግሞ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ እና የጥበብ ቤት ዋና ቤተመጻሕፍት ኃላፊም ሆኖ ተሾመ።

የአል-ክዋርዝሚ የህትመት ጽሑፍ የሙስሊሙን ዓለም የአስርዮሽ ቁጥር ሥርዓትን አስተዋውቋል። ሌሎች እንደ ሊዮናርዶ ያሉት ደግሞ በመላው አውሮፓ እንዲተላለፍ ረድተዋል።

አል-ክሃዋሪዝሚ የአልጀብራ አባት ተብሎ ይጠራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አል-ክሃዋሪዝሚ የአልጀብራ አባት ተብሎ ይጠራል

ፊቦናቺ በዘመናዊ ሒሳብ ላይ ያለው የለውጥ ተጽዕኖ ውስጥ አል-ክዋርዝሚ ትልቅ ድርሻ ነበር። በአራት ምዕተ ዓመታት ገደማ ተለያይተው የነበሩ ሁለት ሰዎች በአንድ ጥንታዊ ቤተ-መጽሕፍት ምክንያት ተገናኙ። በመካከለኛው ዘመን የታወቀው የሒሳብ ባለሙያ በእስላማዊ ወርቃማ ዘመን ታዋቂ አስተማሪ ትከሻ ላይ መሠረቱን አድርጓል።

ምናልባትም ስለ ጥበብ ቤት ብዙም ስለማይታወቅ የታሪክ ጸሐፊዎች አልፎ አልፎ ስፋቱን እና ዓላማውን ለመግለጽ ይፈተናሉ። ይህም ካለን አነስተኛ የታሪክ መዛግብት ጋር በተወሰነ መልኩ የሚፃረር ደረጃ ይሰጠዋል።

"አንዳንዶች የጥበብ ቤት በብዙዎች ዘንድ እንደታየው ታላቅ ነገር አልነበረም ብለው ይከራከራሉ። ነገር ግን እንደ አል-ክዋርዝሚ ካሉ ሰዎች ጋር ያለው ቁርኝት እና የሒሳብ፣ የከዋክብት ጥናትና የጂኦግራፊ ሥራው የጥበብ ቤት የተተረጎሙ መጻሕፍት ማከማቻ ብቻ ሳይሆን ለእውነተኛ አካዳሚ የቀረበ መሆኑን እንደሚያሳይ ለእኔ ጠንካራ ማስረጃ ነው" ይላሉ አል-ካሊሊ።

በቤተ-መጽሐፍት ውስጥ የነበሩ ምሁራንና ተርጓሚዎች ሥራዎቻቸው ለሕዝብ ተደራሽ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ነበራቸው።

በኦፕን ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ጁን ባሮው-ግሪን "የጥበብ ቤት በመሠረቱ ወሳኝ የሆነው፤ የአረብ ምሁራን የግሪክ ሐሳቦችን ወደ ቋንቋው የተረጉመው የሒሳብ አረዳዳችን እንደመሠረትን ስላስቻሉ ነው" ብለዋል።

የቤተ መንግሥቱ ቤተ-መጽሐፍት ሳይንሳዊ ፈጠራ ቦታ በመሆኑ የቀደሙት ጊዜያትን ቁጥራዊ ሐሳቦችን መመልከቻ መስኮት ያህል ነበር።

ከአሁኑ የአስርዮሽ ሥርዓታችን በፊት ሰዎች ስሌቶችን ለመመዝገብ ቀደምት የቁጥር ሥርዓቶችን ይጠቀሙ ነበር።

እነዚህ የተለያዩ የቁጥር ውክልናዎች ስለ መዋቅር፣ ግንኙነቶች እና ስለተነሱበት ታሪካዊ እና ባህላዊ አውዶች ሊያስተምሩን ይችላሉ።

ቁጥሮች እንዴት እንደሚሠሩ በተሻለ ለመረዳት እንድንችል የቦታ እሴትንና ረቂቅነትን ሐሳብ ያጠናክራሉ። "የምዕራቡ ዓለም ብቸኛው መንገድ አልነበረም። የተለያዩ የቁጥር ሥርዓቶችን በመረዳት ረገድ እውነተኛ እሴት አለ" ይላሉ ባሮው-ግሪን።

አንዲት ጥንታዊ ነጋዴ "ሁለት በጎች" ብላ ለመጻፍ ከፈለገች የሁለት በጎች ምስል በሸክላ ላይ ማስፈር ትችላለች። ይህ ግን "20 በጎች" ለመፃፍ ከፈለገች ተግባራዊነቱ አነስተኛ ነው። የምልክት አጻጻፍ አንድን እሴት ለማመልከት የቁጥር ምልክቶች አንድ ላይ የሚደመሩበት ሥርዓት ነው። በዚህ ሁኔታም ትክክለኛውን ቁጥር ለመወከል ሁለት በጎች መሳልን ይጠይቃል።

ይህን መሰል የሮማውያን ቁጥር ለመጥፋት ተቃርቧል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ይህን መሰል የሮማውያን ቁጥር ለመጥፋት ተቃርቧል

ዘንድሮ የፊቦናቺ የተወለደበት 850ኛ ዓመት ነው። የሮማን ቁጥሮችን ሥራ የሚቀለበስበት ጊዜም ሊሆን ይችላል።

በዩናይትድ ኪንግደም ትምህርት ቤቶች ቀደም ሲል የነበሩት እና በሮማውያን ቁጥሮች የተዘጋጁት የግዜ ሠሌዳዎች በተማሪዎች በቀላሉ በሚነበቡ የዲጂታል ሰዓቶች ተተክተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ተማሪዎች የአናሎግ ሰዓትን በትክክል ማወቅ አይችሉም በሚል ፍራቻ ነው።

አንዳንድ አገራት ከመንገድ ምልክቶች እና ከኦፊሴላዊ ሰነዶች ያወጧቸው ሲሆን ሆሊውድ ደግሞ በፊልሞቹ ላይ የሮማውያን ቁጥሮችን ከመጠቀም ተቆጥቧል። ሱፐርቦውል የተባለው የስፖርት ውድድርም ለ50ኛ ጨዋታው ደጋፊዎችን ግራ የሚያጋቡ ናቸው በሚል አስቀርቷቸዋል።

"የማንን ታሪክ ነው የምንነግራቸው፣ የማንን ባህል እንደሆነ እና ወደ መደበኛው ትምህርት የምናስገባቸው የዕውቀት ዓይነቶች በምዕራባዊያን የቅኝ ግዛት ተጽዕኖ ሥር መውደቃቸው የማይቀር ነው" ይላሉ በኬምብሪጅ የሒሳብ ሥራ አዘጋጅ የሆኑት ሉሲ ሪይክሮፍት-ስሚዝ።

ቀድሞ የሒሳብ መምህር የነበሩት ሪይክሮፍት-ስሚዝ በሒሳብ ትምህርት ውስጥ ዋና ድምጽ ሲሆኑ የዓለም አቀፍ ሥርዓተ-ትምህርቶችን ልዩነቶችም ያጠናሉ። ዌልስ፣ ስኮትላንድ እና አየርላንድ በትምህርታቸው ውስጥ የሮማን ቁጥሮችን ባያካትቱም አሜሪካ ደግሞ ምንም መደበኛ መስፈርቶች የላትም።

እንግሊዝ ተማሪዎቿ እስከ 100 ያሉትን የሮማን ቁጥሮችን ማንበብ መቻል እንዳለባቸው በግልፅ አስቀምጣለች።

ብዙዎቻችን MMXX ላይ ምንም ልዩ ነገር አናገኝም (2020 ማለት ነው)። በእሱ ስም ለተሰየመው በአንድ የሚጀምረው እና ከዚያ በኋላ የሁለቱ ቀዳሚ ቁጥሮች ድምር በሆነው ዝነኛው ንድፍ ፊቦናቺን በጥቂቱ ልናውቀው እንችላለን።

እነዚህም ብዙውን ጊዜ በሥነ-ጽሑፍ፣ በፊልም፣ በምስል ጥበባት፣ በዘፈን ግጥሞች፣ የኦርኬስትራ ውጤቶች እና በሥነ-ሕንጻ ውስጥም እናገኛቸዋለን።

ሊዮናርዶ በሒሳብ ውስጥ ያደረገው አስተዋፅኦ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እምብዛም የሚነሳ ነገር ነው። ይህ ታሪክ የሚጀምረው ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት በቤተመንግሥት ቤተመጽሐፍት ውስጥ ሲሆን በወቅቱ አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን በዕውቀት ጨለማ ውስጥ የነበሩበት ነው።

ይህም ሒሳብን ከአውሮፓ ጋር የሚያያይዘውን ሃሳባችን ሲያፈርስ፣ በእስላማዊው ዓለም ሳይንሳዊ ግኝቶች ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅ እና ከረጅም ጊዜ በፊት ለነበሩ የቁጥር ሀብቶች አስፈላጊነት ትኩረት እንዲሰጥ የሚከራከር ነው።