ሁመራን የጎበኙት የአሜሪካው አምሳደር "ከፖለቲካ በላይ ለሕዝብ ቅድሚያ እንዲሰጥ" ጥሪ አቀረቡ

አምባደሳር ኧርቪን ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, U.S. Embassy Addis Ababa/fb

የምስሉ መግለጫ, አምባደሳር ኧርቪን ማሲንጋ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባደሳር ኧርቪን ማሲንጋ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኘውን ሁመራን በመጎብኝት ሁሉም ወገኖች ከፖለቲካ በላይ ለሕዝብ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ።

አምባደሳሩ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል ከሚወዛገቡባቸው ቦታዎች አንዱ የሆነውን አካባቢ ከጎበኙ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ከምንም ነገር በላይ ሕዝቡን በማስቀደም "መጻኢ ፖለቲካዊ ዕድላቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲወስኑ" ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

"ሁሉም ሰው ደኅንነቱ እና ክብሩ በተጠበቀ ሁኔታ ቀጣይ ሕይወቱን የት መገንባት እንዳለበት እንዲወስን በኢትዮጵያ የሚመራ እና በተባበሩት መንግሥታት የሚታገዝን ሂደት አሜሪካ ትደግፋለች" ብለዋል።

ለዚህም "ሁሉም ወገኖች ከፖለቲካ በላይ ሕዝብን በማቀስደም የወደፊት የፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታቸውን በተገቢው ወቅት እንዲወስኑ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።"

አምባሳደሩ ጨምረውም የወደፊቱ መንገድ "ውስብስብ ነው" በማለት ነገር ግን "ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ጉዳት ላጋጠማቸው ደኅንነት መሆን አለበት" ብለዋል።

አሜሪካም ኢትዮጵያውያን ለዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗንም በአዲስ አበባ የሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ በአምሳደሩ ስም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሰፈረው መልዕከት አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ስር የሚገኙት አወዛጋቢዎቹ አካበቢዎች በትግራይ ክልል ስር የቆዩ ሲሆን፣ ጥያቄ ሲነሳባቸው ቆይቶ ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ከተነሳ በኋላ የአማራ ኃይሎች ተቆጣጥረውት ይገኛሉ።

የይገባኛል ጥያቄው አሁንም ድረስ ዘላቂ መፍትሄ ያላገኘ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል አካባቢው እንዲመለስለት በተደጋጋሚ እየጠየቀ ነው።

በአማራ ክልል በኩል ደግሞ አካባቢዎቹ የክልሉ አካላት መሆናቸውን በመግለጽ አስተዳደር የመሰረቱ ሲሆን የሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ አወዛጋቢ እንደሆነ ቆይቷል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት ያበቃው እና ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካበቢዎች ውስጥ ውድመት እና የነዋሪዎች መፈናቀል መድረሱ ሲዘገብ ቆይቷል።

በተለይ በሁመራ አካበቢ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት የአሜሪካው አምባደሳር ኧርቪን ማሲንጋ በጉዟቸው ሕዝቡ እየተጋፈጠ ያለውን ችግር በዐይናቸው እንደተመለከቱ እና "የመሠረተ ልማት፣ ውስን የጤና አገለግሎት እና የመሠረታዊ አገለግሎቶች አለመኖር" የሕዝቡን ኑሮ እንደጎዳው ጠቅሰዋል።

በግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ለዓመታት በዓለም አቀፍ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ሆነው መቆየታቸውን ያነሱት አምባሳደሩ፣ "ምንም እንኳን ሰብአዊ እርዳታ ወሳኝ ቢሆንም፤ ዘላቂ መፍትሄ አይደለም" ብለዋል።