የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሕጻጽ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ 'እርዳታ አልተቋረጠም' አለ

እህል የተሸከሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, (ፎቶ ከፋይል)

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሕጻጽ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች የሚቀርበው እርዳታ አለመቋረጡን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ረቡዕ ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መንግሥት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች "የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ ይገኛል" ብሏል።

ባለፉት ቀናት በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በሕጻጽ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ በዕድሜ የገፉ ተፈናቃዮች በረሃብ መጎዳታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አካላቸው የተጎዳ እና የተጎሳቆሎ አረጋውያን ምሥሎች በስፋት ተጋርተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ተፈናቃዮችም ከአስር ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሚኖሩበት የሕጻጽ ጊዚያዊ መጠለያ ውስጥ በርካታ አዛውንቶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሕጻናት በምግብ እና በሕክምና እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሕጻጽ የተፈናቃዮች ማዕከል አስተባባሪ ቄስ አብርሃ አርአያ እንዳሉት ቢያንስ 300 ሰዎች ባለፉት ስድስት ወራት የእርዳታ እህል አላገኙም።

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚገኙት አንድ እናት ለቢቢሲ ትግርኛ ስለሁኔታው "እዚህ ሰው ሁሉ በረሃብ አንጀቱ ተጣብቋል" በማለት "ዋናው ችግር ምግብ የሚባል ነገር የለም። የሚሰጡንም እህል የሚሆን አይደለም. .." ሲሉ ችግራቸውን አስረድተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ገንዘብ በማሰባሰብ እና የእርዳታ እህል በመያዝ ወደ ስፍራው መሄዳቸው በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተዘግቧል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ማክሰኞ ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በሕጻጽ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ባሉ ወገኖች ላይ ያጋጠመውን የረሃብ አደጋ የሚያሳይ ቪድዮ "ለሕዝባቸው በሚቆረቆሩ ጥቂት ወጣቶች" መውጣቱን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም ባዩት እና በሰሙት ችግር አዝነው የተፈናቀለ ሕዝብ ለመርዳት የተለያየ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

"እንደ ሕጻጽ ሁሉ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ባሉባቸው ሌሎች 145 መጠለያ ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ያሉት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ለፌደራል መንግሥት፣ ለክልላዊ መንግሥታት እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አቅርበዋል።

"በትግራይ ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በሞት አደጋ ላይ ያሉትን ወገኖች ሕይወት መታደግና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ከውዴታም በላይ ግዴታ ነውና የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሕጻጽ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የሚገልጸው መረጃ "የተሳሳተ እና የመጠለያ ጣቢያውን አጠቃላይ ሁኔታ የማይገልጽ" መሆኑን ገልጿል።

ኮሚሽኑ የሰብዓዊ ድጋፍ "በመደበኛነት ዓመቱን በሙሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የምግብ ሥርጭት ሳይቆራረጥ" እየደረሰ እንደሚገኝ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽኑ በዚህ ዓመትም ባለፉት አራት ወራት፣ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ "የተሟላ እና ያልተቆራረጠ የምግብ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው" መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በሕጻጽ ባለፉት አራት ወራት ለ14 ሺህ 413 ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉን ጨምሮ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጨምሮ "በመስከረም ወር 16 ሺህ 775፣ በጥቅምት ወር 18 ሺህ 290፣ በኅዳር ወር 17ሺህ 813 እንዲሁም በታኅሣሥ ወር የሚያስፈልገው ለ14 ሺህ 413 ዜጎች የሚያስፈልግ ምግብ ተሠራጭቷል" ሲል በመግለጫው ላይ ዘርዝሯል።

ኮሚሽኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር "የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፍ ችግሮች መኖራቸውን እና ተጨማሪ የፌዴራል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቢጠየቅ ኖሮ በኮሚሽናችን በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለመፈጸም የሚያስችል ዝግጁነት" መኖሩን ገልጿል።

ኮሚሽኑ የሚላከው ሰብዓዊ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋሉን የማረጋገጥና ክፍተቶች መኖራቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ክፍተት እንዲሟላ የማድረግ ኃላፊነት "የክልሉ እና የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን" አሳስቧል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በሰጡት መግለጫ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚቻለው "ደኅንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው መመለስ እና ማቋቋም ሲቻል" መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም "የፌደራል መንግሥት አሁንም ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው በተቻለ ፍጥነት እንዲመለሱ እንዲያደርግ" ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል በመቀለ፣ በሽረ፣ በተምቤን፣ በአቢ አዲ፣ በሰሜን ምዕራብ አካባቢ ደግሞ ሰለህለሃ በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።

በሕጻጽ መጠለያ ውስጥ የተፈናቃዮች አስተባባሪ የሆኑት ቄስ አብርሃ አርአያ ለቢቢሲ ትግርኛ በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያው ወደ 14 ሺህ ሰዎች እርዳታ የሚያገኙ ቢሆንም ባለፉት ወራት 300 የሚሆኑት ምንም ዓይነት እርዳታ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የሚሰጣቸው እህል ማሽላ መሆኑን የሚናገሩት አስተባባሪው፣ ማሽላውም የተበላሸ እንደሆነ እና ሌላ ተጨማሪ ገንቢ ምግብ አንደማያገኙ፣ ሕክምናም ሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የትግራይ የሲቪክ ማኅበራት ሕብረት ጥምረት ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ይካሎ ወልዱ በበኩላቸው በትግራይ ክልል በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ "ከፍተኛ የሆነ የምግብ እንዲሁም የእርዳታ እጥረት አለ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።