ከፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚላከው በጀት ተቋርጧል?

የትግራይ ክልል ፕላን ኮሚሽን ወ/ሮ ሃንሳ ተክላይ

የፎቶው ባለመብት, Tigray Plan Commision

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ክልል ፕላን ኮሚሽን ወ/ሮ ሃንሳ ተክላይ

ከፌደራል መንግሥቱ ለትግራይ ክልል የሚላከው በጀት ለሁለት ወራት ያህል አልተለቀቀም ሲሉ የትግራይ ፕላን ኮሚሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሃንሳ ተኽላይ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናገሩ።

ይህ የተሰማው ባለፉት ወራት በፌደራል መንግሥት እና ሕጋዊ ዕውቅናው በተሰረዘበት በህወሓት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል ተብሎ በሚሰጋበት ወቅት ነው።

ወደ ክልሉ የሚገባው ነዳጅም በቂ ባለመሆኑ በአጠቃላዩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ተፈጥሯል ሲሉ ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው የክልሉ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከተቋረጡ በጀት መካከል 844 ሚሊዮን ብር የካፒታል በጀት መሆኑን የተናገሩት የክልሉ ፕላን ኮሚሽን ኃላፊ፣ በተጨማሪም ከፌደራል መንግሥት በድጓማ የሚሰጥ እንዲሁም ከትግራይ ጦርነት በኋላ በየወሩ ይከፈል የነበረ ገንዘብ ይገኝበታል።

በአጠቃላይ ለ2018 ዓ.ም. ለትግራይ የተመደበው 18.8 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት፣ ለአስራ ሁለት ወራት ተካፍሎ፣ በየወሩ የሚላክ ሲሆን ነገር ግን ይህ ገንዘብ ከጥቅምት ወር ጀምሮ መቆሙን ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል።

ወደ ትግራይ ክልል የሚላከው በጀት መቋረጡን በተመለከተ እስካሁን ከፌዴራል መንግሥት የተሰጠ ይፋዊ ማብራርያ የለም።

ቢቢሲ ከገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲሱ የደመወዝ ማሻሻያ መሠረት ለመስከረም ወር 481 ሚሊዮን ብር ወደ ክልሉ የተላከ ቢሆንም ሰፊ ክፍተት በመኖሩ አዲሱ ጭማሪ ለመንግሥት ሠራተኞች ሊከፈል አለመቻሉን ወይዘሮ ሃንሳ አስታውሰዋል።

"የሁለቱም ወራት አንድ ላይ ጥቅምት ወር ላይ ለመስጠት አቅደን ነበር፤ ሆኖም የጥቅምት ወር አልመጣም አሁን ኅዳር 23 ላይ ደርሰናል፤ ምንም አልተላከም።"

ይህ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ በይፋ ጠይቀው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "አዎ ጠይቀናል፣ ነገር ግን ምላሽ አልተገኘም" ብለዋል።

ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም ወደ ትግራይ የተላከው ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ዓመታዊ በጀት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "የሚታረሙ ስህተቶች ስላሉበት" በሚል እንዲመለስ የሚጠይቅ ደብዳቤ በማኅበራዊ ሚዲያ ወጥቶ ነበር።

ቢቢሲ ደብዳቤው ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል።

ነገር ግን ወ/ሮ ሃንሳ ደብዳቤውን በተመለከት እነሱ ቢሮ ጋር የደረሰ ነገር አለመኖሩን እንዲሁም ለእርማት የተመለሰው በጀት ግልፅ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል።

"የተላከው የገንዘብ መጠን ስህተቱ አልታየንም" ያሉት ኃላፊዋ፣ በአጠቃላይ በጀት ለማገድ ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ ከመገመት ውጪ በይፋ የተሰጣቸው ማብራሪያ እንደሌለ ተነግረዋል።

'ከባድ ችግር ውስጥ ነን'

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በአክሱም የፅዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው የክልሉ በጀት ከፌዴራል መንግሥት እየተለቀቀ እንዳልሆነ እና ሌላ ዙር ግጭት እንዳይፈጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት "በበጀት እጥረት ምክንያት የወር ደሞዝ ለሠራተኞች እንኳን መክፈል የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል" ብለዋል።

የዓመታዊ በጀቱ መታገድ ያደረሰው ጉዳት አለ ወይ ብለው የተጠየቁት ወ/ሮ ሃንሳ "እንደ ክልል ገቢ መሰብሰብ እንኳን አልቻልንም። ገንዘብ መደብን ሠራተኞች ከፍለን እና አሰማርተን ነው መሰብሰብ የምንችለው፤ ያንን ማድረግ አልቻልንም" ብለዋል።

ከወረዳ ወደ ወረዳ እና ከከተማ ወደ ከተማ ልዩነቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊዋ "አንዳንድ ዋና ዋና ከተሞች (እንደ ሽረ፣ መቀለ እና አዲግራት ያሉ) ለጊዜው ከራሳቸው ገቢ ደመወዝ መክፈል ቢችሉም በዙሪያው ያሉ ወረዳዎች እና የገጠር አካባቢዎች ደመወዝ መክፍል አቁመዋል" በማለት ቅሬታ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት አንዳንድ የመንግሥት አገልግሎቶች እስከ መቆም ደርሰዋል በማለት ይህ ሁኔታ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት መፈጠሩን ተናገረዋል።

የክልሎች በጀት

የፌዴራል ምክር ቤት በሚያቀረበው ቀመር መሠረት ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ዓመታዊ በጀት ያገኛሉ።

በተጨማሪም በአገሪቱ ውስጥ በሚከሰቱ ለውጦች እና በመንግሥት ውሳኔዎች መሠረት ፕሮጀክት ተኮር እርዳታ እና ድጎማዎች ከፌደራል መንግሥት ለክልሎች ይሰጣል።

በኢትዮጵያ በቅርቡ የተመሠረቱትን ክልሎች ጨምሮ በአጠቃላይ 12 ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አሉ።

ዓመታዊ የበጀት ድልድል የሚካሄደው ከሕዝብ ብዛት እና ከሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በመነሳት ነው።

በመሆኑም በዚህ ዓመት ከፍተኛ የታክስ ገቢ ከሚሰበስቡ ክልሎች አንዷ ለሆነችው ትግራይ 18.8 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ቋሚ በጀት መመደቡን የፌደራል መንግሥት አስታውቋል።