"ተመርቃ ለፍሬ ትበቃለች እያልኩ ስጠብቅ ልጄ ተቀጠፈችብኝ " በደሴ የተገደለችው ወጣት አባት

በደሴ ከተማ ጥቃት ተፈጽሞባት ሕይወቷ ያለፈው ሊዛ ደሳለ

የፎቶው ባለመብት, Tilahun Ashagre

የምስሉ መግለጫ, ሊዛ በደሴ ከተማ ውስጥ የአራተኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ ነበረች

ወጣት ሊዛ ደሳለ የኮሌጅ ትምህርቷን እየተከታተለች በነበረችበት ደሴ ከተማ ውስጥ በአሰቃቂ ጥቃት መገደሏን ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለፈው ረቡዕ መስከረም 28/2018 ዓ.ም. ሞባይል ስልክ ለማሠራት ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ከቤቷ የወጣችው ሊዛ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጥቃት ተፈፅሞባት መንገድ ዳር ወድቃ ነበር የተገኘችው።ሊዛ ለሕክምና እርዳታ ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ብትወሰድም ሕይወቷን ማትረፍ አልተቻለም።

በከተማው ውስጥ በሚገኘው ድሪም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የአራተኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ሊዛ፣ በዚህ ዓመት ትምህርቷን አጠናቃ ለመመረቅ እየተዘጋጀች ነበር።

አባቷ መምህር ደሳለ ለፍሬ ትበቃለች ብለው በጉጉት ሲጠብቋት የነበረችው ልጃቸው በአሰቃቂ ጥቃት መቀጠፏ እጅጉን እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

አባቷ አቶ ደሳለ ለቢቢሲ ከባድ ሐዘን በተጫነው ድምጽ "በመምህር ደመወዝ አስተምሬ ተመርቃ ለፍሬ ትበቃለች እያልኩ ስጠብቅ ተቀጠፈችብኝ" ሲሉ ተናግረዋል።

በ21 ዓመቷ ወጣት ላይ የተፈጸመው ግድያ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ ድርጊቱ የተፈጸመበትን የደሴ ከተማ ማኅበረሰብንም በእጅጉ አሳዝኗል።

"በከተማዋ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ድርጊት ተፈፅሞ አያውቅም" ያሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ድርጊቱ ነዋሪዎችን እንዳሳዘነ እና እንዳስቆጣ ተናግረዋል። ወጣቷ አስቸኳይ ፍትሕ እንድታገኝም ጠይቀዋል።

የሊዛ የአክስት ልጅ የሆነችው ረቢዓ የሱፍ፣ ሊዛ ጥቃቱ በተፈፀመባት ወቅት የአንገት ሐብሏ፣ የእጅ ስልኳ እና ጫማዋ ተወስዶ እንደነበር ጠቅሳ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው ግን ለዝርፊያ እንዳልሆነ ታምናለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ዓይኗ፣ ጭንቅላቷ እና ጀርባዋ ላይ በቦክስ ክፉኛ ድብደባ ተፈጽሞባታል" ስትልም ጥቃቱ ከዝርፊያ የዘለለ እንደሆነ አስረድታለች።

የሊዛ አባት አቶ ደሳለ በበኩላቸው "በልጄ ላይ በቀል የፈጸሙባት ይመስለኛል" በማለት የበቀሉ ምክንያት 'የፍቅር ጥያቄን አለመቀበሏ' ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።

"ልጄ ሴት ናት፤ 21 ዓመቷ ነው። እናም ሁለት የተለያዩ ወንዶች ለፍቅር ጠይቀዋት፤ እርስ በርስ እልህ በመጋባት አንደኛቸው በቀል ፈጽመውባት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ነው ያለኝ" ብለዋል።

እስካሁን ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ አልታወቀም።

ቢቢሲ ከደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ሆኖም መምሪያው ማክሰኞ ጥቅምት 4/2018 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ ወጣት ሊዛ በከተማዋ በተለምዶ ሃቢታት ተብሎ በሚጠራው ቦርከና ቀበሌ አካባቢ "ባልታወቁ ሰዎች" በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ እንደተፈፀመባት አረጋግጧል።

በወንጀሉ ላይ የፍትሕ አካላትን ያካተተ የምርመራ ቡድን አዋቅሮ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንም መምሪያው ገልጿል።

"የምርመራ ቡድኑ በታክቲክ እና በቴክኒክ ማስረጃዎችን በማጣራት ወንጀል ፈጻሚውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሠራ ነው።የምርመራ ቡድኑ የደረሰበትን ውጤት ለሕዝብ እናሳውቃለን" ብሏል መምሪያው።

አባቷ መምህር ደሳለም ፖሊስ የምርመራ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ ተስፋ አድርገዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሴቶች እና በታዳጊዎች ላይ የሚፈፀሙ የተለያየ መልክ ያላቸው ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም የመብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ብቻ በተፈፀመባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለሥነ ልቦናዊ እና ለማኅበራዊ ቀውስ የተዳረጉት ሴቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

በአገሪቷ ውስጥ ያለው ግጭት፣ ሥራ አጥነት፣ የማኅበረሰብ ቸልተኝነት፣ የሕግ መላላት፣ የፍትሕ እጦት ችግሩን እንዳባባሰውም የሴቶች መብት ተከራካሪዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ይነገራሉ።

የሴቶች እና የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓመታት በፊት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ፣ በ2016 ዓ.ም. የወጣው የሥነ ሕዝብ እና የጤና ዳሰሳ በአገሪቷ 26 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው አመልክቷል ብሏል።

እነዚህ ጥቃቶች የተለያየ መልክ ያላቸው ሲሆኑ በዋናነት በአካላዊ፣ በወሲባዊ፣ በሥነ ልቦናዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች የሚገለጡ ናቸው።

በደሴ ጥቃት ተፈጽሞባት የሞተችው ሊዛ ደሳለ

የፎቶው ባለመብት, Tilahun Ashagre

የምስሉ መግለጫ, ሊዛ በሙያዋ ነርስ ከሆነችው ታላቅ እህቷ ጋር የጤና ተቋም የመክፈት ህልም ነበራት

የቅርብ ዘመዷ ብቻ ሳይሆን የሊዛ ጓደኛ የሆነችው ረቢዓ የሱፍ፣ ሊዛ ስልክ ለማሠራት አመሻሽ ላይ ወደ የሞባይል ጥገና ቤት ሄዳ ስልኩን አሠርታ ወደ ጓደኛዋ ቤት በማምራት ላይ እያለች ጥቃቱ እንደተፈፀመባት ለቢቢሲ ገልጻለች።

ረቢዓ እንደምትለው ሟች ሊዛ ጥቃቱ ሳይደርስባት በፊት ለጓደኛዋ ደውላላት ስለነበር ጥቃቱ ወደተፈጸመበት ስፍራ ቀድማ የደረሰችው ጓደኛዋ ነበረች።

ሊዛ ጥቃቱ ከተፈጸመባት በኋላ ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስዳ የሕክምና እርዳታ ቢደረግላትም ሕይወቷ ሊተርፍ እንዳልቻለም ገልጻለች።

ከጥቃቱ በኋላ "አልፎ አልፎ የድንጋጤ፣ የመርበትበት ስሜት ታሳይ ነበር። እስትንፋሷ ነበረች።በሕይወት ትተርፋለች ብለን ብንጠብቅም በዚያው ዕለት ሌሊት አረፈች" ብላለች ረቢዓ።

ረቢዓ በጥቃቱ የምትጠረጥራቸው ሰዎች ባይኖሩም ጥቃቱ የተፈጸመው ለተራ ዘረፋ ወይም በአጋጣሚ እንዳልሆነ ትናገራለች።

ለምርመራ ይረዳሉ የተባሉ መረጃዎችንም ለፖሊስ መስጠታቸውን የገለጸችው ረቢዓ፣ "የፖሊስን ምርመራ ሊያደናቅፍ ይችላል" በሚል ዝርዝር መረጃዎችን ከመናገር ተቆጥባለች።

ቤተሰቦቿ እንደሚሉት ሊዛ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደሴ ከተማ ውስጥ ስትኖር ጥቃትም ሆነ ለጥቃት የሚያሰጋ ነገር ገጥሟት አያውቅም።

"እንደ ወላጅ የምናወራቸው ነገሮች አሉ።ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ትዳር ሕይወት እንደምትገባ እንጂ እንደዚህ ዓይነት ስጋት እንዳለባት ነግራኝ አታውቅም" ብለዋል አባቷ አቶ ደሳለ።

የደሴ ከተማ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ለልጃቸው ፍትሕ እንደሚያገኙም ተስፋ አድርገዋል።

እስካሁን ፖሊስ እያደረገ ባለው ጥረትም ደስተኛ መሆናቸውንም መምህር ደሳለ ገልጸዋል።

ሊዛ ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አስመዝግባ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተመድባ ነበር።

ሆኖም ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ቤተሰቦቿ ከሚኖሩበት ከተማ የሚርቅ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አቋርጣ ደሴ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ድሪም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርቷን እየተከታተለች ባለችበት ወቅት ነበር ለህልፈት ያበቃት ጥቃት የተፈፀመባት።

ሊዛ ከታላቅ እህቷ ጋር የጋራ ህልም ነበራት። በሙያዋ ነርስ በሆነችው ታላቅ እህቷ ምክር የፋርማሲ ሙያን ለመማር የመረጠችው ሊዛ፣ ከእህቷ ጋር የራሳቸውን የጤና ተቋም ለመመሥረት ትምህርቷን በትጋት ስትከታተል ቆይታለች።

የፀጥታ ችግር በተደጋጋሚ በሚከሰትባት ቆቦ ከተማ በመምህርነት እያገለገሉ ያሉት አባቷ አቶ ደሳለ ሞላም ከሚያገኙት የተጣራ 8 ሺህ ብር ወርሃዊ ደመወዝ ግማሹን ለልጃቸው በመመደብ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲያስተምሯት ቆይተዋል።

ልጃቸው በዚህ ዓመት ትምህርቷን አጠናቃ ሊያስመርቋት በጉጉት እየተጠባበቁ ነበረ።

"ልጄ ለእኔ የተለየ ፍቅር ነበራት። በመምህር ደመወዝ አስተምሬ ፍሬዋ ሲደርስ ተቀጠፈችብኝ" የሚሉት መምህር ደሳለ፣ ልጃቸው ሊዛ ሲበዛ ተጫዋች፣ ኃላፊነት የሚሰማት፣ ለትናናሾቿ አርዓያ እና ተንከባካቢ እንደነበረች አውስተዋል።

ያልጠበቁት እና አስደንጋጭ ሐዘን እንዳጋጠማቸው የገለጹት መምህር ደሳለ፣ቤተሰባቸው በከፍተኛ ድንጋጤ እና በቀላሉ የማይወጣው ሐዘን ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

"ባለቤቴ ሐዘኗ ብርቱ ነው። ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ከሊዛ ጋር ተደዋውለው፣ መርዶው የመጣባት ማታ ነው። የእርሷ ነገር ከባድ ነው።ምን አልባት ፖሊስ በምርመራው የልጃችንን ገዳዮች ለፍትሕ የሚያቀርብልን ከሆነ በመጠኑ እንጽናና ይሆናል" ብለዋል።