"ህወሓትን በሕገ ወጥ መንገድ የማገድ እና በትግራይ ሕገ ወጥ ምርጫ የማካሄድ አዝማሚያ አለ" - ህወሓት

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም
የምስሉ መግለጫ, የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት በሕገ ወጥ መንገድ ዕገዳ እንደተጣለበት ገልጾ፤ በቀጣይም እሱን የማያካትት ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ አለ ሲል ከሰሰ።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም በሰጡት መግለጫ ላይ፤ "ህወሓትን በሕገ ወጥ መንገድ የማገድ እና በትግራይ ሕገ ወጥ ምርጫ የማካሄድ አዝማሚያ አለ" ብለው ሁኔታውን የዘፈቀደ ውሳኔ ሲሉ ጠርተውታል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕጋዊ ፓርቲነት ዕውቅናውን ያጣው ህወሓት ከኅዳር 8/2018 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 13//2018 ዓ.ም. የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን አካሂዷል።

ነሐሴ 7/ 2016 ዓ. ም. 14ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያከናውን፤ የሚጠበቅበትን ሂደት ሳይከትል እና ለምርጫ ቦርድ ሳያሳውቅ የሚያካሂደው ነው በማለት በቦርዱ ተቀባይነት የለውም የሚል ደብዳቤ እንደተጻፈለት ይታወሳል።

ከማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል በሰጡት መግለጫ በትግራይ "ሕገ ወጥ ምርጫ የማካሄድ ፍላጎት" እንዳለ ገልጸው፤ ይህም "ህወሓትን ዒላማ በማድረግ ሕዝቡን ለማጥቃት" እንደሆነ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ከህወሓት ሕጋዊ ሰውነት መሻር በተጨማሪ ከኤርትራ እና ከፌደራል መንግሥት ጋር ስላው ግንኙነት እንዲሁም ስለ ተፈናቃዮች ጉዳይም ተጠይቀዋል።

በ14ኛው የህወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ትግበራ በማዕከላዊ ኮሚቴው መገምገማቸውን አቶ ሚካኤል ገልጸዋል።

ከከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች እና ከአባላቱ እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገቢውን ሂደት የተከተለ አይደለም የተባለው የህወሓት 14ኛ ጉባዔ አወዛጋቢ እንደነበር ይታወሳል።

ጉባዔው በህወሓት ሊቀ መንበር እና በምክትሉ በሚመሩ የድርጅቱ አባላት መካከል ክፍፍልን ፈጥሮ ነበረ።

የህወሓት ጠቅላላ ጉባዔ መካሄድ መጀመሩን ተከትሎ የቀድሞው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) "የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚጥስ ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።

በ14ኛው አወዛጋቢ ጉባዔ ላይ በወቅቱ የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች አልተሳተፉም።

በወቅቱ አቶ ጌታቸው ባወጡት መግለጫ፤ "ጉባዔው ትግራይን እና ሕዝቡን አደጋ ውስጥ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም" ብለው ነበር።

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
የምስሉ መግለጫ, የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ከአሸባሪነት መዝገብ የወጣው ህወሓት፤ ከሕጋዊ ፓርቲነት ምዝገባ ተሰርዟል።

ከትግራይ ኃይሎች ተነጥለው የወጡት እና በተለምዶ "ሓራ መሬት" (ነጻ መሬት) ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች በህወሓት ኃይሎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል በሚል መከሰሳቸው ይታወሳል።

እነዚህ ታጣቂዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ እና ድርጅቱን የሚደግፉ የትግራይ ኃይሎች አዛዦች ከሥልጣን ለማስወገድ ወደ አፋር ክልል ሄደው መደራጀታቸውን ይናገራሉ።

ትግራይ ክልል ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ ከሚነገርላቸው ታጣቂዎች "ጀርባ ያለው የፌደራል መንግሥቱ ነው" ሲል ህወሓት መክሰሱ አይዘነጋም።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባዔ የተካሄደው በክልሉ ውጥረት በነገሠበት ወቅት ነው።

ባለፉት ወራት በትግራይ ኃይሎች፣ በነጻ መሬት ታጣቂዎች እና በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች መካከል ዳግም ትግራይ ውስጥ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ጥቅምት 2018 ዓ. ም. ላይ የአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ፤ የትግራይ ኃይሎች በወረዳው ቶንሳ ቀበሌ ላይ "በከፈቱት ጥቃት"፤ "ወደ 15 ኪሎ ሜትር ዘልቀው" መግባታቸውን እና "ስድስት መንደሮችን" መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የድሮን ጥቃት በመፈጸም በትግራይ ኃይሎች አባላት ላይ ጉዳት ማድረሱን ህወሓት ገልጿል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ህወሓት የፈጸማቸው ድርጊቶች ወደ ጦርነት ለመግባት "ከበቂ በላይ ምክንያቶች ናቸው" ሲሉ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መናገራቸውም ይታወሳል።

የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች ተቃውሞ
የምስሉ መግለጫ, የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች ተቃውሞ

ዶ/ር ደብረጽዮን ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል?

በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረን ሰፊ ልዩነት ተከትሎ የፓርቲው ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጉባዔ ረግጠው ወጥተዋል እየተባለ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲነገር ቆይቷል።

ሆኖም ግን የህወሓት ቃል አቀባይ "ሐሰት ነው" ሲሉ አስተባብለዋል።

በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው ላይ መወያያ አጀንዳ የሆነው በ14ኛው ጉባዔ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች አፈጻጸም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ቡድን "የአገር ክህደት" ፈጽሟል ሲል ህወሓት በተደጋጋሚ ከስሷል።

አሁን ላይ በዚህ ቡድን "የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን እየሠራ እንደሚገኝ" ፓርቲው አስታውቋል።

"የሕዝባችንን አንድነት ለማወክ በጎጠኝነት እና በኋላ ቀርነት ጥረት ቢደረግም ስለ አንድነት ውይይት ተደርጓል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከደብረጽዮን ቡድን ጋር ከፍተኛ መቃቃር ውስጥ ገብተው የቆዩት አቶ ጌታቸው፤ ከሁለት ዓመት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ቆይታ በኋላ መጋቢት 2017 ዓ. ም. ላይ ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ አስረክበዋል።

በተጨማሪም አቶ ጌታቸው ከበርካታ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ጋር በመሆን "ስምረት" የተባለ ተቃዋሚ ፓርቲ መሥርተው በሊቀ መንበርነት እየመሩ ነው።

የጉባዔው ተሳታፊዎች
የምስሉ መግለጫ, የጉባዔው ተሳታፊዎች

ያልተመለሰው የተፈናቃዮች ጥያቄ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለአምስት ዓመታት በመጠለያ ለመኖር ተገደዋል።

ያለሰብአዊ እርዳታ በችግር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ ነበረባቸው።

ሆኖም ግን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌደራል መንግሥትም ለተፈናቃዮች አለመመለስ እንዲሁም ለፕሪቶሪያ ስምምነት "አለመከበር" አንዳቸው ሌላቸውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ህወሓት በምዕራብ ትግራይ ያሉ "ታጣቂዎች እንዲሁም አዲስ ሰፋሪዎች እንዲወጡ" እና የራሱን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲዘረጋ ጠይቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ለተፈናቃዮች ወደቀያቸው አለመመለስ ህወሓትን ተጠያቂ አድርገው፤ በትግራይ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች "ራያ ላይ እንደመለስነው፣ ፀለምት ላይ እንደመለስነው፣ ወልቃይት ላይም መመለስ አለበት፤ ይህ የመንግሥት ፅኑ አቋም ነው" ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል "ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ለመመለስ እየሞከሩ ነው። መማረራቸው እውነት ነው። እየኖሩበት ያለው ሰቆቃ ግልጽ ነው። ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ናቸው። ያፈናቀሏቸው ሰዎች አሁንም እዚያው ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ትግርኛ ምላሽ ሰጥተዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በመቀለ ከተማ ያደረጉትን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሳሉ "በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በችግር ላይ ባሉ ሰዎች ሁኔታ ውስጥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አንዱ ተጠያቂ መሆኑን" ተናግረዋል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር አላሳካቸውም ከሚባሉት መካከል አንዱ የተፈናቃዮች አለመመለስ ነው።

ከትግራይ ክልል ተወክለው የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈራራሚ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አሰፋ አብርሃ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ተፈናቃዮችን በማስመለስ ረገድ ዋናው ኃላፊነት የፌደራል መንግሥት መሆኑን አስምረውበታል።

ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰብዓዊነት መሆኑን በመግለጽ "ግዛት ወይም ካርታ የማረጋገጥ ጉዳይ አይደለም። ግዛቱ የእኛ የሚሆነው ሕዝቡ በመሬቱ ላይ ሲኖርበት ነው። ሕዝቡ እዚያ ከሌለ ቦታው የእኛ አይደለም" በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች በጉባዔው አዳራሽ
የምስሉ መግለጫ, የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች በጉባዔው አዳራሽ

ከኤርትራ ጋር ግንኙት አለ?

ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር "እየሠራ ነው" የሚለው የፌደራል መንግሥት ክስ መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል።

አቶ ሚካኤል ግን "ስለ ጉዳዩ ጭምጭምታ ይሰማል። ሆኖም በፓርቲም በመንግሥትም ደረጃ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት አልተጀመረም" ሲሉ አስተባብለዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሠሩ ነው ብሎ መክሰሱ ይተወሳል።

ይሄንን ክስ ህወሓትም የኤርትራ መንግሥትም አስተባብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርትራ እና ህወሓት "በቅርቡ የፋኖ ታጣቂዎች የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልዲያን ለመቆጣጣር ባደረጉት ሙከራ ውስጥ ተሳትፈዋል" ሲል ያለፈው መስከረም ወር ላይ ከሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ማንኛውም ከውጭ አገራት ጋር የሚደረግ ግንኙነት መካሄድ ያለበት በፌደራል መንግሥት በኩል መሆኑን ጠቅሰው፤ "እነሱ [ህወሓት] ከውጭ መንግሥት ጋር ምን እያደረጉ ነው?" ሲሉ ውንጀላ አዘል ጥያቄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ማቅረባቸው አይዘነጋም።

የህወሓት ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽ "ከሻዕቢያ ጋር ወዳጅ በመሆን ብልጽግናን ለመውጋት የተደረገ ንግግር የለም። እኛ እያልን ያለው በጋራ የፕሪቶሪያ ስምምነትን እንተግብር ነው። ሁለታችንንም የሚጠቅመው እሱ ነው። የሚያስተሳስረንም እሱው ነው" ብለዋል።