ኢራን፣ ስደተኞች እና ታሪፍ - ትራምፕ በዴሞክራቶች በተወገዘው ንግግራቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀድሞው አስተዳደር የተረከቡት "የላሸቀ" ምጣኔ ሃብት ቢሆንም የአገሪቱ ኢኮኖሚ "ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲያንሰራራ" ማድረጋቸውን አስታወቁ።
በኮንግረስ ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታሪፎችን ውድቅ ማድረጉንም ኮንነዋል።
ትራምፕ የጣሏቸው ታሪፎች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ቢደረጉም "ፈቃድ በተሰጠው ሌላ የሕግ አማራጭ አማካኝነት" ተግባራዊ መሆኑ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት 'ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን' ንግግር ላይ ትራምፕ ያነሱት ሌላው ነጥብ "ስምንት ጦርነቶችን" ማስቆማቸው ነው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ብለውት እንደነበረው "ስምንት ጦርነቶች" እንዲቆሙ ማድረጋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም "የኢትዮጵያ እና የግብፅ" ይገኝበታል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ካደረጓቸው ንግግሮች የትራምፕ ረዥሙ በመሆን ተመዝግቧል። ትራምፕ ለ1 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ንግግር በማድረግ ከዚህ በፊት በቢል ክሊንተን ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብረዋል።
ትራምፕ በንግግራቸው ስደተኞችን በተመለከተ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አሞግሰዋል።
መንግሥታቸው ሕገ ወጥ ስደትን በመቀነስ እና ደቡባዊ የአገሪቱን ድንበር በማስጠበቅ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሪፐብሊካኖች የትራምፕን ንግግር በጭብጨባ ሲደግፉ ተቃውሟቸውን በአደባባይ ያሳዩ ዴሞክራቶችም ነበሩ።
የቴክሳሱ ዴሞክራት የሕዝብ እንደራሴ አል ግሪን "ጥቁሮች ዝንጀሮ አይደሉም" የሚል ጽሑፍ ከፍ አድርገው በማሳየታቸው ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርጓል።
ከሲ-ኤስፒኤኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ዛሬ ልጋፈጠው ፈልጌያለሁ። ጥቁሮች ዝንጀሮ እንዳልሆኑ እነግረዋለሁ። ባህሪውን ጥቁሮች እንደማይታገሱት ማወቅ አለበት" ብለዋል።
ትራምፕ፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ከለጠፉ በኋላ አጥፍተውታል።
የቴክሳሱ ዴሞክራት የሕዝብ እንደራሴ አል ግሪን "እንዲህ ያለ ድርጊት እንዲቀጥል ከፈቀድን ሕገ መንግሥቱ ትርጉም ያጣል" ሲሉ ትራምፕን አውግዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ በሚኒሶታ ግዛት በሶማሊ ማኅበረሰብ አባላት ማጭበርበሮች ተፈጽመዋል ብለው መናገራቸውን ተከትሎ ዴሞክራቶች ንግግሩን ረግጠው ወጥተዋል።
የሜኒሶታ ዴሞክራት የሕዝብ እንደራሴ ኢልሐን ኦማር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ትራምፕን "ውሸታም" ብለው ተሳድበዋል።
ከአጠገባቸው የነበሩ ሌላ ዴሞክራት የኮንግረስ አባል ለኢልሐን ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ እጃቸውን ጨብጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ የአገሪቱን ብሔራዊ ዘብ ወደተለያዩ ከተሞች ያሰማሩት ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጠር እንደሆነ ተናግረዋል።
የቨርጂኒያ አገረ ገዢ አቢጌል ስፓንበርገር በበኩላቸው ስደተኞች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ "ቤተሰብን የሚበትን ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።
ትራምፕ ሌላው ያነሱት የኢራንን ጉዳይ ነው። ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በድጋሚ ተናግረዋል።
ትራምፕ "የእኔ ምርጫ ችግሩን በዲፕሎማሲ መፍታት ነው። አንድ ጉዳይ ግን እርግጥ ነው። እሱም፤ የዓለም ቁጥር አንድ የሽብር ደጋፊ የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት አልፈቅድም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ አሜሪካ ውስጥ ተንሰራፍቷል ያሉትን ማጭበርበር ለማስቆም ምክትላቸው ጄዲ ቫንስን መሾማቸውን በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
አሜሪካውያን "ቢሊዮን ዶላሮችን" እያጡ መሆኑን ገልጸውም ላለፉት አራት ወራት በጄዲ ቫንስ የሚመራው ቡድን ንቅናቄ ማድረጉን ቀጥሏል ብለዋል።
በሌላ በኩል፤ የጤናው ዘርፍ "ከፍተኛ ምዝበራ እየተደረገበት" እንደሆነ እና ዜጎች ለብዙ ወጪ መዳረጋቸውን ትራምፕ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባማ የተዘረጋው ማኅበረበሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓት (ኦባማኬር) ለዚህ ችግር መነሻ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ትራምፕ በእሳቸው አስተዳደር ሥር የዋጋ ንረት እንደረገበ ገልጸዋል።
"በአገራችን ታሪክ እጅግ የከፋው የኑሮ ውድነት ገጥሞን ነበር። ባለፉት 12 ወራት ግን በአምስት ዓመት ውስጥ ያልታየ ለውጥ ማምጣት ችለናል" ብለዋል።
ትራምፕ በሚያራምዱት "ጠንካራ የድንበር ጥበቃ" አማካኝነት አገራቸው ደኅንነቷ የተጠበቀ መሆኗን እና እንደ ፌንታኔል ያሉ መድኃኒቶች እንዳይገቡ መከላከል መቻላቸውን ተናግረዋል።
ዴሞክራቱ ሐኪም ጀፍሪስ በበኩላቸው አጠቃላይ የትራምፕ ንግግር "በቀውስ የተሞላ" ነው ሲሉ ተችተዋል።
"ለሁለት ሰዓት ገደማ ትራምፕ ውሸት፣ ፕሮፓጋንዳ እና ጥላቻ ነዝቷል" ብለዋል።
"ትራምፕ ከመቼውም በላይ ኑሮ እንዲወደድ አድርጓል። የአሜሪካውያንን የጤና ሥርዓት አዛብቷል። በማኅበረሰቦች ላይ በመንግሥት የተደረገ ነውጥ አነሳስተዋል" ሲሉም አክለዋል።















