ትራምፕ ምን ያህል ጦርነቶችን አስቁመዋል? የኢትዮጵያ እና የግብፅን ውጥረት በማርገብ ሚና አላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰባት ወር ውስጥ ሰባት ጦርነትን ማስቆማቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ በትናንትናው ዕለት በመንግሥታቱ ድርጅት ባደረጉት ንግግር በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ብቻ ሰባት ጦርነቶችን ማስቆማቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርምፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰባት ወር ውስጥ ሰባት ጦርነትን ማስቆማቸውን በመግለጽ በማኅበራዊ ሚደያው ላይ አጋርቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትራምፕ አስቁመዋቸዋል ካላቸው ጦርነቶች መካከል በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል የተካሄደ እንደሚገኝበት ዘርዝሯል።
ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ እና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት የነበራቸውን "ግጭት" በማስቆም "ሰላም" ማምጣታቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በሰኔ ወር ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሥልጣን ዘመናቸው ጣልቃ በመግባት ካስቆሟቸው ግጭቶች መካከል በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል "የተካሄደውን" በማለት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት በመካከላቸው ውጥረት ቢነግስም ወደ ግጭት አልገቡም።
ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ እና ግብፅ "በግዙፍ ግድብ ምክንያት ግጭት ውስጥ" እንደነበሩ ተናግረው ግድቡ፤ "በአስገራሚው የናይል ወንዝ ላይ ተጽዕኖ ያለው" እንደሆነ ጠቅሰው ነበር።
ትራምፕ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል "ሰላም ማምጣታቸውን" ቢያነሱም ፕሬዝዳንቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ የነበራቸው ሚና በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በበጎ አይታይም።
ትራምፕ በ2013 ዓ.ም. በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ማጠናቀቂያ ወራት ላይ ግብፅ ግድቡን "ልታፈነዳ ትችላለች" የሚል ንግግር ማድረጋቸው ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የትራምፕ ንግግር የቆጠረው "በሥልጣን ላይ ባለ" የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደተደረገ "የጦርነት ቅስቀሳ" ነበር።
ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ለሁለት እና ሦስት አስርት ዓመታት ሊቆሙ አይችሉም የተባሉ ጦርነቶችን አስቁምያለሁ ብለዋል።
ትራምፕ በዚህ ጥረታቸው የሰላም ኖቤል ሽልማት እንደሚገባቸው ገልጸው ከዚያ ይልቅ የሰው ሕይወት ማትረፍ መቻላቸው እንደሚበልጥባቸው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በዋነኛነት አሸማጋይ ናቸው።
ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም. በዋይት ሐውስ "ስድስት ጦርነቶችን ቋጭቻለሁ። የተኩስ አቁም የሚለውን ሐረግ ሳልጠቅስ ነው እነዚህ ስምምነቶች ላይ መድረስ የቻልኩት" ሲሉ ተናግረዋል።
በማግስቱ እነዚህ ቋጨኋቸው ያሏቸው ጦርነቶች ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የኖቤል የሰላም ሽልማት "የሰላም ዋነኛ መሪውን" አልፏቸዋል በማለት እንዲያበቁ አድርገዋል የተባሉ ጦርነቶችን ዘርዝሯል።
አንዳንዶቹ ግጭቶች ምንም እንኳን ለረጅም ጊዜ በነበሩ ውጥረቶች መንስዔ ምክንያት የተከሰቱ ቢሆኑም ለቀናት የቆዩ ናቸው።
ትራምፕ በአሸማጋይነት ግጭቶችን እንዲቆሙ ያስቻሏቸው አንዳንድ የሰላም ስምምነቶቸ ዘላቂነታቸው ጥያቄ ውስጥ ነው።
ትራምፕ ስለ ግጭቶቹ በሚናገሩበት ወቅት "የተኩስ አቁም" የሚለውን ሐረግ በተደጋጋሚ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ ቬሪቫይ (የመረጃ ማጣሪያ) እነዚህን ግጭቶች እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመቋጨት ተጫውቸዋለሁ የሚሉትን ሚና ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ እና ግብፅ
ኢትዮጵያ እና ግብፅ ጦርነት ላይ ባይሆኑም ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ሙሌት ጋር ተያይዞ ለዓመታት ውዝግብ ውስጥ ናቸው።
14 ዓመታትን የፈጀው እንዲሁም አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪን የጠየቀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር ሙሌት ተጠናቆ ምረቃው በመጪው መስከረም እንደሚካሄድ ኢትዮጵያ በቅርቡ አሳውቃለች።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ይህንኑ በመድገም ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለንግግሮቹ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
ለግብፅ በግልጽ በመወገን አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ትራምፕ ሰኔ ወር ላይ ሁለቱ አገራት "በግዙፉ ግድብ ምክንያት ግጭት ውስጥ" እንደነበሩ በመልዕክታቸው አስፍረዋል። ግድቡ "በአስገራሚው የናይል ወንዝ ላይ ተጽዕኖ ያለው" እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም አለ፤ በእኔ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ቢያንስ አሁን ላይ [ሰላም አለ]። እናም እንዲህ ሆኖ ይቆያል!" ሲሉ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ትራምፕ ሐምሌ ላይ ከኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ ባደረጉት ውይይት [ሕዳሴ] ግድብን አገራቸው "በገንዘብ ደግፋለች" እንዲሁም ግድቡ "ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ነው" ሲሉ አወዛጋቢ ንግግር አድርገዋል።
"እኔ ግብፅን ብሆን በናይል ወንዝ ውስጥ ውሃ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። እሱ ላይ እየሠራን ነው። ችግሩ መፍትሄ ያገኛል" ብለዋል።
ትራምፕ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የሰጡትን አስተያየት አስመልክቶ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ"ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢትዮጵያን ግድብ በተመለከተ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያስጠብቅ ፍትሃዊ ስምምነት እንዲደረስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም ናይል ለግብፅ የሕይወት ምንጭ አድርገው ዕውቅና መስጠታቸውን ግብፅ ታመሰግናለች" ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በይፋ መግለጫ ባይሰጡም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ግዙፉ የሕዳሴ ግድብ መቶ በመቶ የተገነባው "ያለምንም የውጭ እርዳታም ሆነ ብድር በራስ አቅም" መሆኑን አስታውቋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ አገራቸው በናይል (አባይ) ላይ ያላት የውሃ ድርሻ እንዲነካ እንደማትፈቅድ ከሳምንት በፊት ተናግረው ነበር።
"ግብፅ በውሃ ደኅንነቷ ላይ የተደቀነን የኅልውና ስጋት ችላ ትለዋለች ብሎ የሚያስብ ማንኛውም አካል ተሳስቷል። ሁኔታውን መከታተላችንን እንቀጥላለን፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የሕዝቦቻችንን የኅልውና ሃብቶች ለማስጠበቅ ማንኛውንም እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ አልሲሲ አስጠንቅቀዋል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ትቃወማለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ብትቆይም ከግብፅ በኩል ይህንን የመቀበል አዝማሚያ አልታየም።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
እስራኤል እና ኢራን
እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ ነው ያለችውን ጥቃት ሰኔ 6/2017 ዓ.ም. መፈጸሟን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ለ12 ቀናት የቆየ ግጭት መካሄዱ ይታወሳል።
በዚህ ጥቃት የኢራን ጦር ኃይሎች አንደኛው ኃያል ቅርንጫፍ የሆነው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆሴይን ሳላሚ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም በርካታ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ተገድለዋል።
ትራምፕ እስራኤል ጥቃት ከመፈጸሟ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኤራን ላይ ለማካሄድ ስላቀደችው ዘመቻ እንደነገሯቸው አረጋግጠዋል።
አሜሪካ ለእስራኤል ወግና የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ግጭቱን በአጭሩ የመቋጨት እርምጃ እንደሆነ ተቆጥሯል።
ትራምፕ ሰኔ 16/2017 ዓ.ም. "ኢራን የተኩስ አቁም እንደምትጀምር፤ በ12ኛው ሰዓት እስራኤል የተኩስ አቁም እንደምትቀጥል፤ በ24ኛው ሰዓት የ12 ቀናቱን ጦርነት የቋጨ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደረሳል" ሲሉ አወጁ።
ግጭቱ ከተቋጨ በኋለ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አገራቸው "ወሳኙን ድል" እንደተቀዳጀች በገለጹበት ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነትን አልጠቀሱም።
እስራኤል አሁንም ኢራንን ልታጠቃ እንደምትችል በተደጋጋሚ ስትዝት ትሰማለች።
"ዘላቂ ሰላም ላይ ወይም የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ክትትል በተመለከተ የተደረሰ ስምምነት የለም" ሲሉ በዋሽንግተን መቀመጫውን ያደረገው የብሩኪንግስ የምርምር ተቋም ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ማይክል ኦ ሃንሎን ተናግረዋል።
"ስለዚህ ያለው ነገር የተኩስ አቁም ስምምነት እንጂ ጦርነቱን የቋጨ አይደለም። ሆኖም እስራኤል በአሜሪካ እገዛ ኢራንን ማዳከሟ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ስላለው የተወሰነ ሚና ተጫውተዋል" ብለዋል።
ፓኪስታን እና ሕንድ
የኒውክሌር የጦር መሳሪያ በታጠቁት ሕንድ እና ፓኪስታን መካከል ያለው ውጥረት ለዓመታት የዘለቀ ቢሆንም በግንቦት ወር ላይ ሕንድ በምታስዳድራት ካሸሚር ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ግጭት ተነስቶ ነበር።
ከሁለቱ አገራት የአራት ቀናት ግጭት በኋላ ትራምፕ ሕንድ እና ፓኪስታን "አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን" በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ለጠፉ።
ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት "በአሜሪካ ሸምጋይነት ረዥም የምሽት ድርድር ውጤት ነው" አሉ ትራምፕ።
ፓኪስታን ትራምፕ ተጫውተውታል ያለችውን "ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነት" ጠቅሳ ከማመስገን በተጨማሪ ለኖቤል የሰላም ሽልማት አጨቻቸው።
ሕንድ በበኩሏ የአሜሪካን ተሳትፎ አጣጠጥላ "የተኩስ አቁም ንግግሮች የተካሄዱት በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል በሁለቱ ወታደራዊ ኃይሎች መካከል በነበረው የቀጥታ ግንኙነት መስመር ነው" ሲሉ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ምስሪ አስታውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩዋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሩዋንዳ የሚደገፉት ኤም23 የተሰኙት አማፂያን በማዕድን የበለጸገችውን ምሥራቃዊ ግዛት ከጥቂት ወራት በፊት መቆጣጠራቸውን ትከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ዘመናት ያስቆጠረ ግጭት የበለጠ ተባብሷል።
በሰኔ ወር ሁለቱ አገራት ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት በዋሸንግተን ተፈራረሙ።
ትራምፕ ይህ ስምምነት በአገራቱ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ እንደሚረዳ ተናገሩ።
ሆኖም የአገራቱ የተኩስ አቁም ስምምነትን በመጣስ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ሲሆን፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ይህንን ውዝግብ ከሩዋንዳ ጋር አገናኝተውታል።
የኤም23 አማፂያን ከዚህ የሰላም ስምምነት ራሳቸውን እንደሚያገሉም በቅርቡ ተናግረዋል።
"በኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል አሁንም ጦርነት እየተካሄደ ነው፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አልጸናም" ሲሉ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርጋሬት ማክሚላን ገልጸዋል።
ታይላንድ እና ካምቦዲያ
ትራምፕ "የታይላንድን ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን እየተቀጣጠለ ያለው ጦርነት እንዲቆም እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ አሁን እደውለለታለሁ" ሲሉ ሐምሌ 19/ 2017 ዓ.ም. በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ለጠፉ።
ሁለቱ አገራት በድንበር አካባቢ ያደረጉት ሳምንት ያልቆየ ግጭት መቋጨቱን ከጥቂት ቀናት በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ።
አገራቱ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ" ተስማምተዋል አሉ።
ማሌዥያ የሰላም ድርድሮችን እያካሄደች የነበረ ቢሆንም ትራምፕ የተናጠል ድርድሩን የማታቆም ከሆነ አገሪቱ ላይ ታሪፍ እጥላለሁ ሲሉ ዛቱ።
በማሌዥያ ላይ ብቻ ሳይሆን ታይላንድ እና ካምቦዲያ ግጭቱን የማያቆሙ ከሆነ በእነሱም ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስፈራሩ።
ሁለቱም አገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው የወጭ ንግዶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ናቸው።
ታይላንድ እና ካምቦዲያ በድንበር ላይ ያለውን ግጭት ለማቆም ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም. ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሜንያ እና አዘርባጃን
የአርሜንያ እና የአዘርባጃን መሪዎች ትራምፕ በአገራቱ የሰላም ስምምነትን ለማስፈን ላደረጉት ጥረት የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘት ይገባቸዋል ሲሉ ተናገሩ።
ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳቸው በዋይት ሐውስ የታወጀው ከሁለት ሳምንት በፊት ገደማ ነበር።
"ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ ገፋፍተዋቸው ሊሆን ስለሚችል ሚናቸው ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል" ሲሉ ኦ ሃንሎን ይናገራሉ።
በናጎርኖ-ካራባክህ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ ለ40 ዓመታት ያህል ጦርነት ውስጥ የነበሩት የሁለቱ አገራት መንግሥታት መጋቢት ወር ላይ ለጦርነቱ ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ሰርቢያ እና ኮሶቮ
ትራምፕ ሰኔ አጋማሽ ላይ በሰርቢያ እና በኮሶቮ መካከል ግጭት እንዳይነሳ ማድረግ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።
"ሰርቢያ እና ኮሶቮ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ነበር፤ ትልቅ ጦርነት ይሆን ነበር። 'ወደ ውጊያ የምትገቡ ከሆነ ከአሜሪካ ጋር ንግድ አይኖርም' አልኳቸው። እነሱም 'ጦርነት ውስጥ አንገባም' አሉ" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
"ሰርቢያ እና ኮሶቮ አልተዋጉም ወይም አልተተኳሱም፤ ስለዚህ የቆመ ጦርነት የለም" ሲሉ ፕሮፌሰሩ ማክሚላን ያስረዳሉ።
ኮሶቮ ከሰርቢያ መገንጠሏን ተከትሎ እውቅና በመንፈጓ አገራቱ ግጭት ላይ እንደነበሩ ይታወሳል።
በአንድ ወቅት ሁለቱ አገራት የምጣኔ ሃብት ግንኙነታቸውን ወደ መደበኛው ለመመለስ በአውሮፓውያኑ 2020 በዋይት ሐውስ ስምምነት ላይ ቢደርሱም በወቅቱም ቢሆን ጦርነት ላይ አልነበሩም።















