ትራምፕ፤ ታሪፋቸውን ውድቅ ያደረጉባቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች "ሞኞች" ብለው አዲስ 10% ታሪፍ ጣሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጣሏቸውን ታሪፎች ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ አዲስ 10% ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታወቁ።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አብዛኞቹ የትራምፕ ታሪፎች ሕጋዊ ተቀባይነት የላቸውም ካሉ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ዳኞቹን እያብጠለጠሉ ይገኛሉ።
ትራምፕ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ "መጥፎ ነው" ብለው፤ ታሪፉ ውድቅ እንዲደረግ የደገፉትን ዳኞች "ሞኞች" ሲሉ አንጓጠዋል።
ዋይት ሀውስ በአውሮፓውያኑ 2025 ይፋ ካደረጋቸው ታሪፎች መካከል አብዛኞቹን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል።
ውሳኔው የተላለፈው 6 ለ 3 በሆነ አብላጫ ድምጽ ነው። ትራምፕ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ እየተጠቀሙበት ነው ሲልም ፍርድ ቤቱ ኮንኗል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የትራምፕን ታሪፍ ሲቃወሙ ለነበሩ ነጋዴዎች ትልቅ ድል ነው። በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር በታሪፍ ምክንያት በመንግሥት የተወሰደ ገንዘብ ተመላሽ እንዲደረግም በር ይከፍታል።
ሆኖም ውሳኔው በዓለም አቀፍ ገበያው አዳዲስ ጥያቄዎችን ማጫሩ አልቀረም።
ትራምፕ በዋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር በታሪፍ የተወሰደ ገንዘብ ያለ ፍርድ ቤት ክርክር ተመላሽ አይሆንም ብለዋል። ይህም ዓመታት ሊወስድ ይችላል።
ታሪፍ የአሜሪካን ኢንቨስትመንት እና ንግድ ያበረታታል ብለው የሚከራከሩት ትራምፕ፤ ታሪፋቸውን ተቀባይነት እንዲያገኝ ሌሎች የሕግ አማራጮችን እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትራምፕ አምና በአብዛኞቹ የዓለም አገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ውድቅ ያደርጋል።
መጀመሪያ ላይ ሜክሲኮ፣ ካናዳ እና ቻይና ላይ አነጣጥሮ የነበረው ታሪፍ ሌሎች በ100ዎች የሚቆጠሩ አገራትን እንዲሸፍን ትራምፕ መወሰናቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ታሪፍ የጣሉት እአአ በ1977 የወጣ ሕግን መሠረት አድርገው ሲሆን፤ አሜሪካ አደጋ ውስጥ ስትወድቅ ፕሬዝዳንቷ የገበያ ሁኔታን "እንዲያስተካክሉ" ይፈቅዳል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ሆኖም ግን አሜሪካውያን ነጋዴዎች ምርቶችን ወደ አገራቸው ለማስገባት ከፍተኛ ቀረጥ እየተጠየቁ በመሆኑ የሸቀጦች ዋጋ እንደሚንር በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ፍርድ ቤቱ ታሪፉን ውድቅ ማድረጉን ካስታወቀ በኋላ ትራምፕ ዳኞችን እያብጠለጠሉ ነው። ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከገጠሟቸው ጉልህ ፈተናዎች መካከል የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይጠቀሳል።
ትራምፕ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ "በጣም አሳዛኝ ነው" ብለዋል። ውሳኔውን የደገፉት ዳኞች "እጅግ አሳፋሪ ናቸው" ሲሉም ተችተዋል።
"በአንዳንዶቹ ዳኞች አፍሬባቸዋለሁ። ለአገራችን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ድፍረት የላቸውም" ሲሉ በዋይት ሀውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ትራምፕ ታሪፋቸውን የተቃወሙ ሪፐብሊካን እንዲሁም ዴሞክራት ዳኞችን በጽኑ አውግዘዋል።
የትራምፕ ታሪፍ ውድቅ እንዲደረግ ከደገፉት ስድስት ዳኞች መካከል ሦስቱ ወግ አጥባቂዎች ሲሆኑ የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ ሊበራል ናቸው።
ውሳኔውን ከደገፉት ሦስት ወግ አጥባቂ ዳኞች ውስጥ ደግሞ ሁለቱ (ኤሚ ኮኒ ባሬት እና ኒል ጎርሹን) የተሾሙት በትራምፕ ነው።
ትራምፕ ዳኞቹን "የአገር ፍቅር የሌላቸው እና ሕገ መንግሥታችንን የማያከብሩ" ሲሉም ወቅሰዋል።
በሌላ በኩል ጥቃቅን እና አነስተኛ ነጋዴዎች በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በሚኒሶታ የቢዚ ቤቢ ምርቶችን የምታቀርበው ቤት ቤንኪ "አንድ ሺህ ኪሎ ከሰውነቴ ላይ የተቀነሰልኝ ያህል ነው የቀለለኝ" ብላለች።
ኒክ ሆልም የተባለው ነጋዴም "አነስተኛ ቢዝነስ ላላቸው ሰዎች እፎይታ ነው" ብሏል።
ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የጣሉት አዲስ 10% ታሪፍ መነሻ ያደረገው ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ውሎ የማያውቅ 'ሴክሽን 122' የተባለ ሕግ ነው።
ይህ ሕግ ፕሬዝዳንቱ እስከ 15% የሚደርስ ታሪፍ ለ150 ቀናት ያህል እንዲጥሉ የሚያስችል ነው። ከ150ኛው ቀን በኋላ ኮንግረስ ጣልቃ መግባት ይኖርበታል።
ታሪፉ በአውሮፓውያኑ ከጥር 24 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
በታሪፉ ውስጥ ልዩ ማዕድኖች፣ የተፈጥሮ ኃብቶች፣ እንደ ብርቱካን እና ሥጋ ያሉ የግብርና ምርቶች፣ መድኃኒቶች፣ አንዳንድ ተሽከርካሪዎች እና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች አይካተቱም።















