ዶናልድ ትራምፕ የጣሉት ታሪፍ እንዴት ተሰላ?

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ አገራት ሸቀጦች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።ትራምፕ ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲን ተከትለዋል ያሏቸውን "የለየላቸው አጥፊዎች" ብለው በጠሯቸው አገራት ላይ ደግሞ ከፍ ያለ ታሪፍን ጭነዋል።

ትራምፕ ከውጭ አገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣሉት ታሪፍ በምን ላይ የተመሰረተ ነው? ከቁጥሮቹ በስተጀርባ ስሌት አለው?

ታሪፎቹ እንዴት ተሰሉ?

ትራምፐ በዋይት ሃውስ በሚገኘው ሮዝ ጋርደን ሆነው በአገራቱ ያሉ ታሪፎችን የሚገልጽ ግዙፍ የካርቶን ቻርት ሲያሳዩ የተለያዩ መላምቶች ተሰንዝረው ነበር።

የነዚህ ታሪፎች መነሻ የሆነው ነባር ታሪፎች እና የአገር ውስጥ ንግድን ለመጠበቅ የወጡ መመሪያዎች ሊሆኑ ይችላል ተብሎ ተገምቶ ነበር።

ሆኖም ቆየት ብሎ ዋይት ሃውስ ታሪፎቹን ለማስላት ተጠቅምቤታለሁ ያለውን የተወሳሰበ የሂሳብ ቀመር የሚመስል ስሌት ይፋ አደረገ።

ነገር ግን የተወሳሰበ የሚመስለው ቀመር ቀለል ያለ ስሌት ሆኖ ተገኝቷል።

አሜሪካ ለታሪፏ መነሻ ያደረገችው የንግድ ሚዛኗን ወይም የንግድ ጉድለት (ትሬድ ዴፊሲት) ነው።

የንግድ ጉድለት (trade deficit) የሚባለው የአንድ አገር የወጪና የገቢ ንግድ ማመጣጠን ሳይቻል ሲቀር ነው።

አንዲት አገር ከወጪ ንግዷ ይልቅ የገቢ ንግዷ ከጨመረ በዚያን ወቅት የንግድ ሚዛን አለመመጣጠን ይከሰታል።

የንግድ ጉድለትን፣ በአጠቃላይ ከአንድ አገር ከተገኘው የገቢ ንግድ በማካፈል በመጨረሻም የተገኘውን አኃዝ ለሁለት በማካፈል ነው ታሪፉ የተሰላው።

ለምሳሌ አሜሪካ ለቻይና ከምትሸጠው በላይ ከአገሪቱ የምታስገባው ይበልጣል።

በዚህም መሰረት በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለው የንግድ ጉድለት 295 ቢሊዮን ዶላር ነው።

በአጠቃላይ አሜሪካ ከቻይና የምታስገባው ምርት 440 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ታሪፉንም ለማስላት የንግድ ጉድለቱን 295 ቢሊዮን በ440 ተካፍሎ ሲጠጋጋ ወደ 67 በመቶ ይሆናል።

ይህ አኃዝም በሁለት ተካፍሎ ነው በቻይና ላይ የተጣለው 34 በመቶ ታሪፍ ላይ የተደረሰው።

ይህ ቀመር በተመሳሳይ በአውሮፓ ህብረት የንግድ ልውውጥ ላይ ሲሞከር ትራምፕ የጣሉት 20 በመቶን ታሪፍ ስሌት አስገኝቷል።

የትራምፕ የታሪፍ ስሌት ቀመር
የምስሉ መግለጫ, የትራምፕ የታሪፍ ስሌት ቀመር

የትራምፕ ታሪፎች አጻፋዊ ምላሽ ናቸው?

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እነዚህ ታሪፎች የተጣሉት በአጸፋዊ መልኩ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

አጸፋዊ ሲባል እነዚህ አገራት ቀደም ሲል በአሜሪካ ምርቶች ላይ በጣሉት ታሪፍ ምላሽ ላይ የተመሰረተ ለማለት ነው።

ነገር ግን የዋይት ሃውስ ይፋዊ ስሌት ከዚህ ቀደም አገራት በአሜሪካ የጣሉዋቸውን ታሪፎች መሰረት አድርጎ እንዳልተሰላ ግልጽ አድርጓል።

ታሪፉ የተሰላው አሜሪካ ከአገራት ጋር ያላትን የንግድ ጉድለት (ትሬድ ዴፊሲትን) ለማጥበብ በሚል ነው።

ሆኖም ትራምፕ የንግድ ጉድለት በሌለባቸው እና ምርቶቻቸውን ለአሜሪካ ከሚልኩት በላቀ ከአሜሪካ በሚገዙት ላይም ታሪፍን ጥለዋል።

ለምሳሌ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የንግድ ልውውጣቸው የንግድ ጉድለት ባይታይበትም፤ ዩኬ 10 በመቶ ታሪፍ፣ የፕሬዚዳንቱ የታሪፍ መነሻ ምጣኔ ተጥሎባታል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ100 በላይ አገራት የትራምፕ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።

የትራምፕ ደጋፊዎች

ታሪፍ የአሜሪካን የንግድ ሚዛን ጉድለቷን ያስተካክለው ይሆን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ አገራቸው በአለም አቀፍ ንግድ ላይ ተጠቃሚ አይደለችም እንዲያውም እየተጎዳች ነው ብለው ያምናሉ።

በእርሳቸው አመለካከት ሌሎች አገራት የአሜሪካን ገበያ በርካሽ ዕቃዎች እያጥለቀለቁት ነው፤ ይህም የአገሪቱን ኩባንያዎች የሚጎዳ እንዲሁም ከስራ ውጭ እያደረጋቸው ነው።

ትራምፕ እንደሚሉት እነዚህ አገራት የአሜሪካ ምርቶች በገበያቸው ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የተለያዩ ክልከላዎችን እያስቀመጡ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ትራምፕ እነዚህ ታሪፎችን በመጠቀም የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በማስተካከል የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያብብ እና ስራዎችን ለመፍጠር ተስፋ አድርገዋል።

ነገር ግን ይህ ታሪፍ የሚፈለገውን ውጤት ያስገኝ ይሆን?

ቢቢሲ ለዚህ ምላሽ በርካታ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

ባለሙያዎቹ ታሪፉ በአሜሪካ እና በእያንዳንዱ አገራት መካከል ያለውን የሸቀጦች ጉድለት ሊቀንስ ቢችልም ፤ በአሜሪካ እና በተቀረው ዓለም መካከል ያለውን አጠቃላይ የንግድ ጉድለት አያመጣጥነውም ይላሉ።

"በአሜሪካ እና በእነዚህ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ጉድለት ይቀንሳል። ነገር ግን ግምት ውስጥ ያልገቡ ሰፋ ያሉ ተጽዕኖዎች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው" ሲሉ በለንደን የኪንግ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኔት ጆናታን ፖርትስ ይናገራሉ።

ለዚህም አንደኛው ምክንያት የአሜሪካ አጠቃላይ የንግድ ጉድለት የተፈጠረው የአንድን አገር ገበያ እና ንግድ ለመጠበቅ በተቀመጡ ክልከላዎች ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት በሚመራበት መልኩ ምክንያት ነው ይላሉ።

አንደኛ አሜሪካውያን ከሚያገኙት በላይ ወጪ እንዲሁም ኢንቨስት ያደርጋሉ። ይህ ክፍተት ማለት አሜሪካ ከምትሸጠው በላይ ከአለም እንድትገዛ አድርጓታል። ስለዚህ ይህ እስከቀጠለ ድረስ አሜሪካ በአለም አቀፍ የንግድ አጋሮቿ ጋር ታሪፍ ብትጨምርም የንግድ ጉድለቷ በዚያው ሊቀጥል ይችላል።

አንዳንድ የንግድ ጉድለቶች ከታሪፎች ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ለምሳሌ በሌሎች አገራት ለማምረት ቀላል ወይም ርካሽ የሆነ ምግብ መግዛት ሊሆን ይችላል።

"ቀመሩ አሜሪካ የንግድ ጉድለት ባለባት አገሮች ላይ ታሪፍን መጣል ምክንያታዊ ለማድረግ ሞክሯል። ይህንን ለማድረግ ምጣኔ ኃብታዊ ምክንያት የለም። የዓለምን ምጣኔ ኃብትም እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለዋል" ሲሉ በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ባልደረባ የሆኑት ቶማስ ሳምፕሰን ይናገራሉ።